Thursday, March 15, 2012

ሠራዊቱ በወሰደው የማጥቃት እርምጃ የኤርትራ መንግሥትና ተላላኪዎቹን የጥፋት ተልዕኮ ማዕከላትን አወደመ

(መጋቢት 6 ቀን 2004 (አዲስ አበባ) --የአገር መከላከያ ሠራዊት በወሰደው የማጥቃት እርምጃ የኤርትራ መንግሥትና ተላላኪዎቹን የጥፋት ተልዕኮ ማዕከላትን ዛሬ ማውደሙን አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ የኢንዶክትሬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ማዕከል ኃላፊ ኮሎኔል ገብረ ኪዳን ገብረ ማርያም ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ሠራዊቱ ማለዳ ላይ ባደረሰው ጥቃት በሦስት ካምፖች ተሰባስቦ የነበረውን ኃይል ለማውደም ተችሏል።

በዚህም ከኢትዮጵያ ድንበር በቅርብ ርቀት ባሉት ራሚድ፣ገላህቤንና ጊምቢ በተባሉ ሥፍራዎች ተሰባስቦ የነበረውን ኃይል ሙሉ በሙሉ አውድሟል።

ሠራዊቱ የኤርትራ መንግሥትና ተላላኪዎቹን የጥፋት ተልዕኮ ለማክሸፍ ተመሳሳይ ድርጊቶችን ለማድረስ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ካልተቆጠበ ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል ኮሎኔል ገብረ ኪዳን አስረድተዋል። በጥቃቱ በርካታ የጥፋት ቡድኑ አባላት እንደተገደሉና ሌሎች ደግሞ እንደተማረኩ ገልጸው፣ዝርዝሩ ወደፊት ይፋ ይደረጋል ማለታቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ ያመለክታል።

የኤርትራ መንግሥት በተለይም ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂ ቀይሶ እንደሚንቀሳቀስና በዚህም በአፋር ክልል በጉብኝት ላይ የነበሩትን ቱሪስቶች ላይ መግደሉንና ማሰቃየቱን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን ዓይነት ድርጊት እንዳይደገም ሁኔታውን ስታጠና መቆየቷንና ለዚህም ተመጣጣኝ ነው የምትለውን እርምጃ መውሰዷን ኃላፊው አመልክተዋል።

ኤርትራ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ለማተራመስ በምታደርገው እንቅስቃሴ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፣በአፍሪካ ኅብረትና በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መወገዟና ማዕቀብ እንደተደረገባት ኢዜአ በዘገባው አስታውሷል።
Source: Ethiopian News Agency 

No comments:

Post a Comment