Sunday, October 28, 2012

በእስራኤል የተደበደበው የሱዳን ሚስጢራዊ የጦር መሣሪያ ፋብሪካ ለኢትዮጵያ ሥጋት መሆኑ ተጠቆመ

(Oct 27, 2012, Reporter)--ባለፈው ማክሰኞ ሌሊት ከሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በስተደቡብ የሚገኘው ሚስጥራዊ የጦር መሣርያ ፋብሪካ በእስራኤል የሚሳይል ጥቃት እንደተፈጸመበት ከታወቀ በኋላ፣ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥጋት መሆኑን ዜጎችና የፖለቲካ ተንታኞች እያስረዱ ነው፡፡

እስራኤል በዚህ እጅግ ሚስጥራዊ ነው በተባለለት ወታደራዊ የጦር መሣርያ ፋብሪካ ላይ ጥቃቱን የፈጸመችው በቅርቡ በሒዝቦላህ የተላከባት ሰው አልባ የጦር አውሮፕላን (Drone) ግዛቷ ውስጥ መትታ ከጣለች በኋላ መሆኑ ታውቋል፡፡ የእስራኤል ወታደራዊ ባለሥልጣናት ሰው አልባው የጦር አውሮፕላን የተመረተው በካርቱም የጦር መሣርያ ፋብሪካ ውስጥ መሆኑን፣ በግብፅ በኩል ተጓጉዞ ለኢራን ከደረሰ በኋላ ሊባኖስ ውስጥ ለመሸገው ሒዝቦላህ መሰጠቱን መግለጻቸው በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኅን ተገልጿል፡፡

ምንም እንኳን እስራኤል የጦር መሣርያ ፋብሪካውን በሚሳይል ማጥቃቷን በቀጥታ ባታስተባብልም፣ የሱዳን መንግሥት ከጠላቶቿ ጋር እያሴረባት መሆኑን ወታደራዊ ባለሥልጣናቷ እየገለጹ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡ የሱዳን መንግሥት ጥቃቱን የፈጸመችው እስራኤል መሆኑን አስታውቆ፣ ጉዳዩን ወደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እወስዳለሁ ብሏል፡፡ በተጨማሪም ለጥቃቱ አፀፋ ምላሽ እንደሚሰጥ ዝቷል፡፡ የሱዳን መንግሥት የካርቱም የጦር መሣሪያ ፋብሪካው መደብደቡን ማረጋገጡ ለኢትዮጵያና ለአካባቢው አገሮች ጭምር ሥጋት መሆኑን የሚገልጹት ተንታኞች፣ በተለይ ኢትዮጵያ ጉዳዩን ትኩረት ሰጥታ ልትከታተለው ይገባል ይላሉ፡፡

ለዚህ አባባላቸው ዋቢ የሚያደርጉት ከካርቱም በስተደቡብ ከዋናው አውራ ጎዳና ሁለት ኪሎ ሜትር ገባ ብሎ በአደገኛ የሽቦ መከላከያ የታጠረው ሚስጥራዊ የጦር መሣርያ ፋብሪካ፣ በኢራን ድጋፍ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖችንና ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይሎች ስለሚመረቱበት ነው፡፡ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ምርምር የሚያካሂዱ አንድ ስማቸው ያልተገለጸ ተመራማሪ፣ በሱዳን ውስጥ የተገነባው ሚስጥራዊ የጦር መሣርያ ፋብሪካ ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ላለችው የህዳሴ ግድብ ጠንቅ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡

በቅርቡ ዊክሊክስ በዓባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የምትገነባቸውን ግድቦች ግብፅ በሚሳይል ወይም በልዩ ኮማንዶዎች ለማውደም ዕቅድ እንደነበራት መጋለጡን የሚያስታውሱ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ኢትዮጵያዊ የመስኩ ባለሙያ የሱዳን፣ የግብፅና የኢራን ጥምር ፕሮጀክት የሆነው የጦር መሣርያ ፋብሪካ በእስራኤል መመታቱ ለኢትዮጵያ የማንቂያ ደወል ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህ ሚስጥራዊ የጦር መሣርያ ፋብሪካ ምናልባት የኢትዮጵያ መንግሥት መረጃ ሊኖረው ይችላል የሚሉት ባለሙያው፣ በእስራኤል ጥቃት እንደደረሰበት ይፋ መውጣቱ ግን ሥጋቱ ምን ያህል ግዙፍ እንደሆነ ያሳያል ብለዋል፡፡

ከዚህ ሚስጥራዊ የጦር መሣርያ ፋብሪካ በስተጀርባ ግብፅ እንዳለችበት ሳይታለም የተፈታ ነው የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ሌላው አስተያየት ሰጪ፣ ኢትዮጵያ ስድስት ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የምትገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ምን ያህል አደጋ እንደተጋረጠበት ማሰብ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ የሱዳንና የግብፅ ሚስጥራዊ ግንኙነቶችና ትብብሮች እንዲህ ሲጋለጡ ማየት ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡

አንድ የእስራኤል ወታደራዊ ባለሥልጣን ‹‹የሱዳን መንግሥት በዓለም ላይ አደገኛው አሸባሪ ነው›› በማለት በእስራኤል ሬዲዮ ሰሞኑን የተናገሩትን ያስታወሱት እኚሁ መምህር፣ የሱዳን መንግሥት በፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር አመራር ከኢትዮጵያና ከአካባቢው አገሮች በስተጀርባ ምን እየሠራ እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት በንቃት መከታተል አለበት ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል የተፈጠረውን ችግር በመፍታት ሰላም ለማውረድ ስትሯሯጥ፣ ለህልውናዋ አደገኛ የሆነ ተግባር ሱዳን ውስጥ ሊቀነባበር ስለሚችል ብርቱ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

እስራኤል ከ18 ወራት በፊት ሱዳን ውስጥ ተመሳሳይ ድብደባ መፈጸሟን የሚያስታውሱ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ውስጥ የሆነ አንድ የምዕራብ አገር ዲፕሎማት፣ የአል በሽር መንግሥት ከኢራን ጋር በመተባበር ሒዝቦላን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን፣ ሮኬቶችንና ተወንጫፊ ሚሳይሎችን እንደሚያስታጥቅ ግልጽ እየሆነ መጥቷል ይላሉ፡፡ ዲፕሎማቱ የሱዳን የጦር መሣርያ ፋብሪካ በተለይ  በኢትዮጵያ ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ሥጋት በአሁኑ ወቅት ለመግለጽ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ግን ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባታል ይላሉ፡፡

አል በሽር ዳርፉር ውስጥ በተፈጸመ የጦር ወንጀል ምክንያት በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ዋራንት ተቆርጦባቸው ሲፈለጉ፣ ኢትዮጵያና የተወሰኑ የአፍሪካ አገሮች ትብብር አለማድረጋቸው ትክክል አለመሆኑን የገለጹት ዲፕሎማቱ፣ የአል በሽር ሕገወጥ ተግባሮች ግን ለኢትዮጵያም ሆነ ለአካባቢው አገሮች አይበጁም ብለዋል፡፡ ዲፕሎማቱ ግብፅ በጦር መሣርያው ፋብሪካው ስላላት ተሳትፎ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ለጊዜው ተጨባጭ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸው፣ እስራኤል እንዳለችው ሰው አልባዎቹ አውሮፕላኖች በግብፅ በኩል ለሒዝቦላ ደርሰው ከሆነ መጠርጠር አይከፋም ብለዋል፡፡ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የሙስሊም ወንድማማቾች ቡድን አመራር ከእንዲሀ ዓይነቱ ድርጊት ሊታቀብ እንደማይችልም ጠቆም አድርገዋል፡፡

የግብፅ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ በሱዳን ላይ ጥቃት አድርሳለች የተባለችውን እስራኤልን ባለፈው ዓርብ ማውገዛቸውን ተከትሎ፣ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ፕሬዚዳንቱ እስራኤልን ያወገዙት ለሱዳን ጉርብትና ሲሉ ሳይሆን ግብፅ የጦር መሣርያ ፋብሪካው ባለድርሻ በመሆኗ ነው እያሉ ነው፡፡ ሙርሲ እስራኤል በሱዳን ላይ ወረራ ፈጽማለች ብለው፣ አገራቸው ግብፅ ለሱዳን ድጋፍ ትሰጣለች ማለታቸው ግብፅ የጦር መሣርያ ፋብሪካው ጥቃት እንዳበሳጫት አመላካች መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ግብፅ እጇ ባይኖርበት ኖሮ ይኼን ያህል ለምን ትንጨረጨራለች በማለት የሚጠይቁት አስተያየት ሰጪዎች፣ የእስራኤል ድርጊት መወገዝ ከነበረበት በአፍሪካ ኅብረት ነበር ይላሉ፡፡

የብዙዎች ጥያቄ የካርቱም የጦር መሣርያ ፋብሪካ ለእስራኤል ሥጋት ሆኖ ዕርምጃ ከወሰደችበት፣ ለኢትዮጵያስ ሥጋት አይሆንም ወይ የሚለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ለመገንባት እንቅስቃሴዎችን ስታደርግ፣ ለህልውናችን አስጊ ሊሆን ይችላል በማለት የሚያስቡት ግብፅና ሱዳን ነገ ከነገ ወዲያ ምን ዓይነት የተቀናጀ ጥቃት ሊሰነዝሩ እንደሚችሉ ማሰብ የግድ መሆኑን በአጽንኦት ይናገራሉ፡፡

የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል እንዲኖር አዲሱን የትብብር ማዕቀፍ ሲፈርሙ ግብፅና ሱዳን እስካሁን ማፈንገጣቸውን የሚያስታውሱት የተፋሰስና የተሻጋሪ ወንዞች ባለሙያዎች፣ በቅርቡ በዊኪሊክስ የወጣውን መረጃ ፈጽሞ ማጣጣል አያስፈልግም ሲሉ ይመክራሉ፡፡ እስራኤልና ኢራንን ከበስተጀርባ የሚያናቁረው የካርቱም ጦር መሣርያ ጥቃት አሁን ግብፅን ጭምር ያካተተ በመሆኑ፣ ከማንም በላይ የወደፊት ጥቃት ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ የምትሆነው ኢትዮጵያ የተፋሰሱን አገሮች በማስተባበር ዓለም አቀፍ የሰላም ዘመቻ ማካሄድ አለባት ይላሉ፡፡

ለወታደራዊ ጥቃት ከሚደረገው ዝግጅት በተጓዳኝ የዓባይን ወንዝ በሰላምና በፍትሐዊ መንገድ መጠቀምን አስፈላጊነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስደመጥ ግብፅና ሱዳንን ወደ ድርድር ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን አጋጣሚ በሚገባ ሊጠቀምበት ይገባል ሲሉም ያሳስባሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በንቃት እንደሚከታተል የገለጹ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ ባለሥልጣን፣ መንግሥት በችኮላ የሚሰጠው አስተያየት እንደሌለ ገልጸው፣ እንደወትሮው ሁሉ በዓባይ ዙሪያ ከማንኛውም ወገን ጋር ለመነጋገርና ለመደራደር ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡ የህዳሴ ግድቡን በተመለከተም የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ባለሙያዎች በጋራ እየሠሩ መሆኑን አስታውቀው፣ መንግሥት ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኙ ይሠራል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

የእስራኤልን የካርቱም የጦር መሣርያ ፋብሪካ ጥቃት በተመለከተም ከሚዲያ ከመስማታቸው ውጭ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ጠቁመው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ለጊዜው የመንግሥትን አቋም ለመግለጽ እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡ የዜጎችንና የፖለቲካ ተንታኞችን ሥጋት በተመለከተም እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ሁሌም ከበድ ስለሚሉ ነገሮችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማየት የግድ ነው ብለዋል፡፡ ባልተረጋገጡ ጉዳዮች ላይ መደምደሚያ ላይ መድረስ አስቸጋሪ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ከዓባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ በተለይም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከተጀመረ ወዲህ ግድቡ ጥቃት እንዳይደርስበት፣ በአሻጥር ግንባታው እንዳይስተጓጎል ወይም መጓተት እንዳይፈጠርበት የሚሰጉ ዜጎች፣ የካርቱም ሚስጥራዊ የጦር መሣርያ ፋብሪካ በእስራኤል መመታቱን ከሰሙ ጀምሮ መንግሥት ብርቱ ጥንቃቄና ዝግጅት ማድረግ አለበት እያሉ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ በውኃ ሀብቷ ላይ የምታካሂዳቸውን የተለያዩ ፕሮጀክቶች እንደምታደናቅፍ የምትጠረጠረው ግብፅ፣ ከሱዳን በተጨማሪ ኤርትራ ውስጥ ምን እያከናወነች እንደሆነ መንግሥት ሊከታተል ይገባዋል ይላሉ፡፡ የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለማዳከም ወይም ለማጥፋት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም ሲሉ ያሳስባሉ፡፡ ኢትዮጵያ ሱዳን ድንበር አጠገብ ታላቁን የኃይል ማመንጫ ግድብ እየገነባች ሱዳን ውስጥ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖችን፣ ሚሳይሎችንና ሮኬቶችን የሚያመርት ሚስጥራዊ የጦር መሣርያ ፋብሪካ መኖሩ በእጅጉ አሳሳቢ ነው ሲሉ ሥጋታቸውንም ይገልጻሉ፡፡
Source: Reporter
 Home

4 comments:

Unknown said...

this is a great challenge, Ethiopian government should strengthen the dialog as well every possibility to protect the land. as they have right to use Nile, they must know we have too. if possible every thing should be finish on the table. how ever, Egyptians and North Sudan should understand there is nothing above rule. besides Ethiopian people has a right to protect them selves with any means. any way the government must get ready.......

dani said...

thise like a ringing tone 4 ethiopiane gov't.and should take care.



Anonymous said...

sudan ayadergum ayibalm,gen bayimokirut yishalachewal

Anonymous said...

The Ethiopia government has to realize how to deal with the situation happening in the region and must go ahead of such situation before any other countries in order to make our country national interest is safe by strengthening the inside and out side spying system.

Post a Comment