Thursday, July 04, 2013

ታላቁ የህዳሴ ግድብን መቃወም የፖለቲካ ክስረትን ያስከትላል!

(July 05, 2013, (አዲስ አበባ))--ኢትዮጵያ ባለፉት 12 ዓመታት ገደማ ዘርፈ ብዙ ዕድገትን ማስመዝገብ ችላለች። ይህ ግስጋሴ ተከታታይና ባለሁለት አኀዝ የኢኮኖሚ ዕድገት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊና ለመጪው ዘመን መሠረት የተጣለበት መሆኑ ሌላ ስኬት ነው። የቀጣዮቹን ሁለት ዓመታት ጨምሮ ሽግግራዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተጣለውም ይህንኑ ዕድገት ይበልጥ ለማረጋገጥ ነው።

ከዕቅዱ ዘርፍ ብዙ ተግባራት አንዱ የሆነው የኃይል ማመንጫ ግንባታ ሥራም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን እንደሚሆን ተቀምጧል። ገና ከፕሮጀክቱ ጅማሮ አንስቶ የመላውን ሕዝብ ጠንካራ ድጋፍ ያገኘው ይህ ሥራ መንግሥትም በልዩ ትኩረትና ተነሳሽነት እየተገበረው ይገኛል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የግብጽ አንዳንድ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች «የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ» በማራመድ ፕሮጀክቱን ኢ ፍትሐዊ ለማስመሰል ሞክረዋል። የተፋሰስ ሀገራቱን የ12 ዓመታት ድርድርና ድካም ችላ ያለ፣ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ያላተኮረ የግል ጥቅምን ብቻ ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ ለማንም እንደማይበጅ የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ዓለም እየተናገረ ነው።

አንዳንድ የሀገራችን ተቃዋሚዎች ደግሞ ከሕዝብ የሚነጠሉበትን አጉል እሰጣ አገባ ውስጥ ሲገቡ እየተስተዋሉ ነው፡፡ በአንድ በኩል የፕሮጀክቱን ፋይዳና የመጪው ጊዜ የሀገሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምሰሶ መሆኑን በመዘንጋት በሌላ አነስተኛ የኃይል ማመንጫ ሥራዎች መተካት አለበት ይላሉ። ሲፈልጉም ድርድሩ በቂ አይደለም። የሚገነባበት ቦታ ለጥቃት የተጋለጠ ነው። በቂ በጀት አልተያዘለትም። በአሥር ዓመትም አያልቅም። ኢህአዴግ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ አውሎታል... ይላሉ።

በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት መቃወም የማይገሰስ መብት ቢሆንም «ሁሉንም ነገር መቃወም!» ደግሞ ጤነኝነት አይደለም። ዛሬ ሀገሪቱ በጀመረችው ፈጣን ዕድገት ምክንያት ኃይል እንደ ቁምጣ እያጠራት ነው። አንድ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ እስከ 300 ሜጋዋት እየጠየቀ ነው። በዚያ ላይ ለዘመናት ያልተደፈረና ሲጎዳን የነበረን ወንዝ ጥቅም ላይ ለማዋል ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ተደራድሮ ሕዝብ አሳምኖ አቅሙን አሟጥጦ ልሥራ ያለ መንግሥት ሊመሰገንና ሊደገፍ ሲገባው ለተቃውሞ ሲባል ብቻ « መናገር» ትዝብት ላይ ይጥላል። የፖለቲካ ውድቀትና ሞትንም ከማፋጠን ያለፈ ፋይዳ የለውም።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ለ100 ዓመት ያህል በየቀኑ በአማካኝ 2 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ ያስገኛል የሚለውን የሥነ ምጣኔ ትንታኔስ ፓርቲዎች እንዴት ቢያዩት ነው? ነዳጅ አምራች ያልሆነችው ሀገራችን ከእዚህ ሌላስ ምን ያህል ጠቃሚ የተፈጥሮ ሀብት ጥቅም ላይ ልታውል ትችላለች። ስለሆነም መንግሥት መላው ሕዝብ ተቃዋሚዎችም ሆኑ ሌሎች የሲቪክ ማኅበራት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሊለያዩ የሚችሉበት ጉዳይ የለም። ለአመል « ለመቃወም» ካልሆነ!

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን «... በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ሀገራችን የያዘችውን አቋም የዓለም ኅብረተሰብም እየተቀበለው ነው፡፡ አሁንም ፍላጎታችን በቅርበት በመወያየት በመደራደር እንዲሁም ሰጥቶ በመቀበል ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማራመድ ነው!» ብለዋል። ከእዚህ ውጪ ያለ አሰላለፍ ተራ ሁካታና « ቀባሪ የሚያሳጣ» የፖለቲካ ክስረት ነው።
ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment