Friday, April 19, 2013

አሰልጣኝ ሠውነት መንግሥት ለእርሳቸውና ለቤተሰባቸው ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ

(Apr 19, 2013, (አዲስ አበባ))--የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሠውነት ቢሻው የተወሰኑ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በተለያዩ ጊዜዎች እያደረሱባቸው የሚገኘው ጫና ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው በመግለጽ ጫናው በእርሳቸውና በቤተሰባቸው ላይ ጉዳት ይደርሳል የሚል ስጋት ስለፈጠረባቸው « መንግሥት ጥበቃ ያድርግልኝ » ሲሉ ጠይቀዋል።

አሰልጣኙ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጻፉትና ለመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፣ ለፌዴራልና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ፣ለስፖርት ኮሚሽን ፣ ለኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እንዲሁም ለመንግሥትና ለግል የመገናኛ ብዙኃን በግልባጭ ባሳወቁት ደብዳቤያቸው ላይ እንደገለጹት የተለመደ ስራቸውን ለማከናወን ስቴዲየም በሚገኙባቸው አጋጣሚዎች ከተወሰኑ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች እየደረሰባቸው የሚገኘው ከስፖርቱ ስነ ምግባር ውጪ የሆነ ድርጊት በስራቸው ላይ ጫና ፈጥሮባቸዋል። ይህ ድርጊት በእርሳቸውና በቤተሰባቸው ላይ አደጋ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ስለፈጠረባቸው መንግሥት ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ለመጠየቅ አስገድዷቸዋል።

አሰልጣኝ ሰውነት ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በፊርማቸው አስደግፈው በላኩት መግለጫ ፤ እነኝህ «የተወሰኑ » ሲሉ የገለጿቸው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የካቲት 26 ቀን 2005ዓ.ም ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከቤኒን አቻው ጋር በአዲስ አበባ ስቴዲየም በተጫወተበት ወቅት የእርሳቸውንና የቡድኑን ተጫዋቾች ስብዕና የሚነካ ስድብና ዘለፋ በመሰንዘራቸው ተጫዋቾቻቸው ውጤት እንዳያስመዘግቡ እንቅፋት ሆነዋል ብለዋል።

በተመሳሳይ መጋቢት 15 ቀን 2005ዓ.ም ብሔራዊ ቡድኑ ከቦትስዋና አቻው ጋር በአዲስ አበባ ስቴዲየም ባደረገው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ እነዚሁ ደጋፊዎች « ሠውነት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ገዳይ፤ ሠውነት ጋዳፊ » እያሉ የስራ ነጻነታቸውን ፣ ሞራላቸውንና ስብዕናቸውን የሚፈታተኑ አጸያፊ ቃላት እንደወረወሩባቸው በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።

«ይህ ድርጊት በስሜታዊነት የተሰነዘረ ነው ብዬ ለማለፍ ብሞክርም ሁኔታው ከመቆም ይልቅ ፍጹም በተደራጀ መልኩ ተከስቷል » በማለት በመግለጫቸው የጠቀሱት አሰልጣኝ ሠውነት ፤ ሚያዚያ 5 ቀን 2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች ባደረጉት ጨዋታ ላይ ድርጊቱ ከቀድሞው በበለጠ መልኩ መከሰቱን አስታውቀዋል።

ይህ ሁኔታ በማንኛውም ጊዜ በእርሳቸውና በቤተሰባቸው ላይ አደጋ ይደርሳል የሚል ስጋት እንዲያድርባቸው እንዳደረገ በመግለጫቸው ገልጸዋል። በመሆኑም ስራቸውን ተረጋግተው እንዲሰሩ መንግሥት ሁኔታውን ተከታትሎ የማያዳግም መፍትሔ እንዲሰጣቸውና ፣ ለእርሳቸውና ለቤተሰባቸው ጥበቃ እንዲደረግላቸው በመግለጫቸው ጠይቀዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ « ስብሰባ እየመራሁ ነው » በሚል ምላሽ ሊሳካልን አልቻለም። የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ ክለባቸው ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment