Tuesday, January 22, 2013

ዋሊያዎቹ የማይቻል ነገር የለም እያሉ ነው

(Jan 22, 2013,አሰግድ ተስፋዬ)--ከ31 ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላትና ልዑካን ከትናንት በስቲያ ኦሊቨር ታምቦ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ሲደርሱ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።


በአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው የተገኙት ኢትዮጵያውያን እጅግ በርካታ ከመሆናቸውም በላይ የአገራችንን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ የብሔራዊ ቡድኑ አለኝታ መሆናቸውን አስመስክረዋል። የብሔራዊ ቡድኖቻቸውን ጨዋታዎች ለመመልከትና ድጋፍ ለመስጠት ቀድመው በርካታ ቁጥር ያለው የስቴዲየም መግቢያ ቲኬት ከገዙት አፍሪካውያን መካከል ኢትዮጵያውያን ከዛምቢያ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጡ ሲሆን፤ ድጋፋቸውን ቡድኑ ደቡብ አፍሪካ ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ መስጠት ጀምረዋል።

ዋሊያዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ነገ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ከአምናዋ ሻምፒዮና ከዛምቢያ ጋር የሚያደርጉ ሲሆን፤ በኢትዮጵያውያን ጠንካራ ድጋፍ እንደሚታጀቡ ይጠበቃል። የቡድኑ አባላትም በደቡብ አፍሪካ የሚኖራቸው ቆይታ ከአገር ቤት ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን መግለጻቸው ይታወሳል። 

ዋሊያዎቹ ሰኞ ከቺፖሎፖሎ ጋር በኔልስፕሩት ከተማ በሚገኘው ምቦምቤል ስቴዲየም የሚያደርጉትን ጨዋታ ለመመልከት የመግቢያ ቲኬት በመግዛት የመጀመሪያዎቹን ሁለት ደረጃዎች በያዙ በሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች ደማቅ ድጋፍ በሻምፒዮናው ከሚደረጉት ጨዋታዎች ሁሉ ልዩ ሊሆን እንደሚችል ነው የሚጠበቀው። 

የዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፈረንሳዊው ኸርቬ ሬናርድ ከፍተኛ ደጋፊ ካላቸው ከዋሊያዎቹ ጋር የሚደርጉት የመጀመሪያ ጨዋታ እጅግ ፈታኝና ከባድ ሊሆንባቸው እንደሚችል የተናገሩትም ከዚህ በመነሳት ይመስላል። አሰልጣኙ አሉት ብሎ ኤምቲኤንፉትቦል ዶት ኮም ድረ ገጽ እንደዘገበው ኢትዮጵያ ለሻምፒዮናው ለማለፍ ያደረገቻቸው የማጣሪያ ጨዋታዎች የወቅቱ ሻምፒዮናዎች የመጀመሪያ ጨዋታ ፈታኝ ሊሆንባቸው እንደሚችል ጉልህ ማሳያ ነው።
 
የአምና ድላቸውን ለማስጠበቅ ያስችላሉ ያሏቸውን ተጫዋቾች በቡድናቸው አካትተው ጠንካራ ልምምድ ሲያደርጉ የከረሙት ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ለድረ ገጹ በሰጡት አስተያየት፤ የዋሊያዎቹ ስብስብ ግላዊ ተሰጥኦ ያላቸው በርካታ ተጫዋቾችን ያካተተ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የቡድኑ አባላት ሙሉ ዘጠና ደቂቃ በብቃት የሚጫወቱ ናቸው። በመሆኑም ቺፖሎፖሎዎቹ በጥንቃቄ መጫወት ይጠበቅባቸዋል። «በሦስት የወዳጅነት ጨዋታዎች ሽንፈት ያላስተናገዱትን ዋሊያዎቹን ተረጋግተው እንዳይጫወቱ ማድረግ አስቸጋሪ ነው» ሲሉም ነው ሬናርድ ለድረ ገጹ የተናገሩት።  

«የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በርካታ ልዩ ክህሎት ያላቸውና ዘጠና ደቂቃ በብቃት መጫወት የሚችሉ ተጫዋቾችን ያካተተ ቡድን ነው። በመሆኑም በጣም መጠንቀቅ ይኖርብናል » ሲሉም አክለዋል። ዋሊያዎቹ ባደረጓቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች ኒጀርንና ታንዛኒያን አንድ ለዜሮና ሁለት ለአንድ ሲያሸንፉ በአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ከሆነችው ከቱኒዚያ ጋር አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት መለያየታቸው ይታወሳል።
 
ዋሊያዎቹ ከ31 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያደርጉትን ጨዋታ በአምበልነት በመምራት ወደሜዳ እንደሚገባ የሚጠበቀው 19 ቁጥር ለባሹ አዳነ ግርማ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በሰጠው አስተያየት ላይም የሚስተዋለው የራስ መተማመን ይህንኑ የአሰልጣኝ ሬናርድን አስተያየት የሚያጠናክር ነው።

