Friday, February 15, 2013

ምላጭ የማይሰሩ ምላጮች (በመኩሪያ መካሻ)

(Feb 15, 2013, በመኩሪያ መካሻ, አዲስ አበባ)--በምርጫ ሰሞን ተመራጮች ደግ ይሆናሉ። መራጮች ተስፋ ያደርጋሉ። እንደ ተመራጮች ግን በተስፋ እሳት የሚቃጠል የለም። ያን ሰሞን ተመራጮች ትንፋሽ ያጥራቸዋል። ተመራጭ መሆን ደስ ይላል። ክራቫት አስሮ መደስኮር ኩራት ነው። በሕዝብ ስም መማል ያጓጓል። አስርቱ ቃላት ውስጥ ስላልተመዘገበ በሰማይም ቤት አያስጠይቅም። ተመራጭነት በራሱ ልዩ ረሃብ ነው። ይፋጃል። ያቁነጠንጣል። 

ወስፋት እያገላበጠ ሆድ ያጮሃል። አምሮት የሚበርደው ምሱን ሲያገኝ ነውና ምርጫ ይኑር! ምርጫ ካለ ወፍራም ደመወዝ አለ። ንፁህ አፓርታማ አለ ፣ እንደ ውሃ ግን በውሃ የማይፈስ መኪናም አለ። ሁሉም ይኖራል።

በተለይ በሕዝብ መመረጥ ጥቅም ነው። ተመራጭነት የሞቀ ወንበር ነው – ይሽከረከራል። ተሽከርክሮ ያሽከረክራል። ወንበር ብቻ ሳይሆን ስምንም ለመለወጥ ይጠቅማል። ከምርጫ በኋላ እድሜና እውቀት አይታሰቡም። «ክቡር የፓርላማ አባል» የሚለው ይሰፍናል። «ክቡር እከሌ» እንዳሉት እየተባለ በየጋዜጣው ይጻፋል። ተመራጩ ቢሞት እንኳ «ክቡር የፓርላማ አባል ፣ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ በትጋት ለሕዝብ ያገለገሉት በተወለዱ በሰላሳ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ» ተብሎ ይነገራል። መራጩ በተራው «የተከበሩ የፓርላማ አባል» እያለ ማመልከቻውን ይጽፋል። አንዳንድ የፓርላማ ስልጣኖች ረዘም ይላሉ - «እከሌ -- የፓርላማ አባልና የውጭ ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር» ይሆናል። ስለዚህ ሰው ከአያቱ በላይ በማይጠራበት አገር ተመራጭነት ያስደስታል።  

«የተመረጠ በለጠ ነው» ወዳጄ! ሕግ እንኳ አይደፍረውም። ወንጀል ሰርቶ እንኳ ቢገኝ ቤቱ በፖሊስ አይበረበርም። ቆመጥ አያርፍበትም። «ያዘውየሚል ትእዛዝ አይቆረጥበትም። እንደተመራጭ ልዩ ነገር የት ይገኛል? «የተመረጠ ይግደለኝና» ሕዝብ ከፈቀደ ፣ ሕዝብ ከጠቆመ ኮሌጅ መበጠስ ምን ፈይዶ የተመረጠ ይግደለኝ። 

በምርጫ ሰሞን ተመራጮች ሥራ ይበዛባቸዋል። እንዲያውም ከፍተኛ ጫና ያለባቸው በዚያን ሰሞን ነው። በሕይወት ያሉና የሌሉትን ዘመዶቻቸውን ያስታውሳሉ። «አይ እከሌ ቢኖር! ስንት ሰው ባስፈረመ» እስከማለት ይቆጫሉ። ለዘመድ አዝማድ ስልክ መደወል ይበዛል፡፡ በውድቅት ሌሊትም ቢሆን ከመደወል ወደኋላ አይሉም። የስልክ ደብተሮች ሥራ ይበዛባቸዋል። ዘመድን ይቀርባሉ። የሰፈር ጐረምሶችን እጅ ይነሳሉ። ወጣት ሽማግሌውን በሰላምታቸው ያሰለቻሉ – ለሰፈር ሕፃናት ከረሜላ ገዝተው እስከማደል ይደርሳሉ። ደርሶ ቸር ይሆናሉ። 

ዳግም እንደነ ክሊንተን ለመመረጥ ያሰፈሰፉት ደግሞ «የሕዝቡን ስስ ብልት» እናውቃለን ይላሉ። እውነትም – ስስ ብልታችንን ያውቁታል። በተለይ ስስ ብልት በማወቅ ረገድ በስደት የቆዩት ፓርቲዎችና ግለሰቦች የተካኑ ናቸው፡፡ 

በአለባበስና በአሽሙር ንግግር የሚችላቸው የለም። ቀብረር ማለትን ያበዛሉ። የእንግሊዘኛ ቃላትን ይቀላቅላሉ። የአሜሪካንን ዴሞክራሲ በምሳሌነት ያቀርባሉ። የአውሮፓ ኅብረት ውህደት ተምሳሌታቸው ነው። 300 የፓርቲ አባል ይዘው ግን ጉራ ይነዛሉ። «ስልጣን ስጡን እንጂ ኢትዮጵያን እንገለባብጣታለን» እስከማለት ይደርሳሉ። 

በውጭ ቆይታቸው ግን ሀገሪቱን የሚጠቅም አንድ ሙያ እንኳ ይዘው አይመጡም። ምላጮች ቢሆኑም ምላጭ መስራት እንኳ አይችሉም። ያን ሰሞን የቀድሞ ተመራጮች ረዳቶቻቸውን አስከትለው በየቀጣናው ይሰማራሉ። ለሕዝብ ያስገኙለትን ጥቅም በመግለጽ ረገድ ወደር አይገኝላቸውም። ሕዝቡን መስለው ፣ እርሱን ሆነው ይቀርቡታል። መንገዶች ፣ ጤና ጣቢያዎች ፣ ትምህርት ቤቶች የጉብኝት አጀንዳ ያጣብባቸዋል። የበታች ሹሞች ያን ሰሞን ይርገበገባሉ ፣ ግሳፄውን ቶሎ ብለው በማስታወሻቸው ላይ ይይዛሉ። «ማስታወሻ ያዥ» ይበዛል በምርጫ ሰሞን። «በአስቸኳይ ይጠናቀቅየተለመደ ቀጭን ትእዛዝ ሆኖ ይከርማል። 

ተመራጮች መቼም ደጐች ብቻ ሳይሆኑ አዛኞችም ናቸው። ልበ-ጩቤነት የለባቸውም። ስለዚህ የሕዝብን ጓዳ ጐድጓዳ ማወቅ ይፈልጋሉ። የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ያን ሰሞን ያልፍላቸዋል። ንፁህና ክፍት ይሆናሉ። በዓመት በዓል ሰሞን የምናጣቸው ውሃና መብራቶች ይለቀቃሉ። ተመራጩም እጁን እያወዛወዘ ፣ ክራቫቱን እያስተካከለ «ፓርላማ ውስጥ የከረምነው ለሕዝቡ እድገት ነው» ሲል አጭር ዲስኩር ያደርጋል። አጠገቡ የቆመ ሁሉ ጭንቅላቱን ይነቀንቃል። ባልታሰበ ፍጥነት ጭብጨባ ይነግሳል። ጭብጨባው ማቋረጫ አይኖረውም።  

«አድምጡኝ ወገኖቼ! እኔ ብመረጥ የሚጠቀመው ማን ይመስላችኋል 
ሕዝብ ያዳምጣል። መልስ ግን አይሰጥም። 
«አትሳሳቱ! ተጠቃሚዎች በመጀመሪያ እናንተ ቀጥሎ አካባቢያችን ነው» 
ሕዝብ «እህእያለ አንገቱን ይነቀንቃል፡፡ 
«እኔ ብመረጥ እናንተ ተመረጣችሁ ማለት ነው። የእናንተ ድምጽ አዲስ አበባ መሀል ተሰማ ማለት ነው። ታዲያ እኔ አሸንፌ አዲስ አበባ ካልገባሁ እናንተን የሚያስታውስ ማን ይሆናል 
ሕዝብ ይታዘባል። ሕዝብ ያዳምጣል። ሕዝብ ይመዘግባል። ግን አይጠይቅም።
ከዚህ ዲስኩር በኋላ በሚከንፉ መኪኖች ውስጥ ሆኖ እጅ እያወዛወዙ ሰፊውን ሕዝብ በእንባ መለየት
ነው። ሕዝብን ሲለዩት እንዴት ያሳዝናል ወዳጄ!? 

