Sunday, March 10, 2013

«...ቁማርተኛ ጣቶች!!! »

(Mar 10, 2012, አዲስ አበባ, ኢትዮጵያ))--የሳዑዲው ልዑል በአረብ ሕዝብ ጥቅም ላይ ያነጣጠሩ ለራሳቸው የረባ ጥቅም የማይገነቡ ይሆነኝ ብለው የአረቡን ዓለም ለመጉዳት የሚያሴሩ ኢትዮጵያዊ ጣቶች እንዳሉ ነግረውናል:: ልዑሉ እሳቸው ደጃፍ በአረቡ ሕዝብ ስም የሚቦካው ለአረቡ ዓለም ሕዝብ ፋይዳ የሌለው ያረጀ ጎረቤትን በማደህየት የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚጥር ፖለቲካዊ አተያይ የማይገባን መስሎአቸው ከሆነ ስተዋል::

ኢትዮጵያንና የአፍሪካን ቀንድ የሚያምሰው የነማን ረጅም እጅ እንደሆነ እንረዳለን:: ይህ ረጅም እጅ መደፈቅ ያለበት ያረጀ የግብጽ ፖለቲከኞች ቁማር ነው:: ሁሌም የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ ጎረቤት በማተራመስና በማዳከም የሚያምን ደሀ አመለካከት:: እንዲህ ያለው አመለካከት ነው አስቦና ተጠቦ ሞቶ ከሰማንያ በመቶ በላይ ውሃ የምታበረክተውን አገር አንዳች ጠብታ ውሃ የማትጠቀምበትን ስምምነት ያሰረው::

ይሄ ያረጀው የግብጽ ፖለቲከኞች ቁማር በውጤታማ ዲፕሎማሲ ሲረታና ውሃው ፍትሀዊ ክፍፍል ሊደረግበት ጫፍ ሲደርስ የማይቀረውን ለማስቀረት ባለበሌለ ኃይሉ እየተፍጨረጨረ ነው:: የግብጽ ሕዝብ ኢትዮጵያ እየተራበች እኛ እንብላ የሚል ኢ-ፍትሀዊ አቋም አለው የሚል እምነት የለኝም::

የሳዑዲው ልዑል ሲሆን ሲሆን ወደ በራችን ያመጡትን ጣት በአግባቡ ቢጠቀሙበት ጥሩ ነበር:: ጣታቸውን በወሳኝ ብሄራዊ ጉዳያችን ውስጥ ሰንቅረው ሲያበቁ እንዲህ ለነተበ የማጋጨትና የማተራመስ አጀንዳ የተጠቀሙት መሆኑ ሃሳባቸውን ያኮስሰዋል ፣ያረክሰዋልም::

በእርግጥ ራሳችንን እንዴት መከላከልና ጥቅማችንን እንዴት ማስከበር እንዳለብን የምናውቅ በመሆኑ የልዑሉ አይነት የተረገሙ አስተያየቶች አያሰጉንም:: ያም ሆኖ በቀጣናችን ያረጁ የፖለቲካ ጓዳዎች የሚቦካውን እና እንደሚቦካ የምንጠረጥረውን የመከላከያ ባለሥልጣኑ ስላበሰሩን እናመሰግናቸዋለን:: የሱዳኑ የዜና ምንጭ በትክክል እንደጠቆመው ይሄ ንግግር ከጀርባው ሌላ ጉዳይ እንዳለው ተረድተናልም::

በቅርቡ ሙስሊሙ ያነሳውን የውስጥ ጉዳይ አስታከው ሀገር ወዳዱን ሙስሊም ይሸውዱት ይመስል ከጥያቄው ጀርባ ምን ሊሰሩ ይተጉ እንደነበር ተደርሶበታል:: አሁን ልዑሉ እንደነገሩን አጀንዳው ኢትዮጵያ ስታድግ ያመናል የኢትዮጵያ ማደግ ግብጽን ይጎዳል በሚል የሚቀነቀን እና በፍትሀዊው አገር ወዳድ ሙስሊም የውስጥ ጉዳይ በመግባት ኢትዮጵያ የማያባራ ቀውስ ውስጥ እንድትገባ በመመኘት እየሰሩት እንደሆነ እናውቃለን:: ይህ የቀውስ መረብ እየተበጣጠሰ ነው።

መረቡ የተበጠሰው ከኢጋድ ቀጣናዊ መዋቅር ጀምሮ በሌሎች አካላት እይታ ውስጥ መውደቁን ሲያውቁ ከዋሽንግተን እስከ ካይሮ፤ ከካይሮ እስከ ሪያድ ያሉ የእዚሁ ሴራ መረቦች ሁነኛ መልካቸውን እና አጀንዳቸውን ፍንትው አድርገው ይነግሩን ጀምረዋል:: የግብጻዊው ሰባኪ የጂሀድ አዋጅ በሀገር ወዳዱ ሙስሊም ስም ነው ፊልም የተሰራበት:: ኢትዮጵያዊው ጁሀርም ሃይማኖት ተንተርሶ የመጣው ሴራ አላማ የኢትዮጵያን መንግሥታዊ መዋቅሮች ማውደም እንደነበር በተባ ምላሱ ነግሮናል:: የሳዑዲው ልዑል ንግግርም በእዚሁ ማዕቀፍ የሚታይ ነው::

ልዑሉ ይቺ አገር የማይጠቅም ግድብ እየሰራች ያለችው ይሆነኝ ብላ የሱዳንን እና የግብጽን ጥቅም ለመጉዳት ነው የሚል ተረታቸውን ነው የነገሩን:: ልዑል ሆይ 6000 ሜጋ ዋት ኃይል ለእርስዎ ፋይዳ ቢስ ከሆነ ከጪሳሙ ነዳጅ ኤሌክትሪክ እንደሚያገኙ በመተማመኖ ሊሆን ይችላል:: ለእኛ 6000 ሜጋ ዋት ማለት እስካሁን የምናመርተውን ኤሌክትሪክ አቅም በሦስት እጥፍ የሚያሳድገው መሆኑን ጠንቅቀን እናውቃለን:: የማይጠቅም ግድብ የሚሆነው በርሶ የተቃወሰ ምዘና ካልሆነ በቀር ይህን የመሰለ ጥቅም የለም:: የማይጠቅመውስ የእርሶ የርጎ ዝንብነት የእርሶ ጣት የማይመለከታትን መጠንቆሏ ነው:: ሌላው የማብራሪያዎ ውበት ግድቡ ከፈረሰ ካርቱምን ይጠራርጋታል አስዋን ግድብንም ያሰጋዋል የሚለው ቅኝትዎ ነው::

ልዑል ሆይ አስዋን ቢፈርስስ ካይሮ አትጥለቀለቅም እንዴ? ከሆነ ደግሞ መሰራት አልነበረበትም ማለት ነው እንደርስዎ ገለጻ:: የሆነ ሆኖ ሞት ተፈርቶ መተኛት ስለማይቀር ተሰራ:: የእኛ ሲሆን ካርቱምን ስለሚያጥለቀልቅ አይሰራም የግብጾቹ ሲሆን ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ነው አይደል?! ልዑልነትዎ አይዞት ቢፈርስ እንኳ ከአስዋን ቀድሞ አይፈርስም:: ከፈረሰም አስዋን ከሚያስከትለው የበለጠም የተለየም ጉዳት አያደርስም:: እናም በርስዎም እርባናቢስ መከራከሪያ ቢሆን ግድባችን ፍትሀዊ ነው::

ልዑል ሆይ ሲፈርስ የሚከሰተው ያሳስቦታል? ባለመገንባቱ ኢትዮጵያና ቀጣናው የሚያጡት 6000 ሜጋ ዋት ኃይል አያስጨንቆትም? ይልቅ ልዑልነትዎ የሚሻለው ግድቡ እንዳይፈርስ የምዕራቡን ዓለም ባንክ ያጣበበውን ገንዘባችሁን ብታበድሩን ኖሮ ግድቡን ይበልጥ ጠንካራ አድርገን እንገነባው ነበር:: ለነገሩ ከእናንተ የጀርባ ውጋትነትም ጋር ቢሆን አስተማማኝ እና ጠንካራ ግድብ ነው እየሰራን ያለነው:: ሲፈርስ ካርቱም ስለምትጠፋ ብቻ ሳይሆን ከግድቡ የሚገኘውን ኃይል ዘላቂ ማድረግ ስለምንፈልግ:: ከደቃቃው አቅማችን የተሰበሰበውን ሀብት ማባከን ስለማንፈልግ እንዲያውም በመገንባቱ የሚጎዱ ያስመሰሏቸውን ግብጽንና ሱዳንን ስለሚጠቅምም ጭምር::

ልዑልሆይ አስዋንን እና የእኛን ግድብ ምን ይለየዋል? የእኛም ግድብ ለመብራት ኃይልና ለአሳ ምርት ቢያገለግል ነው ልክ አስዋን ለግብጾቹ እንደሚያደርገው:: ወይስ ኢትዮጵያ ውስጥ ናይል ሲገደብ ለአሸባሪ ፈንጂና ቦምብ የምናመርትበት አስመሰሉት:: የእኔ ጌታ እኛም ጋ ውሃ ሲገደብ ኃይል አሳ እና በተወሰነ ደረጃ መስኖ ሊሆን ቢችል ነው:: በባህሪው የአባይ አቀማመጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስኖ የመዋል እድሉ ጠባብ ቢሆንም::

በእርግጥ ጉዳዩን ለማብራራት ቀናነት ብቻ ሳይሆን እውቀትም ይፈልጋል:: ቀናነቱ እንደጎደሎት አስተያየትዎ ያመለክታል የእውቀትም ችግር ያለብዎት መሆኑን ግን የሚያቀርቡት መከራከሪያ ደካማነት ያመለክታል:: ኢትዮጵያውያን ትሁት ነን ከተነካን ግን ያውቁታል:: እርሶ የማንበብ እድሉ ካልነበረዎት ሌሎችን ይጠይቁ:: ዛሬም ያ አቅማችን አብሮን አለ እንዲያውም ዘምኖና ተሻሽሎ ጭምር:: ሁሌም ለሰላማዊ እና ለዲፕሎማሲያዊ አማራጭ ቅድሚያ የምንሰጥ ቢሆንም::

ለነገሩ አለቆችዎ ልዑል አፋቸውን አድጧቸው ነው ብለዋል:: የሆነ ሆኖ እሚከካ እሚቦካውን መጠርጠራችን ከዚያም አልፎ እንዲህ በአደባባይ ቀረርቶ ማረጋገጣችን ደስ አስኝቶናል:: የምር እንኳን አፉን አዳልጦት አጀንዳ ፈጥሮልናልና:: ሁሌም ስለአረብ ሲነሳ ስለ ኢትዮጵያ ሙስሊም የተነሳ የሚመስላቸው ደምና ሀገርን ከሃይማኖታዊ መመሳሰል ጋር የሚያስተሳስሩ ደካሞች አሉ:: አዎን ሙስሊሞች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ግን ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች ናቸው:: ሳዑዲ አረብያዊ ወይም ግብጻዊ አይደሉም:: ሃይማኖታቸውን በሀገራቸው ይኖሩታል ሀገራቸውን ለሃይማኖታቸውም ጭምር ሲሉ ይጠብቋታል::

ለአብነት የቅርቡን ጊዜ ሰላማዊውን የሙስሊሙን የውስጥ ጉዳይ እኚሁ የውጭ ኃይሎች ለአሸባሪነት አጀንዳቸው እንዴት ይፈትሉት እንደነበር እናስታውሳለን:: በአንድ በኩል ለሙስሊሙ ከራሱ በላይ ያውቅለት ይመስል መንግሥት በጉዳይህ እየገባ እየፈተፈተ ነው የሚል ፕሮፖጋንዳ ይነዛሉ:: በሌላ ገጽታው ደግሞ ከሀገር ወዳዱ ሙስሊም ጀርባ ከቅጥረኞቻቸው ጋር በመተባበር አሸባሪ ድርጊታቸውን ለመፈጸም ሳያሰልሱ ይሰራሉ:: ያም ሆኖ የከፋ ችግር ሳይፈጠር ሁኔታው መልክ እየያዘ ነው:: የሚቀሩትም ነገሮች በሂደት ኢትዮጵያዊው ሙስሊም በራሱ መንገድ የሚፈታቸው ይሆናሉ::

ሙስሊሙ ህብረተሰብ ሰላማዊ ጥያቄውን በራሱ መንገድ መፍታቱን አያቆምም:: ያ አንድ ነገር ሆኖ ሲያበቃ በሌላም በኩል ልዑል ሆይ እርስዎን እና ግብጻዊውን ሼክ የመሳሰሉ ሰባኪዎችንም ከመሰረታቸው መንጥሮ ከቅጥሩ ያወጣል:: ይቅርታ ያድርጉልን ጌታዬ ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ዜግነቱን ወዶ የሚኖር እንጂ የተጋተው አይደለም:: አገሩን በፖሊስ ያስጠብቃል የመስጊዱን ሰላም በፖሊስ ያስጠብቃል እንጂ ማንነቱ ተጠርጥሮ ፖሊስ በገባበትና በወጣበት የሚጠብቀውም አይደለም::

ልዑሉና መሰሎቻቸው ኢትዮጱያዊው ሙስሊም አባይን ብርና እውቀቱን ሰውቶ እየገነባው እንደሆነና በቀጣይም በማያሰልስ ትጋቱ እንደሚገነባው የገባቸው አልመሰለኝም:: ይሄ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ሀገራዊ ፍቅሩ ከደሙ ጋር የተሰናሰለ መሆኑን አያውቁትም:: ሃይማኖታዊ ተመሳስሎው እና አምልኮቱን በየዋህነት ለአሸባሪና አውዳሚ እቅዳቸው የሚያውለው ይመስላቸዋል::

አይ አለማወቅ ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን እንደማይቀይር ቢያውቁ በበጃቸው ነበር!!! እነዚህ ተከታታይ ድርጊቶች በእምነቱ ቅጥር ሥር ሊሰሩ መሞከራቸውን የተረዳው ሙስሊም ኢትዮጵያዊ ብሄራዊ ጥቅሙን አሳልፎ አይሰጥም::
አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment