Sunday, August 05, 2012

መንግሥት በለንደን አውሮፕላን ማረፊያ ዕፅ ሲያዘዋውሩ ስለተያዙት ኢትዮጵያዊት ዲፕሎማት አላውቅም አለ

(Aug 04, 2012, Reporter)--በለንደን ሔትሮ አውሮፕላን ማረፊያ 56 ኪሎ ግራም ካናቢስ ሲያዘዋውሩ ስለተያዙት ኢትዮጵያዊት ዲፕሎማት ጉዳይ መንግሥት ምንም አላውቅም አለ፡፡

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የቪዛ ክፍል ውስጥ የሚሠሩት ወይዘሮ አመለወርቅ ወንድማገኝ 160 ሺሕ ፓውንድ ዋጋ ያለው የካናቢስ ዕፅ ሲያዘዋውሩ ር የተያዙ ሲሆን፣ የሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወር እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ስለድርጊቱ መስማታቸውን ገልጸው፣ ጉዳዩን ገና እያጣሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለጊዜው ከዚህ በላይ ስለጉዳዩ መናገር እንደማይቻል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የ36 ዓመቷ ወይዘሮ አመለወርቅ 56 ኪሎ ግራሙን ካናቢስ ከአዲስ አበባ አየር መንገድ ሲነሱ ከሰው የተቀበሉት መሆኑን ተናግረው፣ የተቀበሉት ዕቃ ግን ሥጋና በርበሬ ነው የሚል እምነት እንደነበራቸው አስረድተዋል፡፡ በለንደን የሚገኘው ፍርድ ቤት የወይዘሮ አመለወርቅን የዲፕሎማቲክ መብት በመግፈፍ ዕፅ በማዘዋወር ወንጀል የሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወር እስራት ፈርዶባቸዋል፡፡ ዳኛውም ለዲፕሎማቷ፣ ‹‹ያለመከሰስ መብት አለኝ በሚል እሳቤ ዕፁን ይዘሽ መገኘትሽ ለክሱ ዋነኛ መነሻ ነው፤ ምን እንደፈጸምሽም ታውቂያለሽ፤›› ብለዋቸዋል፡፡

ወይዘሮ አመለወርቅ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የቪዛ ክፍል ውስጥ እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ ይሠሩ እንደነበር ሲያወቅ፣ ዕፁ የተያዘባቸው ባለፈው ሚያዝያ ወር ከአዲስ አበባ ወደ ለንደን በተጓዙበት ወቅት ነው፡፡ የለንደን አውሮፕላን ማረፊያ የፀጥታ ሠራተኞች የወይዘሮ አመለወርቅ ሦስት ሻንጣዎች ውስጥ ካናቢስ ከበርበሬ ጋር ተቀላቅሎ መያዝ ችለዋል፡፡ ወይዘሮ አመለወረቅ በመጀመርያ ሻንጣዎቹ የእኔ አይደሉም ቢሉም፣ የተነሱት ፎቶግራፍ ማረጋገጫ ሊሆን ችሏል፡፡ በፎቶግራፉ በታየውና በሻንጣው ውስጥ በተገኘው የአንገት ሀብላቸው ሊረጋገጥ ችሏል፡፡

ዳኛው ወይዘሮ አመለወርቅ ስለዕፁ የተለያዩ ውሸቶችን ሲናገሩ እንደነበሩ ገልጸው፣ “ግለሰቧ አፈጮሌ ናት” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ አመለወርቅ የሁለት ልጆች እናት ናቸው፣ እ.ኤ.አ በ2005 ባለቤታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩባቸው ዲፕሎማቷ የ10 እና የ17 ዓመት ልጆቻቸውም በአሜሪካ ይኖራሉ፡፡ የኤምባሲው ሠራተኞች እየተንከባከቧቸው መሆኑም ታውቋል፡፡ ወይዘሮ አመለወርቅ የእስር ጊዜያቸውን ሲጨርሱ ከዲፕሎማሲው ዘርፍ እንደሚሰናበቱ ይጠበቃል፡፡ 
Source: Reporter

Related topic:

No comments:

Post a Comment