Tuesday, February 12, 2013

የአርቲስት ታምራት ሞላ የቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈፀመ

(Feb 12, 2013, አዲስ አበባ)--የአርቲስት ታምራት ሞላ የቀብር ሥነ ሥርዓት ትናንት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ፡፡ ታምራት በውጭና በሀገር ውስጥ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ በቀብር ሥነሥርዓቱ ላይ የተነበበው የሕይወት ታሪኩ እንደሚያስረዳው ድምፃዊ ታምራት ከፊታውራሪ ሞላ ዘለለውና ከአበራሽ የኔነህ በጎንደር ከተማ ጨርቆስ በሚባል አካባቢ በ
1936 .ም ነበር የተወለደው፡፡

ለቤተሰቡ አራተኛ ልጅ የሆነው ታምራት፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በጎንደር በፃዲቁ ዮሐንስ ትምህርት ቤት፣ ከዚያም ቀዳማዊ ምኒልክ አድቬንቲስት ትምህርት ቤት እስከ ዘጠነኛ ክፍል ተከታትሏል፡፡ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት በትምህርቱ አንደኛ በመውጣቱ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እጅ ሽልማት ተቀብሏል፡፡

ትምህርቱን አቋርጦ በክብር ዘበኛ የልጅ ወታደር ሆኖ የተቀጠረው ታምራት ሞላ በወቅቱ ጦር ሠራዊቱ ድምፃዊ ይፈልግ ስለነበር ተወዳድሮ በማለፍ የድምፃዊነት ሥራውን ጀምሯል፡፡ በ1955 .ም‹‹ታምሜ ተኝቼንና ዘወትር ብርቅነሽ›› የሚሉትን የመጀመሪያ ዘፈኖቹን ለሕዝብ አቅርቦ ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡ ከዚያ በኋላ በርካታ ዘፈኖችን ለሕዝብ ጆሮ አድርሷል፡፡ ሥራዎቹን በውጭና በሀገር ውስጥ ተዘዋውሮ በማቅረብ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ እድገት በሙያው አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

በሙያው ላደረገው አስተዋፅፆ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የወርቅ ሰዓትና ከሌሎች አካላትም ልዩ ልዩ ሽልማቶች ተበርክቶለታል፡፡ ድምፃዊ ታምራት ሞላ ልዩ ልዩ ማህበራዊ ተሳትፎ በማደረግና ችግረኞችን በመርዳት በአርዓያነት ይሠራ እንደነበር የህይወት ታሪኩ ያስረዳል፡፡ 

አርቲስቱ ባለትዳርና የሁለት ሴቶችና ሦስት ወንዶች አባት ነበር፡፡ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ሲፈፀም ወዳጅ ዘመዶቹ፣ የሥራ ባልደረቦቹና አድናቂዎቹ ተገኝተዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment