Wednesday, February 20, 2013

ኮሌስትሮል (Cholesterol ) ሌላው የጤናችን ስጋት

(Feb 20, 2013, እፀገነት አክሊሉ)--አሁን አሁን የዓለምን በስልጣኔ መርቀቅ ተከትሎ የሰው ልጆች አኗኗር እጅግ ዘመናዊነትን እየተላበሰ መጥቷል። የቴክኖሎጂ ውጤቶችም ኑሮን ቀላልና ቀልጣፋ እያደረጉ ነው። ታዲያ አዳዲሶቹ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ስራንና ኑሮን ቀልጣፋ የማድረጋቸውንና የሰውን ልጅ የመጥቀማቸውን ያህል ለስንፍና ዳርገውታል። 

በዚህም ሳቢያ ለተለያዩ በሽታዎች እየተጋለጠ ነው የሚሉ መረጃዎች በየጊዜው ይወጣሉ። እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ብዙ ሩጫ ያለበትን የኑሮ አካሄድ ቢቀይሩም ሰዎች ከመቀመጫቸው ሳይነሱ እንዲውሉ ምግቦቻቸውም የፋብሪካ ውጤቶች እንዲሆኑ በማድረግ የተለያዩ በሽታዎችን እያስከተሉ ይገኛሉ። በሽታዎቹ ደግሞ ግማሾቹ ምንም ምልክት ሳያሳዩ የሚጎዱ ሲሆኑ አንዳንዶቹም በመጨረሻው ሰዓት ላይ ምልክታቸውን የሚያሳዩና የህክምናው እርዳታም ሳይገኝ ወደ ሞት የሚያደርሱ እየሆኑ ነው።
 
ከእነዚህ ድምጽ አልባ ገዳይ በሽታዎች መካከል ደግሞ በተለይም በአሁኑ ወቅት እጅግ እየተስተዋለና ብዙዎችንም ለከፋ ጉዳት እየዳረገ ያለ የበሽታ ዓይነት «ኮሌስትሮል» በመባል የሚጠራው የበሽታ ዓይነት ነው። 

ጎግል የተባለው ድረ ገጽ «ኮሌስትሮል» የሚለውን ቃል «በሰውነት ውስጥ የሚከማች የስብ መጠን ሲሆን መንስዔዎቹም በዕለት ተዕለት ኑሯችን የምንመገባቸው ምግቦች ናቸው።ምንም እንኳን ያልተጋነነ የቅባት መጠን ለሰውነት አስፈላጊ ቢሆንም በሰውነት ውስጥ ባላስፈላጊ መልኩ የሚጠራቀም የስብ መጠን ግን ኮሌስትሮልን በመፍጠር ለልብ ህመምና ስትሮክ የሚዳርግ ይሆናል፤ በተጨማሪም የደም መዘዋወሪያ ቱቦን ወይም አርተሪ በመባል የሚታወቀውን የአካል ክፍል በመዝጋት ለከፋ አደጋ የሚዳርግ ችግር ነው» በማለት ይፈታዋል።

መረጃው በመቀጠልም ኮሌስትሮልን ' ሀይ ዴንሲቲ ሊፖፕሮቲን (high-density lipoprotein): HDL)፣ ሎው ዴንሲቲ ሊፖፕሮቲን (low-density lipoprotein: LDL እና ቬሪ ሎው ዴንሲቲ ሊፖፕሮቲን (very-low-density lipoprotein: VLDL) በማለት በሶሰት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፍለዋል፤ ሀይ ዴንሲቲ ሊፖፕሮቲን ማለት ጥሩ የሚባለው የኮሌስትሮል መጠን ሲሆን የደም መዘዋወሪያው ቱቦ ወይም አርተሪ ያለምንም እንከን ስራውን ያከናውናል ማለት ነው።

ሎው ዴንሲቲ ሊፖፕሮቲን ደግሞ በሰውነት ውስጥ ያለው የኮሌስትሮል መጠን ከመጠን በላይ መሆኑንና የደም መዘዋወሪያ ቱቦዎችም ስራቸው እየተስተጓጎለ መሆኑን የሚያመለክት ነው። ይህ ደግም የልብ ምት ችግርን ብሎም ስትሮክን በማስከተል ይታወቃል። ቬሪ ሎው ዴንሲቲ ሊፖፕሮቲን ይህ የሚስተዋለው ደግሞ በጉበት ላይ ሲሆን ችግሩም ቶሎ ካልተደረሰበት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከፍ ማለቱ እንደማይቀር የሚያመለክት ነው።
 
በተለይም የእኛ ማህበረሰብ አብዝቶ ቅባታማና ጮማ የሆኑ ምግቦችን የሚመገብ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ለዚህ መሰሉ የኮሌስትሮል ችግር የተጋለጠ ነው። ሆኖም ብዙዎቻችን በየጊዜው የህክምና ምርመራን የማድረግ ልምዳችን አናሳ በመሆኑ ችግሩ ከፍተኛው ደረጃ ላይ ሲደርስ ብቻ ነው የምናውቀው። 

ኮሌስትሮል ብዙ ጊዜ ምንም ዓይነት ምልክቶችን ሳያሳዩ በድንገት ከሚከሰቱ ህመሞች መካከል የሚመደብ ነው።በመሆኑም አንድ ሰው የኮሌስትሮል መጠኑ ከፍተኛ፣ ዝቅተኛ አልያም አናሳ መሆኑን የሚያውቀው የህክምና ምርመራ በተለይም የኮሌስትሮል ምርመራን ማድረግ ከቻለ ብቻ ነው። የሚለው መረጃው በተለይም ዕድሜ ከ 20 ዓመት በላይ ሲሆን በየአምስት ዓመቱ መደበኛ የኮሌስትሮል ምርመራን በማድረግ በሽታውን መከላከል እንደሚቻል ይጠቁማል።

ከዚህም በተጨማሪ በሽታው በዘር የሚተላለፍ በመሆኑ በቤተሰብ ውስጥ የኮሌስትሮል ችግር ያለበት እንዲሁም እንደ ስኳርና የልብ ህመም የመሳሰሉ ችግሮች የሚስተዋሉበት ቤተሰብ ውስጥ ያለ። ሁሉ በየጊዜው ምርመራን በማድረግ ራሱን ማወቅ እንዳለበትም መረጃው ይመክራል።

ሆኖም አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ሳይኖሩ በጤናም ላይ ምንም ዓይነት መስተጓጎል ሳይታይ በድንገት በሽታው የሚከሰትበት አጋጣሚም አለና የተለየ የህመም ስሜት ሲሰማ በቶሎ የኮሌስትሮል ምርመራም ይደረግልኝ ማለት ከከፍተኛው ችግር ያድናል ይላል የጎግል መረጃ። ሰዎች የአመጋገብ ልምዳቸው ለኮሊስትሮል ችግር እንደሚያጋልጣቸው መረዳት አለባቸው የሚለው መረጃው አንድ ሰው ጮማ ስጋን ካበዛ ብሎም ጣፋጭ ምግቦችን አብዝቶ የሚመገብ ከሆነ የችግሩ ሰለባ መሆኑ አይቀርምና አመጋገቡን ማስተካከል አለበት በማለትም ያስጠነቅቃል።
 
በሽታው ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የሚከሰት ቢሆንም የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ያለማድረግ፣የአመጋገብ ልማድን ያለመቀ የር፣ሲጋራ ማጨስ፣የእድሜ መግፋትና እንደ ስኳር ካሉ ተዛማጅ የበሽታ ዓይነቶች ጋር አብሮ መኖር ሌላው በሽታውን ሊያመጡ ይችላሉ ተብለው የተቀመጡ ምክንያቶች ናቸው።

ብሔራዊ የኮሌስትሮል ትምህርት ፕሮግራም ባወጣው መረጃ መሰረትም በሽታው ምንም ምልክት ሳያሳይ ከሰዎች ጋር ቢኖርም ሲብስ ግን አንዳንድ መገለጫዎችን ማሳየቱ አይቀርም። ከእነዚህ መካከል ደግሞ የዓይን ዕይታ መቀነስ፣ መፍዘዝ፣ ለመናገር መቸገር፣ የድካም ስሜት መሰማት ሲሆኑ ህመሙ ብዙ ጊዜ ልብን የሚያጠቃ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ደግሞ የደረት ህመም ( የውጋት ዓይነት ስሜት)፣ ለመተንፈስ መቸገር፣ የአየር ማጠር፣ ፈጣን ወይም ያልተለመደ የልብ ምት፣ የመጨነቅ ስሜት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ በውጫዊ አካል ላይ ማለትም በእጅ፣ በጀርባ በሆድና አካባቢው ላይ ምቾት ማጣት፣ የሰውነት መቀዝቀዝ ምልክቶቹ ናቸው።

ከእነዚህ ምልክቶች መካከል ሁሉም ወይም ጥቂቶቹ የታዩበት ሰውም ቶሎ የህክምና እርዳታን ማግኘት ያለበት ሲሆን ምልክቶቹን እያዩ ዝም ማለት ግን ለከፋ ችግር ብሎም ለሞት የመዳረግ እድሉ ከፍተኛ ነው። ይህ ችግር እንዳይከሰት አመጋገብን ማስተካከል በየዕለቱ ከ30 ደቂቃ ያላነሰና ፈጠን ያለ የእግር ጉዞ ማድረግ ደግሞ ከህክምናው ባሻገር ለታማሚው የሚመከር ምክሮች ሲሆን በተለይም ህመምተኛው አመጋገቡ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ይነገራል።
 
በመሆኑም ቅባት ነክ ከሆኑ የምግብ አይነቶች መቆጠብ ፣ጣፋጭነት ያላቸውን የምግብ ዓይነቶች ማስወገድ፣ የተፈጨ አጃ፣ቀይ ስጋ፣አሳ፣ፖም እና ሌሎች አትክልትና ፍራፍሬዎችን በመመገብ ችግሩ ደግሞ እንዳይከሰት ማድረግ እንደሚቻልም መረጃው ያመለክታል። ታዲያ ከዚህ ድምጽ አልባ ገዳይ በሽታ ለመዳን ሁላችንም ምክሩን ማለቱ ሳይበጀን አይቀርም። ከስኳር፣ ከካንሰርና ከሌሎች ምልክታቸውን በቶሎ ከማያሳዩ የህመም ዓይነቶች ጎን ለጎን ለከፋ ጉዳት እየዳረገን ያለውን ኮሌስትሮልን መከላከል በእጃችን ያለ መላ ነው። 
 
ጠዋት ከቤታችን ቀደም ብለን በመውጣት አልያም ማታ ወደ ቤታችን ስንገባ መጠነኛ የእግር ጉዞ ብናደርግ ጨውን፣ ስኳርንና ቅባት የበዛባቸውን ምግቦቻችን ብንቀንስ በሽታውን ከራሳችን የማናርቅበት ምክንያት የለምና « ጎበዝ ሳይቃጠል ...»እንዲሉ ብናስብበትስ?
አዲስ ዘመን

No comments:

Post a Comment