Saturday, August 18, 2012

ታላቅ የምስጋናና የክብር አቀባበል ለጀግኖች አትሌቶቻችን!

(Aug 17, 2012, Reporter)--ለንደን ኦሊምፒክ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የአገር ጀግኖች ናቸው፡፡ ያሸነፉትም ያላሸነፉትም፡፡ ለውድድሩ የቀረቡትና የተዘጋጁት አገርን በመወከል ነውና፡፡ ውጤቱን ስናይ ደግሞ ሦስት ወርቅ፣ አንድ ብርና ሦስት ነሐስ በማግኘት በዓለም ሃያ አራተኛ በአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ተገኝቷል፡፡ የሚያኮራ ነው፡፡

በእርግጥ የተለያዩ የመወያያ ርዕሶች በኅብረተሰቡ እየተነሱ ናቸው፡፡ ‹‹ከሰባቱ ሜዳሊያዎች አምስቱ በሴት አትሌቶች የተገኙ ናቸው፤ ወንዶቹ የት ገቡ?›› የሚል ጥያቄ ይሰማል፡፡ ‹‹ተጨማሪ ሰባት ሜዳሊያዎችን ማግኘት ይገባን ነበር፤›› የሚሉም አሉ፡፡ ‹‹የታክቲክና የሥልጠና ችግር ነው እንጂ በተጨማሪ ሦስት የወርቅ ሜዳሊያዎች ይገቡን ነበር፤›› የሚሉም አለ፡፡

ለንደን ኦሊምፒክ የሄድነው ለውድድርና ለፉክክር ነው፡፡ በውድድር ማሸነፍና መሸነፍ አለ፡፡ ያሸነፍንባቸው አሉ፤ የተሸነፍንባቸውም አሉ፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ግን የዘራነውን አጭደናል፡፡ ያላጨድነው ያልዘራነውን ነው፡፡

በአጠቃላይ የአፍሪካ ውጤት ሲታይም ዝቅተኛ ነው የሚል አስተያየት እየተሰነዘረ ነው፡፡ መልሱ ግን አፍሪካም ያጨደችው የዘራችውን ነው፡፡ ይልቁንስ አሁን ማተኮር ያለብን ከለንደን ኦሊምፒክ ምን እንማራለን የሚለው ላይ ነው፡፡ በእውነት ምን እንማራለን?

ከሁሉም በላይ የምንማረው ተገቢውን ሥራ ከሠራን በርካታ አትሌቶች ማፍራት እንደምንችል ነው፡፡ ከአበበ ቢቂላ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ተተኪዎችን እያፈራች እያሳተፈች ነው፡፡ ታዋቂ ያልነበሩ አትሌቶች ወደ መድረክ እየመጡ ታዋቂ እየሆኑ ናቸው፡፡

ይህ የሚያሳየን ልዩ ትኩረት ሰጥተን፣ አስፈላጊውን በጀት መድበን፣ በቂ የባለሙያ ኃይል አሰባስበን ከተንቀሳቀስን እጅግ በርካታ ምርጥ አትሌቶች ማፍራት እንደምንችል ነው፡፡ አካሄዳችን ግን በገጠመኝ ሳይሆን ጠንካራና በራዕይ የተደገፈ የአትሌቲክስ ተቋማዊ ግንባታ መሆን አለበት፡፡

በአሁኑ ስፖርት ኮሚሽን በኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ ብሔራዊ የስፖርት አካዳሚ እየሠራ እንዳለው፣ በተጠናከረ መንገድ አትሌቶቻችን በሁሉም ዘርፍ የሚለማመዱበትና የሚሠለጥኑበት የስፖርት ማዕከል ያስፈልጋቸዋል፡፡

የአሜሪካ፣ የቻይና፣ የእንግሊዝና የሩሲያ ውጤት እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው ድብቅና ሚስጥር ሆኖ አይደለም፡፡ በስፖርት ላይ ኢንቨስት ስለሚያደርጉ ነው፡፡ የእነሱን ያህል የገንዘብ አቅም ባይኖረንም አቅማችንን አጠናክረን የምንሄድበት ርቀት ግን ከፍተኛ ነው፡፡ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሕዝብም ለበጀቱ የሚሳተፍበት ነው፡፡  ለለንደን ኦሊምፒክ ተሳታፊ አትሌቶች 46 ሚሊዮን ብር ያወጣ ሕዝብ ለአጠቃላይ ስፖርት ዕድገት በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ሊያወጣ ይችላል፡፡ ለስፖርት ተቋም ግንባታ ስለሆነ፡፡

