Sunday, March 10, 2013

የሳዑዲውን ልዑል ምን ነካቸው?

(Mar 10, 2013, (አዲስ አበባ, ኢትዮጵያ))--የሳዑዲው ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ካሊድ ቢን ሱልጣን ወይም አል ሪያድ የሳዑዲ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ናቸው። ስልጣናቸው በሳዑዲ ጉዳይ እንዲያገባቸውና እንደ መከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስልጣን አካል እንዲናገሩ ይፈቅዳል። ለዚህም ነው ምክትል የመከላከያ ሚኒስትሩ ሀገራቸውን ሆነውና ሳዑዲን ወክለው በግብፅ ካይሮ የአረብ አገሮች የውሃ ካውንስል ስብሰባ ላይ የተገኙት፤ የተናገሩትም። 

እናም እኚህ ሰው በስፍራው የተናገሩት እያንዳንዷ ቃል የሳዑዲ መንግስት አቋም መሆኑን፤ አለያም ይህን ያልኩት በግል ከተሰማኝ ስሜት ነው፤ ወይም የግል አስተያየቴ ነው ማለት ይጠበቅባቸዋል። እሳቸው የሳዑዲን መንግስት ወክለው በተገኙበት መድረክ የተናገሩት ቀጣዩ ቃል ምን ይዘት አለው። «ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ብላ ከሱዳን 12 ኪሎ ሜትር ያህል በሚርቀው ቦታ እየገነባች ያለው ግድብ ፖለቲካዊ ትርጉሙ እንጂ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው አይታየኝም፤ ይልቁንም ሀገሪቱ የአረብ ሀገራትን ባገኘችው አጋጣሚ ለመጉዳት የምታደርገው ጥረት ማሳያ ነው። 
 
«የግድቡ መጠናቀቅ ለሱዳንም ሆነ ለግብፅ አጥፊ ነው፤ ኢትዮጵያ ሱዳንን በውሃ ሊያጥለቀልቅ የሚችል፤ ግብፅን በውሃ የሚያስጠማ አቅጣጫ እየተከተለች ነው» ሲሉም ከወዳጅ ሀገር በማይጠበቅና ጣልቃ ገብ በሆነ የሀሰት ትንታኔ ንግግራቸውን ቋጩ።

ይህን ሀሰት ተኮር ትንታኔ ሱዳን ትሪቢዩን በገፁ ይፋ አደረገው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ወዳጅ ከሆነውና ጥሩ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ካለው ሳዑዲ ያልተጠበቀውን ገለፃ በመስማቱ አዘነ፤ ማብራሪያ እንዲሰጠውም ጠየቀ፤ እውን ይህ የሳዑዲ አቋም ነውን? ሳዑዲም መለሰች... ገለፃው የሳዑዲ አቋም አይደለም፤ እኛና ኢትዮጵያ የተጠናከረ ወዳጅነት ያለን ሀገሮች ነን፤ ትስስራችንና ትብብራችን ይቀጥላል። የግለሰቡ ሀሳብ የሳዑዲ ተደርጎም መወሰድ የለበትም።
ኢትዮጵያ በ«ምክትል ሚኒስትሩና ልዑሉ» ሃሳብ አልተደሰተችም፤ አለመደሰቷ በመንግስቷ ብቻ ሳይሆን በሀገሩ ልማት አንድ ሆኖ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ በሆነው ህዝብም ጭምር የተስተዋለ ነው።

ልዑሉን ምን ነካቸው? ሃሳቡ ከተሳሳተ ግንዛቤ የሚነሳ ቢሆንም ከግብፅ ወይም ከሱዳን ቢመጣ ኖሮ ያው በአግባቡ ሙሉ ግንዛቤ ካልተፈጠረበት አስተሳሰብ የመነጨ ነው ሊባል ይችል ነበር፤ ተናጋሪው ግን የሳዑዲው ልዑልና የመከላከያ ምክትል ሚኒስትር ናቸው።

ሳዑዲ የሚኒስትሩን አቋም አቋሜ አይደለም ብትልም፤ የኢትዮጵያ መንግስትም የሳዑዲን ማስተባበያ ቢያሳውቅም የገለፃውና የማስተባበያው ፖለቲካዊ ትርጉም አሁንም ህብር ነው፤ ወደፈለጉት ሊፈቱት የሚችል ጥንቃቄና ጥርጣሬ የሚሻ ጉዳይ መሆኑም በግልጽ መታየት ጀምሯል። የሳዑዲን የማስተባበል አቅጣጫ ጥሩ ነው ብለን ብንቀበለውም እንደ መንግስት በካውንስሉ ስብሰባ የተገኙት ሰው ተራ ግለሰብ ባለመሆናቸው ሃሳባቸው ይከብደናል።

