Tuesday, January 22, 2013

በአፍሪካ ዋንጫ ምን እንጠብቅ?

(Jan 22, 2013, አዲስ አበባ, ቦጋለ አበበ)--የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ባለፉት አስር ዓመታት ከተካሄዱ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች በብዙ መልኩ ይለያል። በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት ለሃያ ዘጠነኛ ጊዜ የሚካሄደው ይህ ዋንጫ በአንድ ዓመት ልዩነት የተካሄደ ልዩ የዋንጫ ውድድር ነው። 


ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ ወደ መሰረተችው የአፍሪካ ዋንጫ ከሰላሳ አንድ ዓመት በኋላ ባልተጠበቀ ሁኔታ በድንቅ ብቃት የተመለሰችበት ነው። ኬፕቨርዴ ለመጀመሪያ ጊዜ አህጉራዊ ውድድሩን ተካፋይ የሆነችበ ተመሆኑም ለልዩነቱ ሌላው ምክንያት ነው።

ኢትዮጵያ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ስትመለስ፤ኬፕቨርዴ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳታፊ የመሆን እድል ታግኝ እንጂ ሁለቱ ሀገሮች ሻምፒዮናውን ለመቀላቀል ያሳዩት ብቃት ዓለምን እያስደመመ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ያላቸው ቤኒንና ሱዳንን የመሳሰሉ ሀገሮችን በአስደናቂ ሁኔታ አሸንፋ በአፍሪካ ዋንጫው የመሳተፍ እድል ማግኘቷ በሀገራችን እግር ኳስ ላይ ታላቅ መነቃቃት ፈጥሯል። ዋልያዎቹ በመባል የሚታወቁት የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾቻችን በሻምፒዮናው የተለየ ደረጃ ይደርሱ ዘንድ ፌዴሬሽኑ ከህዝብ ጋር ተባብሮ የተወሰኑ የወዳጅነት ጨዋታዎች ለማካሄድ ችለዋል። የወዳጅነት ጨዋታዎቹ ላይ ዋልያዎቹ ያሳዩት አስደናቂ ብቃትም ሀገራችን ከተሳትፎ ባለፈ በአፍሪካ ዋንጫ ጠንካራ ተፎካካሪና አዲስ ክስተት ትሆናለች የሚል ግምት ከዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ተሠጥቷል።

ከሀገር ውስጥ ሊጎችና በውጭ ከሚገኙ ጥቂት ተጫዋቾች የተዋቀረው የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ስብስብ ከአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በፊት ይህ ነው የሚባል ግምት ባያገኝም ከስዊድን ሀገር የመጣው የክንፍ ተጫዋች ዩሱፍ ሳላ፤ከአሜሪካ ሜኒሶታ የመጣው ፉአድ ኢብራሂም፤በግብፅ ዋዲ ዳግላ ክለብ የሚጫወተው ሳላዲን ሰኢድ፤አዳነ ግርማና ሌሎች የአገር ውስጥ ሊጎች ተጫዋቾች እያሳዩት ያለው ብቃት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ የተለየ ግምት እንዲሰጣት አድርጓል።

በዋልያዎቹ ስብስብ ሳላዲን ሰኢድ አፍሪካ ዋንጫ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ መፍጠር ከሚችሉ ተጫዋቾች ዋነኛው ሊሆን እንደሚችል ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በመዘገብ ላይ ይገኛሉ። ሳላዲን ከእነ ዩሱፍ ሳላና ፉአድ ኢብራሂም ጋር የፊት መስመሩን በመምራት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ከሰላሳ አንድ ዓመት በኋላ ያልተጠበቀ ውጤት እንድታስመዘግብ የማድረግ አቅም እንዳለው እየተነገረለት ነው።

በሌላ በኩል የኮትዲቯር ወርቃማው የእግር ኳስ ትውልድ የተባለለት የእነ ዲዲየር ድሮግባ፤ኮሎ ቱሬና ያያ ቱሬ ስብስብ የአፍሪካ ዋንጫን የማንሳት የመጨረሻ እድላቸው የዘንድሮው ውድድር ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው።

በተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች ትልቅ ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉ በርካታ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾችን ያሰባሰበው የኮትዲቯር ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ የፊፋን የደረጃ ሰንጠረዥ በቀዳሚነት መምራት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይሁን እንጂ ወርቃማው የእግር ኳስ ትውልድ በተደጋጋሚ ለፍፃሜ ቢደርስም ዋንጫውን ለማንሳት በለስ አልቀናውም። ባለፉት ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች እንኳን ለፍፃሜ ደርሶ በግብፅና በዛምቢያ በመለያ ምት ተሸንፎ ዋንጫ ሳያነሳ ቀርቷል።

የኮትዲቯር ኮከቦች እድሜያቸው እየገፋ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን የመሆን የመጨረሻ እድላቸው በመሆኑ የስብስቡን ወርቃማነት የሚያስመሰክር ዋንጫ የሚያነሱበት አጋጣሚ አሁን ነው። በእዚህም የተነሳ ዝሆኖቹ በመባል የሚታወቁት የኮትዲቯር ተጫዋቾች የሚታወሱበትን ዋንጫ ለማንሳት ከመቼውም በላይ የተለዩ ሆነው እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

በእንግሊዙ ቼልሲ ክለብ አስደናቂ ብቃቱን በማሳየት ባለፈው የውድድር ዓመት መጨረሻ ወደ ቻይናው ክለብ ሻንጋይ ሽኑዋ ያመራው ዲዲየር ድሮግባ በሀገሩ ታላቅ ክብር ቢሰጠውም የአፍሪካ ዋንጫን አንስቶ ለሚያከብረው የሀገሩ ህዝብ ደስታን መፍጠር አልቻለም።ይሁን እንጂ ምናልባትም የመጨረሻው በሆነው የአፍሪካ ዋንጫ የተለየ ችሎታውን ተጠቅሞ ታሪክ የሚሰራበትን እድል ሊፈጥር የማይከፍለው መስዋዕትነት አይኖርም።

ጥቋቁር ከዋክብት በመባል የሚታወቁት የጋና ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች የአፍሪካ ዋንጫን ለማግኘት ጉጉት ያደረበትን ህዝባቸውን ለማስደሰት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረጉ ናቸው። ጋናውያን ተጫዋቾችም ዋንጫ ለማንሳት የዘንድሮው ስብስብ ትልቅ እድል እንዳለው አምነው ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል።

ጋናውያን በተለያዩ የአፍሪካ ዋንጫዎች ቢያንስ ግማሽ ፍፃሜ የመድረስ እድል ነበራቸው።ነገር ግን በተለያዩ ስህተቶች ዋንጫ ለማንሳት ሳይታደሉ ቀርተዋል።እ..አ በ2010 የደቡብ አፍሪካ የዓለም ዋንጫ ላይ አፍሪካን ያኮራ ብቃት ካሳዩ ጋናውያን ተጫዋቾች መካከል በርካቶቹ በዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የጥቋቁር ከዋክብቱ አባላት ናቸው። ከእነዚህም መካከል ዋነኛው አሳሞአ ጂያን ተአምር ይፈጥራል የሚል ግምት አግኝቷል።

ባለፈው የኢኳቶሪያል ጊኒና ጋቦን የአፍሪካ ዋንጫ ያልታሰበ ታሪክ የሰሩት ዛምቢያዎች ለዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ሲያደርጉ ባካሄዷቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች በበርካቶቹ መሸነፋቸው በዋንጫው የተሰጣቸው ግምት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሮባቸዋል። የአምናው ስብስብ አሁንም አንድ ላይ በመኖሩ ያለፈውን ብቃታቸውን የመድገም እድል እንዲኖራቸው ያደርጋል።

«በክርስቶፈር ካቶንጎ የሚመራው የዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞው ጥንካሬውንና የቡድን መንፈሱን አሁንም ከደገመ ታሪክ ይሰራል» የሚሉ አስተያየቶች በዝተዋል። አንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ግን ዛምቢያዎች የምድብ ጨዋታቸውን እንኳን ለማለፍ ይቸገራሉ እያሉ ይገኛሉ። ከአስራ ስድስት ዓመት በፊት ባስተናገደችው የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን መሆን የቻለችው አስተናጋጇ ደቡብ አፍሪካ ዘንድሮም ተመሳሳይ ታሪክ የመስራት እድል ይኖራታል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ    

 Home

No comments:

Post a Comment