ሌላው የምንማረው ትምህርት ሥልጠናን የሚመለከት ነው፡፡ የስፖርት ተቋም እናጠናክር ሲባል የመለማመጃ፣ የስታዲዮምና የስፖርት መሣርያዎች አቅርቦትን ማጠናከር ማለት ብቻ አይደለም፡፡ የአመራሮችንና የአሠልጣኞችን አቅምና ብዛት ማጠናከር ማለት ጭምር ነው፡፡

የለንደን ኦሊምፒክ ያስተማረን አንዱ ትልቁ ነጥብ ቢያንስ ሦስት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያጣንበት ምክንያት የአትሌቶች ጉልበት ወይም የፍጥነት ችግር ሳይሆን የአሠለጣጠን ታክቲካዊ ድክመት ነው፡፡ ውጤቱ አሠለጣጠን ላይ ችግር እንዳለ የሚያፀንባርቅ ነው፡፡ መቼ ፍጥነት መቀነስ፣ መጨመርና መወንጨፍ እንዳለባቸው በትክክል አለማወቅና ይኼንን በሚያውቁ አትሌቶች ተበልጦ መገኘትን ያሳየን ነው፡፡

ስለሆነም ማቴሪያል ብቻ ሳይሆን ጭንቅላትን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተምረናል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ለአትሌቲክስ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የስፖርት መስኮች በቂ ጊዜ ተሰጥቶ እንደ ተቋም ለመገንባት ልዩ ትኩረት፣ ልዩ ፖሊሲ፣ ልዩ በጀት፣ ልዩ ሙያና ልዩ አቅም መመደብ ያስፈልጋል፡፡ ይቻላልም፡፡ የተሻለ ውጤት ማግኘትም ይቻላል፡፡ የስፖርት ኢንቨስትመንት ግን የግድ ይላል፡፡

ይህን ሁሉ ስንል ግን መዘንጋት የሌለበት አንድ ዓብይ ሀቅ አለ፡፡ ቢሸነፉም ቢያሸንፉም በዓለም የሚወክሉን አትሌቶቻችን የአገር ጀግኖች ናቸው፡፡ የአገር ጀግኖች ስለሆኑም ታላቅ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ታላቅ ክብር ይገባቸዋል፡፡ ታላቅ ሕዝባዊ አቀባበል ይገባቸዋል፡፡ ሽልማትና ማበረታቻ ከመንግሥትም ሊደረግላቸው ይገባል፡፡

ሲያሸንፉ እየካብን ሲሸነፉ የምናጣጥል ከሆነ ድርጊታችን አትሌቲክስን የማዳከሚያ ትልቅ በሽታና ዕርምጃ ይሆናል፡፡ ሁሉም አገር አሸንፋለሁ ብሎ በተሰለፈበት ሜዳ መሸነፍ ውርደት አይደለም፡፡ ውጤት ሲጠፋም የአትሌቱ ችግር ብቻ አይደለም፡፡ የተቋማት ጭምር ነውና፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ማሸነፍ የቻሉ አትሌቶች ልምዳቸውን እየሰጡ፣ ምክር እየለገሱ፣ ሞራል እየሰጡ ሌሎች እንዲያሸንፉ የማድረግ ሚና ይጫወታሉ፡፡ እነ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ራሳቸው ባይወዳደሩም ሌሎችን በማበረታታትና የአገርን ገጽታ ከፍ በማድረግ እየተጫወቱት ያለው ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ከሜዳ ውጭ የሚያደርጉትም ያስመሰግናቸዋል፡፡

ሁሉም ጀግኖች አትሌቶቻችን ለአገር ኩራትና አለኝታ እንደሆኑ ሁሉ እኛም እንደ ሕዝብ፣ መንግሥትም እንደ መንግሥት ለአትሌቶች አለኝታና መመኪያ ልንሆን ይገባል፡፡ በሞራል መደጋገፍም ለተቋማት ግንባታ ልዩ ሚና ይኖረዋልና፡፡ ስለሆነም ከሁላችንም ለአትሌቶቻችን ምስጋና ይቅረብ፤ የሁላችንም ክብር ይገባቸዋል፡፡  የጀግና አቀባበልም እናድርግላቸው፡፡ ጀግኖች ናቸውና፡፡ ሁሉም!

No comments:

Post a Comment