Monday, June 17, 2013

ዋልያዎቹ ታሪክ ሠሩ

(Jun 17, 2013, (አዲስ አበባ))--የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች (ዋልያዎቹ) ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ድልድል በመግባት የአገራችንን የእግር ኳስ ታሪክ ቀየሩ፡፡ ዋልያዎቹ ወደ ብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከአስር ምርጥ የአፍሪካ ቡድኖች መካከል በመካተትም የቀድሞ ታሪካቸውን ቀይረው አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል፡፡

ዋልያዎቹ ወደ ብራዚል የሚወስዳቸውን ትኬት ለመቁረጥ የመቶ ሰማንያ ደቂቃ ጨዋታ ብቻ ይቀራቸዋል፡፡ ለዋልያዎቹ ታሪካዊ ቀን በሆነችው በትናንቷ ዕለተ ሰንበት አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታድየም በደጋፊዎች ደስታ ተጥለቅልቆ አምሽቷል፡፡

በማጣሪያው የምድብ ድልድል ከሳምንት በፊት ቦትስዋናን ከሜዳቸው ውጪ ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ያሸነፉት ዋልያዎቹ፣ ምድባቸውን በአስር ነጥብ በመምራት የደቡብ አፍሪካ ከዋክብት የሆኑትን ባፋና ባፋናዎችን በሜዳቸው ለመግጠም የአንድ ሳምንት ልምምድ ብቻ ነበር ያደረጉት፡ ዋልያዎቹ በጨዋታው የተለመደውን ማራኪ ጨዋታ ያሳያሉ ተብሎ ቢገመትም ደካማ ሊባል የሚችል አቋም አሳይተዋል፡፡ በጨዋታው ሙሉ በሙሉ ተበልጠዋል ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመው የታሪክ ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡

በጨዋታው ሙሉ ነጥብ ይዘው ለመመለስ አቅደው የመጡት የጎርደን ኢግሰንድ ልጆች ማራኪ የሚባል ጨዋታ ቢጫወቱም ዕድል ከእነርሱ ጋር አልነበረችም፡፡ እናም ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ተሸንፈው ከዓለም ዋንጫው የጥሎ ማለፍ ድልድል መውጣታቸውን አረጋግጠው ወደ መጡበት ተመልሰዋል፡፡

ግቧ ከተቆጠረች በኋላም ባፋናባፋናዎች በማራኪ የኳስ ፍሰት ዋልያዎቹን ቢያስጨንቁም ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው ያለቀላቸውን ኳሶች በማምከን ትልቅ ሥራ ሠርቷል፡፡ ዋልያዎቹ የጨዋታ ብልጫ ቢወሰድባቸውም በአገኙት አጋጣሚ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ በተለይም ፕሮፌሽናሉ ሳላዲን ሰዒድ ያደረጋቸው ጠንካራ ሙከራዎች በደቡብ አፍሪካው ግብ ጠባቂ መክሸፋቸው የሚያስቆጭ ነበር፡፡

ባፋናባፋናዎች የመጀመሪያው አርባ አምስት ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች እስኪቀሩት ድረስ የጨዋታ የበላይነታቸውን ይዘው መረባቸውን አላስደፈሩም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በአማካይና አጥቂዎች መካከል መናበብ የጎደላቸው ዋልያዎቹ አርባ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ ተረባርበው ወደ ባፋናባፋናዎች ግብ ክልል የወሰዷት ኳስ በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ከመረብ አርፋ አቻ ሆነው የመጀመሪያውን አርባ አምስት ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡

የደደቢቱ የፊት መስመር ተጫዋች ጌታነህ በዓለም ዋንጫው ማጣሪያ ለዋልያዎቹ ሁለተኛውን ግብ ከመረብ በማሳረፍ ለተመዘገበው ደማቅ ታሪክ ባለ ውለታ ሆኗል፡፡ ጌታነህ በኢትዮጵያ ብሪሚየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ከመሆኑም ባሻገር በዓለም ዋንጫው ማጣሪያ ቦትስዋና ላይ ሁለት ግቦችን ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡

በሁለተኛው አርባ አምስት አሰላለፋቸውን ሳይቀይሩ የገቡት የዋልያዎቹ ዋና አሠልጣኝ ሠውነት ቢሻው ጨዋታ መቀየርና የተሻለ የኳስ ቁጥጥርን መፍጠር አልቻሉም፡፡ በእዚህም ምክንያት ግብ ጠባቂው ጀማል ሥራ በዝቶበት ተስተውሏል፡፡ ብዙም ሳይቆይ ጨዋታ አቀጣጣዩን ሽመልስ በቀለን ቀይሮ የገባው አዳነ ግርማ ጨዋታ በማደራጀት ዋልያዎቹ በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ እንዲሆኑ ጥረት አድርጓል፡፡ ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ተረጋግተው መጫወት ባለመቻላቸው የተወሰደባቸውን የጨዋታ ብልጫ መቀልበስ አልቻሉም፡፡

በሁለተኛው አርባ አምስት ወጣ ገባ ያለ አቋም ሲስተዋልባቸው የነበሩት ዋልያዎቹ ታሪክ የሠሩበት ሰዓት ሰባኛ ደቂቃ ላይ ደረሱ። ባፋናባፋናዎቹ በቀኝ ክንፍ በኩል ጥፋት በመሥራታቸው ግብፃዊው ዳኛ ቅጣት ምት ሰጡ፡፡ የዋልያዎቹ የቅጣት ምት ጥበበኛ የሆነው አበባው ቡጣቆ ቅጣት ምቱን ከሩቅ አክርሮ በመምታት የባፋናባፋናዎች በርናርድ ፓርከር አናት ላይ አሳረፋት፡፡ ኳሷም አቅጣጫዋን ስታ መረብ ላይ በማረፍ ዋልያዎቹን ባለታሪክ ለማድረግ በቃች፡፡ ግቧ ከተቆጠረች በኋላ ባፋናባፋናዎቹ ዋልያዎቹን በማስጨነቅ ቢጫወቱም መነቃቃት የተፈጠረባቸው ባለታሪኮቹ ግባቸው እንዲደፈር አልፈቀዱም፡፡ ባፋናባፋናዎቹ አቻ የምታደር ጋቸውን ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ትንቅንቅ በተጫዋቾች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡

ጨዋታውን በትክክል አይዳኙም ተብሎ ተፈርተው የነበሩት አራቱም ግብፃውያን ዳኞች ጨዋታውን በትክክል መርተዋል ማለት ይቻላል፡፡ ከጨዋታው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ብርድና ዝናብ እየተፈራረቀበት የስታድየም መግቢያ ተራ ሲጠብቅ የነበረው የአገራችን እግር ኳስ አፍቃሪ ትናንት ልዩ ቀናቸው ነበረች፡፡ በተለይም ለደቡብ አፍሪካው የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ የተለያዩ ፅሑፎችን ያስነበቡበት ሁኔታ የሚያስመሰግናቸው ሆኗል፡፡

ለእዚህ ድል ዋነኞቹ ምክንያቶች ደጋፊዎች ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ከሃያ አራት ሰዓት ቀደም ብለው ስታድየም በር ላይ ውለው አድረው ለቡድናቸው የሞቀ ድጋፍ በማድረግ ለዋልያዎቹ ድል ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በመጨረሻም የዘሩትን ደስታ አጭደው አዲስ አበባ የትናንቱን ምሽት በደስታ እንድታሳልፍ አድርገዋል፡፡ በመጀመሪያው አርባ አምስት ደቂቃ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር የዋልያዎቹን ተከላካዮች ማስጨነቅ የቻሉት ባፋናባፋናዎች በሠላሳ ሦስተኛው ደቂቃ ላይ መሪ የምታደርጋቸውን ግብ በአስራ ሰባት ቁጥሩ ፓርከር አማካኝነት ከመረብ በማሳረፍ ጨዋታውን መቆጣጠር ችለው ነበር፡፡
ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment