Friday, September 27, 2013

የመስቀል ደመራ በአል በአዲስ አበባ በደማቅ ስነ-ስርአት ተከበረ

(Sept 26, 2013, (አዲስ አበባ))--የመስቀል ደመራ በአል ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ ዲፕሎማቶችና አምባሳደሮች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጥንግ ድርብ የለበሱ ሊቃውንት፣ ካህናትና ምእመናን በተገኙበት በደማቅ ስነ-ስርአት ተከበረ፡፡

በብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትሪያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የቡራኬ ፀሎት በተጀመረው ስነ-ስርአት የአዲስ አበባ ከንቲባ የአቶ ድሪባ ኩማ ተወካይ በመክፈቻ ንግግራቸው የመስቀል ደመራ በአል የሀገራችን ብሄር ብሀሄረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት በድምቀት ሲያከብሩት የኖሩት ሃይማኖታዊ በአል ብቻ ሳይሆን ታሪካችንን፣ የቱሪዝም ሀብቶችንና ሌሎች እሴቶቻችን  ለሌላው ዓለም የምናስተዋውቅበት የማንነታችን መገለጫ ጭምር ነው ብለዋል፡፡

በአይሁዳውያን ተቀብሮ የነበረውን እና በንግስት እሌኒ የተገኘውን መስቀል ለማሰብ በዓሉን ኢትዮጵያውያን  እንደሚያከብሩት፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ተናግረዋል።

ብፁእነታቸው ኢትዮጵያውያን የተገኘውን መስቀል በማሰብ የመስቀሉን በረከት ለማግኘት እንደሚያከብሩትም ነው የተናገሩት። የመስቀል በዓል ለዘመናት ኢትዮጵያውያን በጋራ ሲያከብሩት የቆዩት በዓል መሆኑን ያወሱት ብፁዕነታቸው ፤ ህዝቦች ተከባብረውና ተቻችለው ለመኖራቸው ተምሳሌት መሆኑንም አስረድተዋል።

እናም የመስቀል በዓል በአለም ቅርስነት እንዲመዘገብ የሚደረገው ጥረትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። በበአሉ ጥንግ ድርብ የለበሱ ካህናቶችና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተለያዩ ዝማሬዎችን አቅርበዋል። የደመራ መለኮስ ስነ ስርአቱ ተካሂዶ የደመራው በአል ፍጻሜ ሆኗል ፤ በነገው እለትም የመስቀል በአል በተለያዩ ስነ ስርአቶች ይከበራል።
ምንጭ፡ ኢሬቴድ

No comments:

Post a Comment