ተመራጮች በምርጫ ሰሞን የማይገቡት ቃል የለም። ከግል ካዝናቸው ገንዘብ እያወጡ ለሕዝብ የሚገነቡ ይመስል ደርሶ ለጋስ ይሆናሉ። ሕዝቡ ውስጥ የማይጨበጥ ጉም ይረጫሉ። ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ፣ ወፍጮ በየሰፈሩ፣ ውሃ በየጓዳው፣ መብራት በየራስጌው ይዳረሳል። በአምስት ደቂቃ የቃላት ስፖርት ኢንፍራስትራክቸር ይዘረጋል። «ወንዝ በሌለበት ድልድይ» የሚገነቡ ቃላት አስገራሚዎች ናቸው። አንድ ቀልደኛ በምርጫ ሰሞን የቀለደውን አስታወስኩ።  «ድልድይም አሰራላችኋለሁ» አለ አንድ ተመራጭ። ሕዝብ ደግሞ «እኛ እኮ ወንዝ የለንም» ሲል አጉተመተመ። «ታዲያ ምን ችግር አለ ፣ ወንዙንም አስገባላችኋለሁ።» 

በምርጫ ሰሞን አደባባዮች ያስደስቱኛል። ግድግዳዎች ዓይኔን ይስቡታል። ምክንያቱም በተመራጮች ስለሚያምሩና የሚደምቁ በመሆናቸው ነው። የተመራጮች ፎቶግራፎች በየአደባባዩ ይገጠገጣሉ። 
«ዕድሜ- 32»
«የትምህርት ደረጃ – 12+ (የመደመር ምልክት መቼም አትቀርም
«የምርጫ ምልክት – አካፋ»
«የሚወዳደረው – ለፓርላማ» የሚለውን ካነበቡ በኋላ ፎቶዎቹን ደግሞ መመልከት ኀዘንን ልብ ውስጥ ይለቅቃል። አንዳንዶቹ ፊታቸው የገረጣ-ትክዝ ድንግዝ ያሉ ናቸው። ጆሮአቸው እንደ ደነገጠች ሚዳቋ ይቆማል። አንዳንድ ፎቶዎችን ከምርጫ ምልክቶች መለየት ያስቸግራል። መመሳሰልም ይታያል። ቢያንስ አንድ ነገራቸው ይመሳሰላል። ለምሳሌ የጀበና ምልክት የነበረው ተመራጭ አፍንጫው ከጀበና አፍንጫ ጋር መመሳሰሉ ግልጽ ነው። 

በእርግጥ ይህ መመሳሰል ለመራጩ ከፍተኛ ጥቅም አለው። በምርጫው ህግ መሰረት መራጩ ሕዝብ ትክክለኛውን ሰው ፣ ለትክክለኛ ቦታ ፣ በትክክለኛው ምልክት ለመምረጥ ይረዳዋልና ነው።

ተመራጮች ከተመረጡ በኋላ ጥሩ ይለብሳሉ። በዲስኩራቸው ጣልቃ «. . . . . . » ማለትን ያበዛሉ። ይህን መሰል አነጋገር ከመልካም ወንበር ይወለዳል። ድምጽም ጐርነን ይላል። «ሕዝባችን» የሚለው ቃል እንደ አንገት ማተብ አይለያቸውም። ታዲያ ትልቁ ችሎታቸው «ሰማዩ አረንጓዴ ነው» ብሎ ማስጨብጨብ ነው። ይህ ችሎታ ከዲስኩር ትምህርት ቤት እንኳ በቀላሉ አይገኝም።

