Friday, February 01, 2013

መጨካከኑ ለምን ይሆን? (ትዝብት) በ እንግዳወርቅ ባዬ

(Feb 01, 2013, እንግዳወርቅ ባዬ)--ከአንድ ወዳጄ ጋር ምሳ ለመብላትና እግረ መንገዳች ንንም የሆድ የሆዳችንን እንድናወራ ተቀጣጥረን ስለነበር የቀጠሮው ሰዓት ከመድረሱ በፊት ከመሥሪያ ቤቴ ወጥቼ ወደ ቀጠሮው ቦታ አመራሁ። 

እኩለ ቀን በመሆኑ የፀሐይዋ ሙቀት በርትቷል። ከጓደኞዬ ጋር ምሳ ለመብላት ከምንገናኝበት ቦታ ለመድረስ 15 ደቂቃ የሚፈጅ ቢሆኑም እየሞቀኝም ቢሆን በእግሬ መሄድን መረጥኩ። በተለምዶ ዘሪሁን ሕንፃ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ ተነስቼ ዑራኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ እንደደረስኩ ግን ዓይኖቼ አንድ አሳዛኝና አሰቃቂ ትዕይንት ላይ አረፉ።

ዑራኤል ድልድይ አጠገብ አንዲት ተሽከርካሪ (ቪትዝ) በዕድሜያቸው ገፋ ያሉ አንድ ቄስን ገጭታ መሐል አስፓልት ላይ ጣለቻቸው። የመኪናዋ አሽከርካሪ የሰውየውን መውደቅና ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለማሳየታቸውን ሲረዳ ተጎጂውን ከወደቁበት አንስቶ ከመርዳት ይልቅ መሬት እንደተጋደሙ ጥሏቸው ማምለጥን መረጠ። ወደ ዑራኤል የትራፊክ ማስተላለፊያ መብራት አቅጣጫ በፍጥነት እየበረረ ለመጓዝ ሞከረ። በወቅቱ የነበረው የትራፊክ መጨናነቅ ግን በፈለገው ፍጥነት ሊያስኬደው ስለማይችል መኪናውን አዙሮ ሽቅብ ወደ ዘሪሁን ሕንፃ አቅጣጫ አመራ። 

በአደጋው ሥፍራ ድንገት የተሰበሰበው ሕዝብ በተፈጠረው ሁኔታ እና በተለይ የመኪናው አሽከርካሪ ለማምለጥ ያደረገው ሙከራ በእጅጉ በመበሳጨቱና በማዘኑ የቻለውን ያህል መኪናውን ለማስቆም ጥረት አደረገ። እኔም በደረሰው አደጋ በጣም ተደናግጬ ስለነበረ የሚሆነውን ዝም ብዬ መከታተል ጀመርኩ። አንድ አንዱ «ያዘው! ያዘው! ቁምእያለ ወደመኪናው አቅጣጫ ይሮጣል። ሌላው ደግሞ «በለው በለው» በማለት ከድንጋይ ጀምሮ ያገኘውን ነገር እያነሳ ወደመኪናው በመወርወር የመኪናውን ፍጥነት ለመግታት ጥረት ያደርጋል። 

ከየአቅጣጫው ለሚወረወረው የድንጋይ እሩምታ ያልተበገረው አሽከርካሪ ግን ከሚወረወርበት ለማምለጥ መኪናውን አንዴ ወደቀኝ ሌላ ጊዜ ወደግራ ዚግዛግ እየሠራ ተጨማሪ አደጋ ሊያስከትል በሚችል መልኩ ፍጥነቱን ጨምሮ ለጊዜው አመለጠ። በሄደበት አቅጣጫ የተወሰኑ ሰዎች ተከትለውት ቢሮጡም መኪናውን በእግር አሳድዶ መያዝ ግን እማይሆን ነገር በመሆኑ ከንቱ ልፋት ሆነ። 

ይሁን እንጂ ተገጭተው አስፓልት ላይ ጥቅልል ብለው የተኙት አባት ቀስ በቀስ መንቀሳቀስ ጀመሩ። በአካባቢው የተሰበሰበው ሰው የሰውየውን በሕይወት መትረፍ እንዳየ ትኩረቱን ወዲያው ወደ እርሳቸው አደረገ። በፍጥነት ወደ ህክምና አገልግሎት እንዲሄዱ ለማድረግ በአካባቢው የሚተላለፉ መኪኖችን አስቁሞ ለመለመን ጥረት ቢያደርግም ማንም ፈቃደኛ አልሆነም። 

ድርጊቱ በተፈጸመ ሃያ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንድ የትራፊክ ፖሊስ ቦታው ላይ ደረሰ። ተገጭተው የወደቁ ቄስ ከተመለከተ በኋላ ሰውየው ወደ ጤና ተቋም እንዲሄዱ እርሱም በአካባቢው የሚተላለፉትን መኪኖች መጠየቅ ጀመረ። አንድ ሦስት አሽከርካሪዎች አላየንም በሚል ሁኔታ ለእርሱም ምላሽ ሳይሰጡት ሄዱ። ሁኔታው ሁላችንንም በእጅጉ አሳዘነን፡፡ አበሳጨንም። ሰው እርስ በእርሱ እንዲህ ተጨካክኗል ማለት ነው? በማለት ለራሴ ውስጤን ጠየኩት። 

