Tuesday, November 15, 2011

የዳዉሮ ዋካው ኢትዮጵያዊው ``ሞሃመድ ቡዐዚዝ``አረፈ

(ቀን 2011-11-15, Ethiopia)--የኔሰው ገብሬ ይባላል። ዕድሜው ወደ 29 አመት ነው።ሥራው መምህር ነበር።የተወለደው በጂማ ከተማ ዉስጥ ሲሆን የአንደኛም ሆነ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው እዚያው ጂማ ከተማ ነበር።

ከዚያም ወደ ዋካ ከተማ በመምጣት ታላቅ እህቱ ዘንድ ኑሮዉን አደረገ። ከዚያም ወደ መምህራን ኮሌጅ በመግባት በመምህርነት ሰልጥኖ በዳዉሮ ዞን ዉስጥ በተለያዩ ወረዳዎች ዉስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እየተዛወረ በመምህርነት አገልግሏል።

መምህር የኔሰው በመምህርነት ሙያው እጅግ የተከበረ ነበር።መጻህፍት ማንበብና እውቀቱን ለማስፋት የሚያደርገው ጥረት በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ የሚታወቅለት ባህርዩ ነበር። የቋንቋ ችሎታው ወደር አልነበረውም።የኔሰው የትኛዉን የትምህርት ዓይነት ነው የሰለጠነው? በሚባል መልኩ የሁለገብ እውቀት ባለቤት ነበር።


ከአንድ ወር ወዲህ የዳዉሮ ዋካ ህዝብ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄ በየደረጃው ለመንሥስት አቅርቧል። እንዲሁም አላግባብ ግለሰቦች በሥልጣን ዘመናቸው ቦታ ተመርተው፣ቤት ገንብተውና ነግደው ለመጠቀም ሲሉ ብቻ፤ የህዝብን አደራ ወደ ጎን በመተው የወረዳ አስተዳደር እርከን የነበራትን፣አብዛኛውን የወረዳዉን ህዝብ የምታማክለዉን የዋካ ከተማ የወረዳ ርዕሰ ከተማነትን አሳጥተዋል። ስለዚህ ተግባራዊ የሆነ መፍትሄ ይሰጠን አለ ህዝቡ።

መምህር የኔሰው ሳይሆን ጥያቄዉን ያቀረበው፣ያመፀው፣አደባባይ የወጣው የዋካ ከተማና አካባቢው ነዋሪ ህዝብ ነው። አቤቱታ ለበላይ አካል አቅርባችሁብናል፤አሳጣችሁን፤የሥልጣን ዕድሜያችንን አሳጠራችሁብን፤አርፋችሁ ለምን አትገዙልንም...የሚሉ ባልሥልጣኖች የህዝብ ተወካይ የሆኑትን ያገር ሽማግሌዎችን በሙሉ ሰብስበው አሰሩ። አመጹን አቀጣጥላችሁታል በሚል በርካታ ወጣቶችም ታጎሩ።

መምህር የኔሰውም አስተባባሪ ነበርክ በሚል ብቻ ያለአንዳች መረጃ ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በቁጥጥር ሥር እንዲቆይ ተደርጎ፤ ምንም መረጃ ሊቀርብበት ባለመቻሉ ከሽማግሌዎች ጋር አብሮ ተፈቷል ።

የሰዉ በደልና ስቃይ የሚያመው፤ለፍትህና ለነፃነት የቆመ፤ ሁልጊዜ በየመድረኩ ስለ ዴሞክራሲና እኩልነት ይሚዘምር አገር ወዳድ ወጣት ነበር መ/ር የኔሰው።በኢትዮጵያ ዉስጥ የተንሰራፋው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲወገድ፤ያለአግባብ በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀመው እስር፣እንግልት፣ዱላ የመሳሰሉ ነገሮች እንዲቆሙ፤ በየደረጃው የሚገኙት ባልሥልጣኖች የህዝብ ወገንተኝነት እንደሚጎድላቸው በአንክሮ ተናግሯል።

በ2011-11-11 ማለትም ባለፈው ዓርብ ዕለት በእስር ቤት የነበሩት ጓደኞቹ ፍርድ ቤት የሚቀርቡበት ቀን ነበርና ሁኔታዉን ለመከታተል መ/ር የኔሰውም ማረቃ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀረበ። አላግባብ ታስረው ስለነበር ይፈታሉ የሚል ግምት ህዝቡ ነበረው። ለካስ ዳኛው ፍታቸው ተብለው አልታዘዙ ኑሯል። ሌላ የጊዜ ቀጠሮ ይሰጣሉ ዳኛው። መቼም ዳኛ ናቸው እንበልና ነው።

በዚህ ሁኔታ ፍርድ ቤት ቀርበው ሲከታተሉ የነበሩ የእስረኞቹ ቤተሰቦች በጣም ገርሟቸው ታሳሪዎቹን አይዟችሁ ምንም አትሆኑም፤ጀግኖቻችን ናችሁ፣ነገ ይህ ቀን ታሪክ ይሆናል ብለው አፅናንተዋቸው ታሳሪዎቹ ወደ ወህኒ ቤት ወረዱ።ከዚህ በኋላ ነው መ/ር የኔሰው በሃገሪቱ እውነትና ፍትህ እንደሌለ፤ ነፃነትና ዴሞክራሲ በዚህ ሥረዓት በፍፁም የማይታሰቡ ነገሮች መሆናቸው ፍንትው ብሎ የታየዉና ለነፃነት ትግሉ ወጣቱ ትውልድ አርማዉን እንዲያነሳ አሳስቦ ራሱን ለመሰዋት የወሰነው።

በህይወቱ ላይም ዉሳኔ የሰጠው እነዚህና የመሳሰሉትን በደሎች በሌላው የህብረተሰብ ክፍል ላይ መፈፀሙ ተገቢነት እንደሌለው በአንክሮ ስለሚያምን ነበር። እውነተኛ የህዝቡን ልጆች ያለምክንያት አሰሩዋቸውት። እሱ ቀድሞ ከእስር በመፈታቱ ምክንያቱን ጠየቃቸው።እንኳንና የታሰረበትን ምክንያቱን ሊነግሩት ቀርቶ ያሰረህ ይሄ ክፍል ነው፣ ወይም እኔ ነኝ፤ የሚል አካል ማጣቱ እጅግ አንገበገበው።

ከዚያም ከፍ/ቤት ምልስ ጉዞዉን ወደ አስተዳደር ጽ/ቤት አደረገ። እሱ አስተዳደር ጽ/ቤት ግቢ ሲደርስ ከፍተኛ የክልል ባለሥልጣኖችን ጨምሮ የዳዉሮ ዞን አመራሮች፤ የሁሉም ወረዳ አስተዳደር ተወካዮች በሚወያዩበት ቀርቦ፤አለምክንያት እንደእንስሳ መታሰሩ ሳያንስ ያሰረዉን አካል እንኳ ለማወቅ መብት ማጣቱ እጅግ እንዳንገበጋበው፤በዚህ ሥርዓት እንኳንና የግለሰብ የህዝብ ነፃነት ብሎ ነገር እንደሌለ ማረጋገጡን፤ለልማት ሳይሆን የሚወያዩት ህዝብንና አገርን ለመበደል ብሎም ራስን ማገልገል የዘወትር ተግባራቸው መሆኑን፤ህዝብ ነፃነት እንደሌለው ማረጋገጡን በኃይለ ቃል ከተናገረ በኋላ፤ የዋካ ከተማ ህዝብ በአመፅ ወቅት በአደባባይ ሲያስተጋባ የነበረዉን መፈክር እንደገና ብቻዉን አስተጋባ።

ከዚያም አስተዳደር ጽ/ቤቱ ግቢዉን ሳይለቅ ቢሮው በራፍ ላይ ብዙ ሰዎች እያዩት ቤንዚን በራሱ ላይ አርከፍክፎ ክብሪት ጭሮ ራሱን በእሳት ለኮሰው። በአቅራቢያው የነበሩ ሰዎች በንግግሩና በመፈክሩ ተመስጠው ያዳምጡት የነበሩ ሁሉ አዝነውና ደንግጠው እሳቱን ለማጥፋት ሣር፣ቅጠል፣አፈር፤ውሃ ያገኙትን ሁሉ ተጠቀመው እሳቱን በማጥፋት እሱን ለማትረፍ ተሯሯጡ።

ህክምና እንዲያገኝ ወደ ተርጫ ሆስፒታል ቢወስዱትም የኔሰው ገብሬ አልተረፈም።ትናንት ሰኞ ቀን ረፋዱ ላይ በሆስፒታሉ ዉስጥ ህይወቱ አልፏል። የዳዉሮው የነፃነት አርበኛ መ/ር የኔሰው ገብሬ ለዴሞክራሲና ለፍትህ እንዲሁም ለህዝብ የበላይነት ሲል እነሆ ሁለተኛው ሞሃመድ ቡዐዚዝ ሆነ። በዚህ ዓይነት ከዋካ የተነሳው እሳት የት ይደርስ ይሆን? እንጠብቅ!
Source: http://addisvoice

No comments:

Post a Comment