Friday, February 01, 2013

ዋልያዎቹ ውጤት ቢርቃቸውም ጥሩ ጨዋታ አሳይተዋል

(Feb 01, 2013, ቦጋለ አበበ)--ዋሊያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ባሳዩት ማራኪ ጨዋታ ሊመሰገኑ ይገባል፤ ከሰላሳ አንድ ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተመለሱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች ዋልያዎቹ በምድብ ሦስት ከዛምቢያ፤ቡርኪናፋሶና ናይጄሪያ ጋር የተደለደሉበትን የመጨረሻ የምድብ ጨዋታቸውን በሽንፈት አጠናቅቀዋል።  
 

ዋልያዎቹ የመጨረሻውን የምድብ ጨዋታቸውን ከናይጄሪያ ጋር አድርገው ሁለት ለዜሮ በሆነ ውጤት ተሸንፈው ወደ ሩበ ፍፃሜ ሳያልፉ ቀርተዋል።በጨዋታው ዋልያዎቹ ከቡርኪናፋሶ ጋር ሁለተኛውን ጨዋታቸውን ሲያካሂዱ የነበሩባቸውን ክፍተቶች አሻሽለው ታይተዋል።

south africaየአጨዋወት ስልት ቀይረው ተጠባባቂ የነበሩትን ዩሱፍ ሳላና ፉአድ ኢብራሂምን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ያሰለፉት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ሁለተኛውን የምድብ ጨዋታ ሲያደርጉ ካሳዩት እንቅስቃሴ በሁሉም መልኩ የተሻለ አሰላለፍ ይዘው ቀርበዋል።

ዋልያዎቹ ሙሉውን ዘጠና ደቂቃ ኳስ ተቆጣጥረው በናይጄሪያ ላይ የጨዋታ ብልጫ ወስደዋል። ዋልያዎቹ ግብ ማስቆጠር ባይችሉም ደጋፊውን በጨዋታ እንዲረካ አድርገዋል።ሰማኒያኛው ደቂቃ ላይ አሉላ ግርማ ግብ ጠባቂ ክልል ውስጥ በሰራው ጥፋት ናይጄሪያዎች በፍፁም ቅጣት ምት አንድ ለባዶ እየመሩ በነበረበት ሰዓት እንኳን ዋልያዎቹ ሳይደናገጡ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገዋል።

በመጨረሻው የምድብ ጨዋታቸው ማራኪ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ደጋፊውን ከማስደሰቱም በላይ ተጫዋቾቻችን በዓለምአቀፍ ውድድሮች ልምድ ሲኖራቸው ትልቅ ነገር ሊሰሩ እንደሚችሉ ያመላከተ ነው። በጨዋታው ላይ የነበረባቸው ትልቅ ድክመት የልምድ ማነስ ነው ማለት ይቻላል።ጨዋታው ሊጠናቀቅ አስር ደቂቃ ሲቀረው የተቆጠሩትን ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶችም ሊገኙ የቻሉት በተጫዋቾቻችን ልምድ ማነስ ነው።
 
በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ዋልያዎቹ በተለይም በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸው ከዛምቢያ አቻቸው ጋር ሲጫወቱ ያሳዩት አስደናቂ ብቃት እንድንኮራባቸው አድርጓል። ዋንጫ የማንሳት ግምት የተሰጣት ናይጄሪያ እንደተጠበቀችው ጥሩ አቋም ይዛ አልተገኘችም።ይሁን እንጂ ከሦስተኛው ምድብ ወደ ሩብ ፍፃሜ ካለፈችው ቡርኪናፋሶ ጋር ተያይዛ አልፋለች።ናይጄሪያ ደካማ እየተባለ የሚገኘውን አቋም ይዛ በሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ኮትዲቯርን ትገጥማለች።
 
ኮትዲቯር የአፍሪካ ዋንጫው የመጀመሪያ ከፍተኛ ቅድመ ግምት የተሰጣትና ጥሩ አቋም እያሳየች እንደመሆኗ መጠን ናይጄሪያን በቀላሉ አሸንፋ ግማሽ ፍፃሜ የመግባት ዕድል አላት።ናይጄሪያ በበኩሏ አሁን ያላትን አቋም አሻሽላ በሩብ ፍፃሜው ካልቀረበች በቀላሉ የማሸነፍ ዕድል የላትም።

የአምናዋ ሻምፒዮን ዛምቢያ ሦስቱንም የምድቧን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ ከምድብ ሦስት ከኢትዮጵያ ቀጥሎ በጊዜ ከአፍሪካ ዋንጫ የተሰናበተች ሀገር ሆናለች።ዛምቢያ አምና ሻምፒዮን እንደመሆኗ መጠን ዘንድሮ ከምድቧ ማለፍ ያለመቻሏ አስደናቂ ነገር ሆኗል።

አምስት ነጥብ መሰብሰብ የቻሉት ቡርኪናፋሶዎች በበኩላቸው በመጨረሻው የምድብ ጨዋታ ከዛምቢያ ጋር አቻ መውጣታቸው በቀጥታ ወደ ሩብ ፍፃሜ አሳልፏቸዋል።ወደ ግማሽ ፍፃሜ ለማለፍም ከምድብ አራት ሁለተኛ ሆኖ ወደ ሩብ ፍፃሜ ካለፈ ሀገር ጋር ትፋለማለች።
አዲስ ዘመን
 Home

No comments:

Post a Comment