በግብፅና በሱዳን ጉዳይ እንደ አረብ ሀገር ተቆርቁረው ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን የአረቦች ጠላት አድርገው በመፈረጅ የተፈላሰፉበትና ነቢይ የሆኑበት ሃሳብ በጥልቅ ሊመረመር ይገባል። በሀገራችን ላይ የተቃጣ አደገኛ ጉዳይ ተደርጎም መወሰድ ያለበት ነው። ግን ደግሞ ገለፃቸው የበለጠ ያጠናክረን እንደሆነ እንጂ አያስፈራንም። 

እንኳንስ እንዲህ አንድ ሆነን ሃሳባችንንም፣ ጉልበታችንንም፣ ገንዘባችንንም ስንቅ አድርገን በገባንበት ጉዳይ ቀርቶ፣ የህዳሴያችንንና የብልፅግናችን መንገድ መጀመሪያ በሆነው የአብሮነታችን መታያ በሆነው ጅምር ጉዟችን ላይ የተቃጣ ሴራ መሆኑም ቀርቶ፣ በእልህና በቁጭት በሌለን ካፒታል የጀመርነው ሐውልታችን መሆኑ ቀርቶ... ሀገራችንና ህዝባችንን በሚመለከት ትንሿም ጉዳይ ኢትዮጵያውያኖች ክፍተት አንሰጥም። 

ልዩነታችን ሀገራችንን የሚያበለጽገውና የሚያሳድገው የትኛው ነው በሚል መሆን አለበት እንጂ ኢትዮጵያውያን ሆነን ለሀገራችን ከጠላት ጋር የምንሰለፍበት እድል የለም፤ ይልቅ ጠላታችን ድህነት ነው።

እኚህ ሰው «የወዳጅ ሀገር መንግስትን» ወክለው በልማታችን ላይ ያለንን ህብረት ሊያጨናግፉ፣ ከጎረቤት ሀገሮች ህዝቦች ጋር ሊያለያየን ወይም ጥርጣሬ ሊፈጥርብን የሚችል ጥፋት አውጀዋል። መንግስት ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት ፈጣን፣ ተገቢና ጥንቃቄ የታከለበት ቢሆንም ብዙዎች የሳዑዲን መንግስት ምላሽ አልረኩበትም። 

የሳዑዲ መንግስት ከዚህ የተሻለ ማብራሪያ እየደጋገመ ሊሰጠንና ሊያሳምነን ይገባል የሚሉ ሃሳቦች ብቅ እያሉ ነው፤ በተለይ ምሁራኑ ጥርጣሬያቸው ጎላ ብሏል፤ ሰውየው የሳዑዲ መንግስት ሁነኛ ባለስልጣን እንጂ መንገደኛ አይደሉም በሚል፤ ማስተባበያውም ማስተዛዘኛ ካልሆነ በቀር ቁም ነገር አይታይበትም በሚል፤ መንግስት በውሃ ጉዳይ ከሚፈራረመው ስምምነት በዘለለ ጥንቃቄውን ያጠናክር በሚል፤ ሀገራችንንና መንግስታችን ሉዓላዊነታቸውንም የሚያስነኩበት እድል የለምም በሚል ጭምር።

በነገው እትማችን የመንግስታችን አቋም «ብዙም ከማያሳምነው የሳዑዲ ምላሽ» አንፃር ምንድን ነው? ምንስ ሊሆን ይገባል? በብሄራዊ ጥቅማችን ጉዳይ የመገናኛ ብዙሃኖቻችን አቋም ምን መሆን አለበት? አሁንስ ያለበት ደረጃ ምንድን ነው?

የሀገራችን የፖለቲካ ምሁራን እንደ ሌሎች አገሮች ምሁራኖች በእንዲህ አይነቱ ወሳኝና ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ሃሳብ በማካፈልና አቋማቸውን በግልፅ ላለማቅረብ ያሉባቸው ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? ምንስ ሊያደርጉ ይገባል? በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር መረራ ጉዲና፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር አብዲሳ ዘርዓይ ያካፈሉንን ሃሳብ ይዘን እንቀርባለን። እስከ ነገ የሳዑዲውን ልዑል ምን ነካቸው እያልን ብንቆይስ?
አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment