Friday, March 22, 2013

ዋልያዎቹ እሁድ ቦትስዋናን ያስተናግዳሉ

(Mar 22, 2013, (አዲሰ አበባ))--ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ የሠሩትን ታሪክ በዓለም ዋንጫ ለመድገም ልምምዳቸውን በማጠናቀቅ ላይ ናቸው፤ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ምድባቸውን እየመሩ የሚገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ዋልያዎቹ በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ ስቴድየም አስር ሰዓት ላይ ቦትስዋናን ያስተናግዳሉ።የቦትስዋና ብሔራዊ ቡድንም ጨዋታውን ለማካሄድ ትናንት ምሽት አዲስ አበባ ገብቷል።
 
ዋልያዎቹ እሁድ ቦትስዋናን ያስተናግዳሉ
ዋልያዎቹ ለብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከደቡብ አፍሪካ፤መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክና ቦትሱዋና ጋር ተደልድለዋል።በእዚህም መሠረት የመጀመሪያውን የማጣሪያ ጨዋታ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ከሜዳቸው ውጪ አካሂደው አንድ ለአንድ በሆነ ውጤት ተለያይተው ነጥብ መጋራት ችለዋል።

ዋልያዎቹ ሁለተኛውን የማጣሪያ ጨዋታ በሜዳቸው ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር አካሂደው በሳላዲን ሰኢድ ሁለት ግቦች ማሸነፋቸው ይታወሳል።በእዚህም መሠረት ዋልያዎቹ ምድባቸውን በአራት ነጥብ በመምራት ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ የምትሳተፍበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ የሚገኙት ዋልያዎቹ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ታሪክ ምድባቸውን ይህን ያህል ጊዜ ሲመሩ የመጀመሪያቸው ነው ማለት ይቻላል።

ዋልያዎቹ ከእሁዱ የቦትስዋናው የማጣሪያ ጨዋታ በኋላ ደቡብ አፍሪካን በሜዳቸው ያስተናግዳሉ።በቀጣይም ከመካከለኛው አፍሪካና ቦትስዋና ጋር ከሜዳቸው ውጪ የደርሶ መልስ ጨዋታ ያካሂዳሉ። አሁን ባለው ሁኔታ ከምድባቸው ለማለፍ ትልቅ ተስፋ ያላቸው ዋልያዎቹ በቀጣይ ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ከቻሉ ወይንም ስድስት ነጥብ ማግኘት ከቻሉ ከምድባቸው በአስር ነጥብ አንደኛ ሆነው የማለፍ ተስፋ አላቸው።
 
በእሁዱ የማጣሪያ ጨዋታ ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ያሳዩትን ድንቅ ብቃት ከደገሙና ስህተቶቻቸውን አርመው ወደ ሜዳ ከገቡ ጨዋታውን በድል የማይወጡበት ምክንያት አይኖርም። በአፍሪካ ዋንጫው ብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ከነበሩ ተጫዋቾች የኢትዮጵያ ቡናውን ዳዊት እስጢፋኖስንና የቅዱስ ጊዮርጊሱን ኡመድ ኡክሪ እንዲሁም ግብ ጠባቂውን ዘሪሁን ታደለን የቀነሱት አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ዋልያዎቹን በዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማብቃት ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ላይ ናቸው።

የቦትስዋ ብሔራዊ ቡድን አብዛኞቹ ተጫዋቾች በሃገር ውስጥ ሊጎች፤ አምስት ያህሉ ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ሊጎች የሚጫወቱ ናቸው።በዋልያዎቹ በኩል ከአፍሪካ ዋንጫው በኋላ ከግብፁ ዋዲ ዳግላ ክለብ ወደ ቤልጂየሙ ሊርስ ክለብ ካመራው ሳላዲን ሰኢድ ውጪ ሁሉም በሃገራችን ሊጎች የሚጫወቱ ናቸው።

ሳላዲን ዋልያዎቹን ተቀላቅሎ ከትናንት ወዲያ ልምምዱን ጀምሯል።በማጣሪያ ጨዋታውም ለቦትስዋና አሳሳቢ ተጫዋች ሆኗል።ቦትስዋና ምድቡን በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛ ነው ዋልያዎቹን የምትገጥመው። ቦትስዋና በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ከደቡብ አፍሪካ ጋር ባካሄደችው ጨዋታ አቻ በሆነ ውጤት ተለያይታ አንድ ነጥብ ብታገኝም በመካከለኛው አፍሪካ በመሸነፏ ከምድቧ ተፎካካሪ የምትሆንበትን ሦስት ነጥብ አጥታለች።
 
ዋልያዎቹ ከደቡብ አፍሪካና መካከለኛው አፍሪካ ጋር ባደረጉት ጨዋታ የተሻሉ ሆነው ነጥብ መሰብሰባቸው ከቦትስዋና ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ እንዲቀላቸው ያደርጋል።ቦትስዋና የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ካለመሆኗም በተጨማሪ በዋልያዎቹ ምድብ ከተደለደሉት አገሮች በጥንካሬ ደከም ያሉ ናቸው ማለት ይቻላል።ዋልያዎቹ ከምድባቸው ጠንካራ ከሚባሉት አገሮች ጋር ነጥብ ከመጋራታቸውና ከማሸነፋቸው አኳያ ቦትስዋናን በቀላሉ የማሸነፍ አቅም እንደሚኖራቸው ይታመናል።

ቦትስዋና በበኩሏ ወደ ብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ለማምራት የሚያስችላትን ነጥብ ለማግኘት ከዋልያዎቹ ጋር ከሚኖራት የማጣሪያ ጨዋታ በተጨማሪ ቀሪዎቹን የማጣሪያ ጨዋታዎች አሸንፋ ነጥብ መሰብሰብ ይጠበቅባታል።በእዚህም ምክንያት ቦትስዋና የዓለም ዋንጫ ተስፋዋን ለማለምለም በቀሪዎቹ የማጣሪያ ጨዋታ ጠንካራ አቋም ይዛ እንደምትቀርብ ይጠበቃል።

ደቡብ አፍሪካ ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በዋልያዎቹ ምድብ በእዚህ ሳምንት መጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታቸውን የሚያካሂዱ አገሮች ናቸው።የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጇ ደቡብ አፍሪካ በዋልያዎቹና በቦትስዋና ነጥብ መጣሏን ተከትሎ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች።

ባፋናባፋና በመባል የሚታወቁት ደቡብ አፍሪካዎች በአፍሪካ ዋንጫው ሩብ ፍፃሜ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችው ኬፕቨርዴ ተሸንፈው ከውድድር ከወጡ በኋላ ትኩረታቸውን ሙሉ ለሙሉ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ላይ አድርገዋል።

አሠልጣኝ ጎርደን ኢግሰንድም በዓለም ዋንጫው ማጣሪያ ሁለት ጨዋታዎችን አድርገው ሁለቱንም በአቻ ውጤት የተለያዩትን ባፋናባፋናዎች ከአጣብቂኝ ለማውጣት ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል። አሠልጣኙ ባፋናባፋናዎቹ በሁለት ጨዋታ በሰበሰቡት ሁለት ነጥብ ከምድባቸው መብለጥ የቻሉት ቦትስዋናን ብቻ ነው።አሠልጣኝ ጎርደን ኢግሰንድ ባፋናባፋናዎቹ ከምድባቸው በሦስተኛ ደረጃ ላይ መገኘት ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ከሜዳቸው ውጪ ዋልያዎቹን ማሸነፍ አለማሸነፋቸው ያሳስባቸዋል።
 
አሠልጣኙ አጣብቂኝ ውስጥ እንዳሉ ቢያምኑም ቀሪዎቹን የማጣሪያ ጨዋታዎች በጠቅላላ አሸንፈው ወደ ብራዚል ለማምራት ዕድሉ እንዳላቸው አምነዋል።ይሁን እንጂ ባፋናባፋናዎቹ የቀሩትን ማጣሪያዎች በጠቅላላ ያሸንፋሉ ለማለት አስቸጋሪ እንደሆነ የስፖርቱ ተንታኞች ያምናሉ።

ከደቡብ አፍሪካ በተሻለ በዓለም ዋንጫው ተስፋ ያላት መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በዋልያዎቹ አዲስ አበባ ላይ ሁለት ለዜሮ ብትሸነፍም ጠንካራ ቡድን እንዳላት ታይቷል።ይህም ለደቡብ አፍሪካ የሚያሰጋት እንደሚሆን ታምኗል። መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በምድባቸው በሦስት ነጥብ ዋልያዎቹን እንደመከተላቸው መጠን በዓለም ዋንጫው ማጣሪያ ተስፋ አላቸው።ከዋልያዎቹ ጋር የሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ በሜዳቸው መሆኑም በተወሰነ መልኩ ተስፋቸውን ያለመልመዋል። 
አዲስ ዘመን ጋዜጣ
 Home

No comments:

Post a Comment