ድንገት ተሳፋሪ የሌላት አንዲት ነጭ ሚኒባስ መኪና ዝግ እያለች ስትመጣ የትራፊክ ፖሊሱ በእጅ ምልክት አሳይቶ መኪናዋን አስቆመ። መኪናዋን ለሚያሽከረክሩት ሰው ስለደረሰው አደጋ ካስረዳቸው በኋላ ተጐጂውን ሰው ወደ ጤና ተቋም በመውሰድ እንዲተባበሩ ጠየቃቸው። በአካባቢ ያለው ሰውም መኪናዋን በመክበብ ተማጸናቸው። እርሳቸው ግን «እኔ እቸኩላለሁ አልወስዳቸውምሲሉ ቆጣ ባለ ድምፅ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናገሩ። በሁኔታው ክፉኛ የተናደደው የትራፊክ ፖሊስ ጠንከር ባለ አነጋገር «ሰውየውን በመውሰድ መተባበር አለብዎትሲል ገለጸላቸው። ይሄኔ ነበር ብዙዎቻችንን በሚያበሳጭ መልኩ አሽከርካሪው ምላሻቸውን የሰጡት። 

ሰብዓዊነትን ረስተው «የትኛው ሕግ ነው የሚያስገ ድደኝ። በእዚህ የሚቀጣኝን አያለሁ። ወንድ የሆነ ይቀጣኛል። አንተም መቅጣት አይደለም መግደል ትችላለህበማለት እጃቸውን እያወራጩ ለትራፊኩ ምላሽ ከሰጡ በኋላ መኪናቸውን ከበን የቆምነውን ሰዎች በመኪናቸው እየገፈታተሩ መኪናቸውን በማስነሳት ጥለውን ሄዱ። አብዛኞቻችን በድርጊታቸው ረገምናቸው።

መቼም በእዚች ዓለም ክፉ የሆነ እንዳለ ሁሉ ቅን የሆኑም አይጠፋምና አንድ ተባባሪ ሰው በእዚያው ቅጽበት ተገኘ። 'ጠብታ' የተባለ አምቡላንስ መኪና የሚያሽከረክር ሰው ተጎጂውን ሕክምና ወደሚያገኙበት የጤና ተቋም ለማድረስ ፈቃደኛ ሆኖ ጉዳት ደርሶባቸው የወደቁትን አባት ወደ ጤና ተቋም ወሰዳቸው። እርሳቸው ቢሄዱም በውስጤ ግን አንድ ነገር ቀረ።

እንዲህ መጨካከኑ ለምን ይሆን? የሚለው ውስጤን ረበሸኝ። ሲሆን ሲሆን ጉዳት ያደረሰው አሽከርካሪ ራሱን በማረጋጋት የተጐዱትን ሰው በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋም መውሰድ የአባት ነበር። ይህን አለማድረጉ ሳያንስ ይባስ ብሎ ለማምለጥ መሞከሩ ከጥፋትም በላይ ጥፋት ነው። 

ምናልባት የተገጩት ሰው በአፋጣኝ ወደህክምና ተቋም በመወሰዳቸው ሕይወታቸው ሊተርፍ ይችል ይሆናል ብሎ ማሰብ ጥሩ ነው። ባይተርፉ እንኳ በሰብዓዊነት ተገቢውን እገዛ ማድረግ የኋላ ኋላ ፍርድን ለማቃለልም ቢሆን ጠቀሜታ አለው። ከሁሉም በላይ ለጊዜው መሰወር ይቻል ይሆናል እንጂ እስከመጨረሻው ማምለጥ እንደማይቻል ጠንቅቆ ማወቅ ይገባል።

በወቅቱ በአካባቢው የነበረው ሰው ገጪው እንዳያመልጥ ያሳየው ተባባሪነት መልካም ቢሆንም መኪናውን ለማስቆም የወሰደው እርምጃ ግን ተገቢ ነው የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም ሊያመልጥ የነበረውን መኪና ለማስቆም ከየአቅጣጫው የተወረወሩ ድንጋዮች በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ሌሎች መኪኖች ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ይቻላሉ። ይህ አለመታሰቡ በመጠኑም ቢሆን ቅር ያሰኛል። 

ከእዚህ ውጪ ነጋ ጠባ በተለያዩ ሬዲዮ ጣቢያዎች በትራፊክ አደጋ ለተጐዳ ሰው ድጋፍ ማድረግ የሁሉም እንደሆነ የሚነገረውን በተግባር ማሳየት አለብን የሚል እምነት አለኝ። ጥሩ መሥራት መቼም ይሁን የትም ያስከብራል እንጂ ጉዳት የለውም። 

ሁልጊዜ የትራፊክ ሕግና ደንብ ጠብቆ በማሽከርከር የትራፊክ አደጋን መከላከልና መቀነስ ተገቢ ነው። ከአቅም በላይ ሆኖ አደጋው ቢከሰት ግን የሕይወት ማዳን ሥራ የሁላችንም መሆን አለበት። የትራፊክ አደጋ በሁላችንም ላይ ድንገት ሊከሰት እንደሚችል ለአፍታ ማስታወስም እንዲሁ። 

ሰብዓዊነትም ያስፈልጋል። በተለይ አሽከርካሪዎች ጉዳተኛውን በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም መውሰድ በሕይወት አድን ሥራው ላይ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑና በማወቅ ተባባሪ መሆን ይኖርብናል። ከእዚህ ውጪ እየተያዩ መጨካከኑ ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም።

1 comment:

Post a Comment