«ከሻምፒዮናው ለረጅም ዓመታት ርቀናል። በውድድሩም ከፍተኛ ፉክክር ሊጠብቀን እንደሚችል እንገምታለን። ይሁንና ጥሩ የስነልቡና ዝግጅት አድርገናል። የቡድናችን ሞራልም ከፍተኛ ነው። ከዚህም በላይ ቡድናችን ጠንካራ በመሆኑ ማንኛውንም ዓይነት ፉክክር ለመቋቋም የሚያስችል አቅም አለን »በማለት ነው አዳነ የተናገረው። 

የፊት መስመር ተሰላፊው አዳነ « የመጀመሪያው ተጋጣሚያችን የዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ጠንካራ ቢሆንም የአፍሪካ ዋንጫውን ሁለት ጊዜ ያነሳችውን ናይጄሪያንና ቡርኪናፋሶን ከመግጠማችን በፊት ዛምቢያን ለማሸነፍ ቡድናችን አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል » ሲልም ተናግሯል።

ዋሊያዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በማሸነፍ ከምድባቸው ሆነው ለቀጣይ ጨዋታዎች ማሰብ አላማቸው መሆኑንም ነው አዳነ ግርማ ለዜና ምንጩ የተናገረው። ሳላዲን ሰዒድም በተመሳሳይ ዋሊያዎቹ ከዛምቢያና ናይጄሪያ ጋር በመደልደላቸው ምንም የተለየ ነገር ሊፈጠር እንደማይችል ተናግሯል። ተጫዋቹ አክሎም «እኛ ትልቅ ስም ላላቸው ቡድኖችና ተጫዋቾች ብዙ ግምት አንሰጥም። የእኛ ዋና ትኩረት ማሸነፍና ማሸነፍ ብቻ ነው» ብሏል ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በሰጠው መግለጫ።
 
የዋሊያዎቹ ዋና አሰልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው በበኩላቸው የቡድናቸው በራስ መተማመን ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው የጠቆሙት። በተለይ ከ2004 የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤቷ ቱኒዚያ ጋር አቻ ከተለያዩ በኋላ የቡድናቸው በራስ መተማመን ይበልጥ ከፍ ማለቱን ለዜና ምንጩ ተናግረዋል። አሰልጣኝ ሰውነት ቡድናቸው በአፍሪካ ዋንጫው ብቻ የማቆም ዓላማ እንደሌለውም ተናግረዋል። « በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ምድባችንን በመምራት ላይ እንገኛለን። ለዓለም ዋንጫ እንደምናልፍም ተስፋ አደርጋለሁ » ብለዋል።
 
በአፍሪካ ዋንጫው ዋሊያዎቹ የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ መሆን ባይችሉም እንኳን የረጅም ርቀት ሯጮች አገር ለሆነችው ኢትዮጵያ አጋጣሚው ልምድ መቅሰሚያና ለሌላ ታላላቅ ውድድሮች መዘጋጃ ነው። አሰልጣኙ አክለውም « የተጫዋቾቼ የስነ ልቡና ዝግጅት ከፍተኛ ነው። ችሎታቸውን አውጥተው ለዓለም ለማሳየት ጓጉተዋል » ብለዋል።

« ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ብዙ ጊዜ ሞክረናል። በርካታ አሰልጣኞችንም የውጭ ዜጎችን ጨምሮ ቀያይረን ሞክረናል። አሁን ግን ኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች አሳክተውታል። ይህም ለአገራች ታላቅ ስኬት ነው » ማለታቸውንም ነው ዘገባው ያመለከተው። በሰኞው ጨዋታ በሁለት ቢጫ የማስጠንቀቂያ ካርድ ምክንያት የማይሰለፈው የቡድኑ አምበል ደጉ ደበበ ደግሞ ካለፈው የዛምቢያ ስኬት መማር አለብን ይላል። «የማይቻል የሚመስል ነገር የሚቻል መሆኑን ለማሳየት ከዛምቢያ መማር አለብን » ይላል የ29 ዓመቱ የተከላካይ መስመር ተጫዋች። 
 
በአውሮፓውያኑ 1982 በሊቢያ ከተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮና በኋላ ተሳታፊ የሆነውን ቡድን በአምበልነት የሚመራው ደጉ ደበበ በሻምፒዮናው ዋናው ነገር የቡድኑ ጥንካሬ እንደሆነ ያምናል። « በሻምፒዮናው ትልቁ ነገር ጥንካሬአችን ነው። ይህንንም ከአምናዋ ሻምፒዮን ከዛምቢያ መማር አለብን። ዛምቢያ ዋንጫውን ታነሳለች ብሎ ማንም አልገመተም። ዛምቢያዎች ለድል የበቁት ለማንም ቀላል ግምት ሳይሰጡ እንደ ቡድን ስለተጫወቱ ነው » ብሏል ለዋሊያዎቹ ለ46 ጊዜያት የተጫወተው ደጉ ደበበ። 
አዲስ ዘመን ጋዜጣ
 Home

No comments:

Post a Comment