አንዳንድ አፈ-ላጲሶች «ብዙ ተመራጮችን መምረጥ ሥራ አጥነትን ማቃለል ነው» የሚል ፈሊጥ አላቸው። እኔ ከእነዚህ እለያለሁ። እኛ ብዙ ሕዝብ ስላለን ብዙ መሪዎች ያስፈልጉናል። ብዙ ሰው ለአመራር መምረጥ ሥራን ያቀላጥፋል። ሀገራችን ያጣችው ብዙ ካቦዎችን እንጂ ሠራተኞችን አይደለም። ዴሞክራሲን በብዛት ለመተግበር ተመራጮች ይብዙልን አቦ!፡፡ የምርጫ ምልክቶችም ለዘለዓለም ይኑሩ! 

የግል ተወዳዳሪዎች የምርጫ አማተሮች ናቸው። ለቅስቀሳ የሚጠቀሙበት ዘዴ ያስገርማል። ከማስገረምም አልፎ ያሳዝናል። «የዓሣ ምልክት» ያለው ዕጩ ተወዳዳሪ በምን ጉዳዮች ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ተናግሮ ከማሳመን ይልቅ የባዮሎጂ መምህር ሆኖ ያርፈዋል። ዓሣ ትምህርት እንደሚገልጥ ፣ለአዕምሮ ብልፅግና ያለውን ድርሻ ይነግረናል። 

በእርግጥ ይህ ሰው ዓሣ የሚመገበው ሰርክ ሳይሆን በሁዳዴ ብቻ ነው። አንዳንዱ ደግሞ የኤሌሜንተሪ የግጥም ደብተሮቹን አገላብጦ ለውድድር የገባ ይመስላል። የተሰጠውን ጊዜ በግጥም ጨርሶ «አካፋ ነኝ ምረጡኝ» ሲል ማሳሰቢያ ይሰጣል። አንዳንዴ ድሬዳዋ ውስጥ ያገኘኋት ተመራጭ «ሆድዬ» ግን ከሌሎች ተመራጮች የተለየ አቀራረብ አላት። «ሆድዬ ነኝ ምረጡኝ አብረን እንበላለንትላለች።

ሌላው ተመራጭ ደግሞ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ይልና ዲስኩሩን ከሰውነት እንቅስቃሴ ጋር ያቆራኛል። ከፊት ለፊቱ ባለው ካሜራ ቀራጭ ላይ እጁን እያወዛወዘ ይደነፋል። ጥሩ አክተር መሆኑን ማንም ይመሰክራል። ብሔራዊ ቲያትር ቤት ክፍት የሥራ ቦታ ቢገኝለት የክላሲካል ቲያትሮች መሪ ተዋናይ እንደሚሆን መገመት አያቅትም። እንደ እውነቱ ከሆነ እርግጫም የሚቃጣው ዕጩ ባለፈው ሰሞን ምርጫ ታይቷል። «ይህስ ሰው ቴሌቪዥኔን ሊሰብርብኝ ነው» ብዬ ሰግቼያለሁ። 

እንደዚህ ዓይነቱ ሰው ቢመረጥ ፓርላማው መሀል ብጥብጥ ላለመፍጠሩና ቡጢ ላለመሰንዘሩ ምንም ዓይነት ዋስትና አይኖርም። ካልተመረጠ ደግሞ ምክንያት መደርደሩ ያለ ነው። «ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ አይደለም» ሲል በየጋዜጣውና በየባንኮኒው ላይ ቁጭቱን ይገልፃል። «ድሮም ወያኔን ለማጀብ ነበር» ሲል ድክመቱን መከረኛው ድርጅት ላይ ይለጥፋል። «ስህተቴ ምን ነበርማለት አልተለመደም። ምክንያት መደርደር ይቀናዋል - እንደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን። ለማንኛውም ምርጫ ለዘለዓለም ይኑር!
መኩሪያ መካሻ
ምንጭ ፡- እናት 100 ትረካዎች

 Home

No comments:

Post a Comment