Saturday, June 01, 2013

ቡድኑ ሪፖርቱን ይፋ አደረገ /ሙሉ መግለጫ/

(June 01, 2013, (አዲስ አበባ))--የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ባቀረበዉ ሪፖርት ላይ ከዉሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተሰጠው መግለጫ የሚከተለው ነዉ፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ  መንግስት የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመሩን መጋቢት 24 ቀን 2003 አመተ ምህረት በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትራችን በክቡር አቶ መለስ ዜናዊ በተጣለው የመሰረት ድንጋይ ለአለም ማህበረሰብ መበሰሩ ይታወሳል፡፡

ግድቡ በመላ አገራችን ህዝቦችና  በልማታዊ መንግስታችን ጥረት የሚገነባ ቢሆንም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስቱንም የአባይ ተፋሰስ አገራት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡

የኢፌድሪ መንግስት በአባይ ወንዝ ላይ የዚህ ታላቅ ግድብ መገንባት የተፋሰሱ የታችኛው ተጋሪ አገሮች ማለትም በግብፅና በሱዳን  በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ግልፅነት፣ በቂ ግንዛቤ መተማመንና መረዳዳት የሚዳብርበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጠቃሚ መሆኑን በማመን በወሰደው ተነሳሽነት በሶስቱም አገሮች ትብብር አንድ አለም አቀፍ የባለሞዎች ቡድን እንዲቋቋም አድርጓል፡፡

አለም አቀፍ ቡድኑ ከየአገሮቹ የተውጣጡ  ስድስት ባለሞያዎችና በሶስቱ አገሮች የተመረጡ አራት አለም አቀፍ ባለሞያዎች እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ ቡድኑ ስራውን ከመጀመሩ በፊት የሶስቱ አገሮች የውሃ ጉዳይ ሚንስትሮች በአዲስ አበባ ላይ በመገናኘት በተስማሙበት መሰረት በተቀረፀ የስራ ዝርዝርና የአሰራር ስነ-ስርአት እንዲመራም ተደርጓል፡፡ ለአለም አቀፍ የሙያተኞች ቡድን ስራ የሚያስፈልገው ወጭም በሶስቱ አገሮች በጋራ እንዲሸፈን ተደርጓል፡፡

አለም አቀፉ የባለሞያዎች ቡድን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለሶስቱ የተፋሱ አገሮች ግብጽ፣ሱዳንና ኢትዮጵያ የሚሰጠውን ጥቅም፥ እንዲሁም ግድቡ በሁለቱ የታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ላይ የሚያደሰው ጉዳት ካለ የፕሮጀክቱን የጥናት ሰነድ በመመልከት፥ በጥናት ሂደት ውስጥ ያልታዩ ወይንም በደንብ ያልተዳሰሱ ጉዳዮች ካሉ ለይቶ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት አስፈላጊውን የማስተካከከያ እርምጃ እንዲወስድ ሀሳብ የማቅረብ ሃላፊነት የተጣለበት አካል ነው፡፡

የባለሞያ ቡድኑ ባለፈው አንድ አመት የታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የጥናትና የዲዛይን ሰነድ በመመርመር ፣በግንባታዉ ቦታ በመገኘትና ሂደቱን በመቃኘት፣ በሶስቱ አገሮች ውስጥ ለስድስት ጊዜ ያህል ተሰብስቦ በተነሱ ጉዳዮች ላይ በመወያየት እንዲሁም ከግድቡ የግንባታ ተቋራጮችና አማካሪዎች ጋር በመመካከር የደረሰበትን የመጨረሻ የጥናት ውጤት ለሶስቱ አገሮች መንግስታት ግንቦት 23 ቀን 2005 አ.ም አቅርቧል፡፡

በዚህም መሰረት ኢትዮጵያን በባለሞያ ቡድኑ የወከሉ አባላት በተጠቀሰው እለት የሶስቱም አገራት ተወካዮችና አለም አቀፍ ባለሞያዎች ተስማምተው የፈረሙበትን የቡድኑን የመጨረሻ ሪፖርት ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስረክበዋል፡፡

በሪፖርቱ መሰረት፦

* የኢትዮጵያ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የዲዛይን ስራ አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ የዲዛይን መመዘኛና መርሆዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑን

* ለሶስቱም አገራት ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ መሆኑን

* በሁለቱ ተጋሪ አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት የማያደርስ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በማያያዝም በግድቡ መገንባት የሚገኙ ጥቅሞችና ሊደርሱ የሚችሉ ችግሮች ካሉ አንዳንድ ተጨማሪ ጥናቶች እንዲጠኑ የጠየቀ ሲሆን፥ የግድብ ግንባታ ለተፋሰሱ አገራት የተሻለ ጥቅም እዲሰጥ የሚረዱ ሃሳቦችን አቅርቧል፡፡ ቡድኑ አገራችን ይህን የኤክስፐርቶች ቡድን በማቋቋም ከሁለቱ አገራት ጋር መተማመንን ለመፍጠር የወሰደችውን እርምጃ አድንቋል ፡፡

መንግስታችን የቀረበው የቡድኑን ሪፖርት በጥንቃቄ በመመርመር ከሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ጋር በቀጣይነት የትብብር መድረክ ተፈጥሮ ለጋራ ጥቅም በጋራ የሚሰራበት ሁኔታን ያመቻቻል፡፡

በዚሁ አጋጣሚ የሁለቱ አገራት መንግስታት ላደረጉት ትብብር ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ እንዲሁም የአለም አቀፍ የባለሞያ ቡድኑ ላለፈው አንድ አመት በአገራቱ መካከል መተማመንና ግልጽነት እንዲፈጠር ላደረገው ጥረት ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ ከተፋሰሱ አባል አገራት ያለንን ጥብቅ ትብብርና ወዳጅነት በማጠናከር በናይል ጉዳይ  በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነታችን ይቀጥላል ፡፡

በባለሞያ ቡድኑ ውስጥ ኢትዮጰያን የወከሉት አባላት፥ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ተወካዮች ከበስተጀርባ በመሆን ከፍተኛ የሙያ ድጋፍ ይሰጥ የነበረው የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ብሄራዊ ባለሞያዎች ቡድን ለፈጸሙት ከፍተኛ አገራዊ አስተዋፆ ያለንን አድናቆትና ምስጋና እናቀርባለን፡፡

የባለሞያ ቡድኑ ስራ እንዲሳካ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለተሳተፉ የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ያለንን አክብሮት እንገልፃለን፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብ ርብርብ የህዳሴው ግድብ እውን ይሆናል፡፡
ምንጭ፡ ኢሬቴድ

No comments:

Post a Comment