Wednesday, July 31, 2013

ወደ ጁባ ሊያመራ የነበረ የሩሲያ ሄሊኮፕር ወድቆ ተከሰከሰ

(July 31, 2013, (አዲስ አበባ))--ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተልእኮ ወደ ደቡብ ሱዳን ጁባ ለማምራት በዝግጅት ላይ የነበረ አንድ የሩሲያ ሄሊኮፕር ወድቆ መከስከሱን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሸን ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ እንዳስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በደቡብ ሱዳን ጁባ ለሚያካሂደው ተልእኮ ሁለት የሩሲያ ሄሊኮፕተሮች ከጅቡቲ በአዲስ አበባ ቦሌ አለም  አቀፍ ኤርፖርት ነዳጅ ለመሙላትና ለቴክኒክ ፍተሻ በረራ በማድረግ ላይ ነበሩ።

ከሁለቱ ሄሊኮፕተሮች መካከል አንዱ ለጊዜው በውል ባልታወቀ ምክንያት ዛሬ ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ20 ደቂቃ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ልዩ ሰሙ ጨፌ ዲንሳ አካባቢ ወድቆ መከስከሱን ባለስልጣኑ አስታውቋል። በተከሰከሰው ሄሊኮፕተር ውስጥ ሁለት አብራሪዎችን ጨምሮ አራት ሰዎች በውስጡ ተሳፍረው እንደነበር የገለጸው ባለስልጣኑ በአደጋው ሳቢያ ከአካል ጉዳት በስተቀር የህይወት ህልፈት አለመኖሩንም አመልክቷል።

በአደጋው የተጎዱት ሰዎች ለመርዳት የኢትዮጵያ አየር ሃይል ሄሊኮፕተሮች በፍጥነት በስፍራው በመድረስ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመሆን በህይወት ማዳን ዘመቻው ላይ ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን ባለስልጣኑ አመልክቷል።

የአደጋውን መንስኤ ምንነት ለማጣራት ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጣ የብሄራዊ ፈልጎ ማዳን ኮሚቴና ልዩ የምርመራ ቡድን ነገ ሌሊት ወደ ስፍራው ለመጋዝ ዝግጅት ማጠናቀቁን ባለስልጣኑ አስታውቋል።
ምንጭ፡ ኢሬቴድ

No comments:

Post a Comment