Friday, February 15, 2013

የናይጄሪያ ቡድን የክብር ኒሻን፣ የገንዘብና የመሬት ስጦታ ተበረከተለት

(Feb 15, 2013, አዲስ አበባ)--29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቡርኪና ፋሶን አንድ ለዜሮ በማሸነፍ ዋንጫ ያነሳው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን የናይጄሪያን የክብር ኒሻን፣ የገንዘብና የመሬት ስጦታዎች ከፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ተበረከተለት።

በዚሁ መሰረት « ኦነር ኦፍ ሜምበር ኦፍ ዘ ኦርደር ኦፍ ኒጀር» የተባለውንና በኒጀር ወንዝ ስም የተሰየመውን የአገሪቱን የክብር ኒሻን ለተጫዋቾቹ በሙሉ ሲሰጡ፤ ለአሠልጣኙ ስቴፈን ኬሺ «ኮማንደር ኦፍ ዘ ኦርደር ኦፍ ዘ ኒጀር » የተባለውን ኒሻን ሸልመዋቸዋል። የቡድኑ ረዳቶችና አምበሉ ጆሴፍ ዮቦ ደግሞ « ኦፊሰር ኦፍ ዘ ኒጀር » የተባለውን የአገሪቱ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የአረንጓዴ ንስሮቹ አባላት በሙሉ የናይጄሪያ መንግሥት መሬት የሰጣቸው ሲሆን፤ የቡድኑ አሠልጣኝ ስቴፈን ኬሺ አስር ሚሊዮን ናይራ (62 500ዶላር) የገንዘብ ሽልማት እንደተሰጠው ቢቢሲ ዘግቧል ። የቡድኑ ተጫዋቾች ደግሞ እያንዳንዳቸው አምስት ሚሊዮን ናይራ (31 250 ዶላር) ሽልማት ተሰጥ ቷቸዋል።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን የአረንጓዴ ንስሮቹን አባላት «እንድንኮራ ስላደረጋችሁን እናመሰግናችኋለን። ላስመዘገባችሁት ድል ምስጋናና አድናቆት ይገባችኋል። ያስመዘገባችሁት ድል የማይሳካ ነገር እንደሌለ አሳይቶናል » በማለት አወድሰዋቸዋል ። 

ፕሬዚዳንቱ አክለውም « ..አ በ2012 ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ሲሳነን የአገራችን እግር ኳስ መሰረት እንደተናጋ ተደርጎ ሲወራ ነበር። ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ስታልፉም ማንም ዋንጫ ታነሳላችሁ ብሎ አልገመተም ። እናንተ ግን በፍጹም ወኔ ማሸነፍ ችላችኋል» በማለት የቡድኑ አባላት ያሳዩትን ጽናት አድንቀዋል። 

ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን የአገሪቱን የስፖርት ዘርፍ የበለጠ ለማሻሻል ጥረት እንደሚያደርጉም ለአረንጓዴ ንስሮቹ ሽልማት በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል ። አሠልጣኝ ስቴፈን ኬሺ ላስመዘገቡት ውጤት ያመሰገኑት ፕሬዚዳንቱ፤ በቀጣይም ቡድኑን ለብራዚሉ የዓለም ዋንጫ እንዲያሳልፍ ከአደራ ጋር አሳስበዋቸዋል። ለዚህም መንግሥታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል ።
 
በተለያዩ የኢንዱስትሪ መስክ የተሰማሩ የአገሪቱ ባለሀብቶች ሁለት ሚሊዮን ዶላር ለቡድኑ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል ። የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ለውድድሩ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዝ ቢያሸንፍም የገንዘብ ሽልማት እንደማይሰጠው የአገሪቱ የስፖርት ባለሥልጣናት የገለጹ ቢሆንም ቡድኑ በታሪኩ ለሦስተኛ ጊዜ ዋንጫ ማግኘቱን ተከትሎ ከፍተኛ የተባለውን ሽልማት ማግኘት መቻሉን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል ።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ

 Home

No comments:

Post a Comment