Thursday, August 23, 2012

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ስርዓተ ቀብር ዛሬ ተፈፀመ

(አዲስ አበባ ነሃሴ 17/ 2004)--የብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ስርዓተ ቀብር ዛሬ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል በታላቅ ስነ ስርዓት ተፈፀመ። 

Priests conduct ceremony next to casket bearing remains of Patriarch of the Ethiopian Orthodox Church, Abune Paulos, Aug. 23, 2012.
በስነ-ስርዓቱ ላይ ከአገር ውስጥና ከውጭ የመጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡራን ሚኒስትሮች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንት፣ በርካታ የከተማ ነዋሪዎችና ከውጭ የመጡ እንግዶች ተገኝተዋል። ከተለያዩ ገዳማትና አድባራት የተውጣጡ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ የፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ ማርሽ ባንድና ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

በቀብሩ ስነ-ስርዓት ላይ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ጳጳሳትና ሊቃውንተ በተክርስቲያን አባቶች በየአገሮቻቸው ቋንቋ የፀሎት ስነ ስርዓት የከናወኑ ሲሆን ስራዎቻቸውን የሚዘክሩ የተለያዩ ፅሁፎችና የህይወት ታሪካቸው በቅርብ ቤተሰባቸው በንባብ ቀርቧል።  በስርዓተ ቀብሩ ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያወ ሪፓብሊክ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደተናገሩት ብፁዕነታቸው ባለፉት 20 ዓመታት መንግሥት የጀመረውን የልማት ጉዞ ለማሳካት ያለሰለሰ ጥረት ያደረጉ ታላቅ አባት ነበሩ።

በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አገሪቱ በነደፈችው የልማት ስራ ላይ ተሳትፎ እንዲኖራት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ለልማቱ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩ አባት ነበሩ ብለዋል። በሌላ በኩል በውጭ የሚገኙ የአገሪቱ ቅርሶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ረገድና በአገር ውስጥ ያሉ ቅርሶችም በአዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ሰዎችን በማስተባበር ከፍተኛ ስራ መስራታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ተተኪ የቤተክርስትያን አባቶችም የእሳቸውን ፈለግ በመከተል በመንግሥት የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ አገሪቱን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው የልማት ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለመላው ሰብዓዊ ፍጡር ትልቅ አክብሮት ያላቸውና በህዝቦች መካከል መልካም ጉርብትና እንዲኖር የሰሩ ብልህና መንፈሳዊ መሪ ናቸው። የአገሪቱ ህዝቦችና አፍሪካውያን ሰብዓዊ ቀውስ ሲያጋጥማቸው ፈጥነው የሚደርሱና ለህዝቦች ሰላም ሳይታክቱ የሰሩ አባት እንደነበሩ ተናግረዋል።

እኚህ አባት በሰሩት ስራ ዓለም የማይረሳቸው እንደሆኑ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ ለመላው የኦርቶዶክስ ክርስትያንና ቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እንደሚመኙ መልዕክት አስተላልፈዋል። የአዲስ አበባ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ በበኩላቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በአገሪቱ የኃይማኖት መቻቻል እንዲጎለብት ትልቅ ጥረት ያደሩጉ ታላቅ መንፈሳዊ መሪ እንደነበሩ አመልክተው በሞታቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን በከተማዋ ነዋሪዎች ስም ገልጸዋል።

በተለይ የአክራሪነትን ጎጂ ባህል በማስተማርና የትምህርት ዕድል በአገሪቱ እንዲስፋፍ የበኩላቸውን የተወጡ ትልቅ አባት እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡ በአገሪቱ ጧሪና ቀባሪ ያጡትን በመደገፍና በጤናው መሰክ ኤች.አይ.ቪ./ኤድስ በመከላከል ረገድ ያሳዩት ተግባር በተምሳሌት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል። በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የዓለም አብያተ ክርስትያናት ተወካይ ባስተላለፉት መልዕክት እኚህ አባት በአገራት መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በማብረድና ሰብዓዊ ቀውስ ያጋጠማቸውን ሀገራት በመደገፍና በማፅናናት ከፍተኛ ስራ የሰሩ ናቸው።

በተለይ ሱዳን ውስጥ የነበረውን ችግር ለመፍታት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ይሰጡት የነበረው ጠቃሚ አስተያየት ዓለም የሚረሳው አለመሆኑን ገልፀዋል። የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ተወካይ በበኩላቸው ዓለማችን ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥማት ቀድመው የሚደርሱ እውነተኛ አባት ነበሩ።

የእሳቸው ህልፈተ ህይወት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው የኦርቶዶክስ ክርስትያን አማኞች በሙሉ አስደንጋጭ ዜና ነው። አቡነ አቡነ ጳውሎስ ለዓለም ሰላም በጣም አስፈላጊ ሰው ነበሩ በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡
Source: ENA

No comments:

Post a Comment