(Feb 12, 2013, አዲስ አበባ)--በኢትዮጵያ በሁለት አቅጣጫ በአምስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባው ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ባቡር መስመር ግንባታ ዋና ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ። ፕሮጀክቱ ለ131 ሺ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እንደሚያስገኝ ተገልጿል ፡፡
የኢትዮጵያን ህዳሴ በማጠናከር መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍና ሀገሪቱን እርስ በርስና ከአፍሪካ ሀገሮች ጋር ያለውን እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከአምስት ሺ ኪሎ ሜትር የሚበልጥ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ባቡር መስመር ዝርጋታ በሁለት ምዕራፍ እየተካሄደ ነው ፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ምክትል
ዋና ሥራ አስኪያጅና የመሠረተ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ኢንጂነር ደቦ ቱንካ እንደገለጹት፤ በሁለት አቅጣጫ በመከናወን ላይ
ያለው የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሲሆን፤ ይህም ከጂቡቲ ጋር የሚያገናኝ የኤሌክትሪክ ባቡር መስመር ነው።
እንዲሁም 739 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ከአዲስ አበባ ሰበታ - ሚኤሶና ከሚኤሶ - ድሬዳዋ ደወሌ ከሊሌ ኢትዮጵያ ድንበር በሁለት አቅጣጫ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል ፡፡ ከሊሌ - ጂቡቲ 82 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መስመርም በሁለቱ ሀገሮች የጋራ ስምምነት እየተገነባ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡
በሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ባቡሩ በሰዓት ከ120 ኪሎ ሜትር በላይ የሚፈጥንና በአንድ ጊዜ እስከ 30 ፉርጎዎች የሚጎትት መሆኑን ገልፀው፤ ይህም የሀገሪቱን ማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ የወጪና የገቢ ንግድ እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያስችል አስታውቀዋል ፡፡
ባቡሩ የሚያልፍባቸው አካባቢዎችን ዕድገት የሚረጋገጥ ከመሆኑም ባሻገር በተለይ ድሬዳዋ የምሥራቁ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከልነቷን ስኬታማ እንደሚያደርገው ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያንና የጂቡቲን ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ እንዲሁም የእርስ በርስ ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ለማጎልበት እንደሚያስችል ኢንጂነር ደቦ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሚኤሶ - ድሬዳዋ - ደወሌ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘከሪያ ጀማል በበኩላቸው፤ የ340 ኪሎ
ሜትር ፕሮጀክት በቻይና የሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን አማካይነት እንደሚከናወን ጠቁመው፤ ካለፈው
ዓመት ጀምሮ ሲከናወን የነበረው የቦታ መረጣ፣ ንድፍ ማጣጣምና የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች የማሟላት ፣ የካምፕ
ግንባታ ፣ የሐዲድ ንጣፍ ማምረቻ ሥራ መጠናቀቁን አስታውቀዋል ፡፡
በየወረዳው ኮሚቴ ተቋቁሞ ለፕሮጀክቱ ተብሎ ለሚነሱ ሰዎች ቦታ የማመቻቸትና ለአሸዋና ጠጠር እንዲሁም ለአፈር ማምረቻ ለተመረጡ አካባቢዎች የካሳ ክፍያ እየተፈፀመ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡ በመሆኑም 40 ከመቶ የሚሆን የአፈር ቁፋሮና ድልደላ ሥራ መጠናቀቁን ገልጸው፤ ሐረዋዋ ፣ መልካ ጀብዱና ላሳራት በተባሉ አካባቢዎች 20 ኪሎ ሜትር የኮንስትራክሽን ሥራ መከናወኑን ጠቁመው፤ የሃዲድ ማንጠፍ ሥራ በቀጣዮቹ ሳምንታት በተጠናከረ መንገድ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የኮርፖሬሽኑ የኦፕሬሽን መምሪያ የአቅም ግንባታ አስተባባሪ አቶ ኢሊያስ ከበደ በበኩላቸው እንደ ተናገሩት፤ በሁለቱ አቅጣጫ እየተከናወነ የሚገኘው ፕሮጀክትና የአዲስ አበባ ከተማ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ለ131 ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል። በሦስት ምዕራፍ ተከፍሎ የተጀመረው ፕሮጀክት 40 ከመቶ የሆነው የአፈር ቁፋሮና ድልደላ ሥራ መጠናቀቁንና የሃዲድ ማንጠፍና የኤሌክትሪፍኬሽን እንዲሁም የኮሙኒኬሽንና የሲግናል ሥራዎች ቀጣይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ባቡሩ በሚያቋርጣቸው ቀበሌዎችና ወረዳዎች
የሚገኙ ነዋሪዎችና ከቴክኒክ ሙያ ኮሌጆች በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተመረቁ ወጣቶች እንዲሁም በጥቃቅንና አነስተኛ
ነዋሪዎችና ሥራ ለይ የተሠማሩ ማህበራት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከመሆናቸው በተጨማሪ የሥራ ላይ ሥልጠና እንደሚያገኙ
አስረድተዋል ፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ
1 comment:
betam yasedsetal bertu
Post a Comment