Sunday, March 10, 2013

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሃያ ሁለት ተጫዋቾች ተመረጡ

(Mar 10, 2012, አዲስ አበባ, ኢትዮጵያ))--ዋልያዎቹ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ምድባቸውን በነጥብ እየመሩ ነው፤ በብራዚል አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በመሳተፍ ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአምስት የፕሪሚየር ሊግና ከአንድ የብሔራዊ ሊግ ክለቦች ሃያ ሁለት ተጫዋቾች ተመርጠዋል። ተጫዋቾቹ ዛሬ ሆቴል ገብተው ልምምዳቸውን እንደሚጀምሩም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዳስታወቀው ፤ በርካታ ተጫዋቾችን በማስመረጥ ደደቢትና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች ቅድሚያውን ሲይዙ ኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ሁለት ተጫዋቾችን አስመርጧል።

ለብሔራዊ ቡድኑ የ2005 .ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መለስ ዋንጫን በ22 ነጥብ በመምራት ላይ የሚገኘው ደደቢት እግር ኳስ ክለብ ዘጠኝ ተጫዋቾችን ሲያስመርጥ የአምናው የሊጉ ሻምፒዮና ቅዱስ ጊዮርጊስ ስምንት ተጫዋቾችን ለቡድኑ አበርክቷል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና መብራት ኃይል እግር ኳስ ክለቦች አንድ አንድ ተጫዋቾችን ሲያስመርጡ ሰበታ ከነማ አንድ ተጫዋቹን ለዋሊያዎቹ በማስመረጥ ብቸኛው የብሔራዊ ሊግ ክለብ ሆኗል።

ከደደቢት እግር ኳስ ክለብ ሲሳይ ባንጫ፣ አክሊሉ አየነው፣ ብርሃኑ ቦጋለ፣ ዓይናለም ኃይሉ፣ ስዩም ተስፋዬ፣ አዲስ ሕንጻ፣ በኃይሉ አሰፋ፣ ምንያህል ተሾመና ጌታነህ ከበደ ብሔራዊ ቡድኑ መጋቢት 15 ቀን 2005.ም ከቦትስዋና ጋር ለሚያደርገው የማጣሪያ ጨዋታ የተመረጡ ተጫዋቾች ናቸው ። ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በበኩሉ አምበሉን ደጉ ደበበን፣ ቢያድግልኝ ኤልያስን፣ አሉላ ግርማን፣ አበባው ቡጣቆን፣ ሽመልስ በቀለን፣ ዮናታን ብርሃኑን፣ ያሬድ ዝናቡንና አዳነ ግርማን ለብሔራዊ ቡድኑ አስመርጧል።
 
2003.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ ኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂውን ጀማል ጣሰውንና ኤፍሬም አሻሞን ለብሔራዊ ቡድኑ አበርክቷል። መብራት ኃይል አስራት መገርሳን፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፍጹም ተፈሪን ሲያስመርጡ በብሔራዊ ሊግ በመሳተፍ ላይ ከሚገኘው ሰበታ ከነማ ደረጀ ዓለሙ በቡድኑ ተካቷል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በተካሄደውና በናይጄሪያ አሸናፊነት በተጠናቀቀው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የዋሊያዎቹ አባል የነበሩት ሳላዲን ሰኢድን፣ ዩሱፍ ሳልህንና የፉአድ ኢብራሒም በቡድኑ ይካተቱ ወይም አይካተቱ ምንም ያለው ነገር የለም። መሪነቱን በደደቢት ከመነጠቁ በፊት ለበርካታ ሳምንታት ሊጉን ሲመራ ከቆየው ከሐዋሳ ከነማ አንድም ተጫዋች አለመመረጡ አስገራሚ ሆኗል። 

በአውሮፓውያኑ 2014 በብራዚል አስናጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ አርባ የአፍሪካ አገሮች በአስር ምድቦች ተከፍለው ማጣሪያቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ከአስሩ ምድቦች አንደኛ አንደኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ አስር ብሔራዊ ቡድኖች በአምስት ምድብ ተከፍለው በሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ አህጉሪቱን በዓለም ዋንጫው የሚወክሉ አምስት አገሮች ይለያሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ አንድ ከደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋናና ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር ተደልድሎ ጨዋታውን በማድረግ ላይ ይገኛል። ብሔራዊ ቡደኑ በማጣሪያው በሜዳውና ከሜዳው ውጪ አንድ አንድ ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን በሜዳው ሁለተኛውን ጨዋታ በመጋቢት ወር አጋማሽ ላይ ያደርጋል።

ብሔራዊ ቡድኑ በማጣሪያው ከደቡብ አፍሪካ ጋር ከሜዳው ውጪ፣ ከመካከለኛው አፍሪካ ጋር አዲስ አበባ ላይ ተጫውቶ ከደቡብ አፍሪካ አንድ ለአንድ አቻ ተለያይቶ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክን ሁለት ለዜሮ መርታቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከነዚህ ሁለት ጨዋታዎች በሰበሰባቸው አራት ነጥቦች ምድቡን በቀዳሚነት በመምራት ላይ ሲገኝ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በሦስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ደቡብ አፍሪካ ያደረገቻቸውን ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ በሁለት ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ቀጣይዋ የኢትዮጵያ ተጋጣሚ ቦትስዋና በአንድ ነጥብ ከምድቧ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ አንድ ግብ የተቆጠረበት ሲሆን ሦስቱንም ግቦች ከመረብ ላይ ያሳረፈው በቤልጅየም ሁለተኛ ዲቪዚዮን በመሳተፍ ላይ ለሚገኘው ሊርስ እግር ኳሰ ክለብ በመጫወት ላይ የሚገኘው ሳላዲን ሰኢድ መሆኑ ይታወሳል።



No comments:

Post a Comment