Sunday, October 23, 2011

በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩት ስዊድናውያን ጋዜጠኞች ይቅርታ ጠየቁ

(23 October 2011, ሪፖርተር)--በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል በቁጥጥር ሥር ውለው የታሰሩት ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞች "ሕጋዊ ሰነድ ሳይኖረን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰን በመግባታችን፣ የኢትዮጵያን መንግሥትና ሕዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን፤" ሲሉ፣ ከእነሱ ጋር በቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ ሁለት የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ታጣቂዎች አንደኛው ወታደር  በመሆኑ ትንሽ የፈጸመው ነገር እንዳለ፣ ሁለተኛው ግን የፈጸመው ነገር እንደሌለ ጥቅምት 9 ቀን 2004 .. ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ይቅርታ የጠየቁትና ወታደር ሆነው ካደረጉት ውጭ ሌላ ምንም ነገር እንዳላደረጉ የተናገሩት፣ ጋዜጠኛ መርቲን ካርል ሺብዬ፣ የፎቶ ጋዜጠኛው ጆሃን ካርል ፐርሰን፣ የኦብነግ ታጣቂዎች የሆኑት አብዲወሊ መሀመድ እስማኤልና ከሊፍ ዓሊ ዳሂር ጥቅምት 9 ቀን 2004 .. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ልደታ ምድብ ችሎት ቀርበው፣ በቀረበባቸው ክስ ላይ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሲሰጡ ነው፡፡  

ፍርድ ቤቱ በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የተመሠረተውን ክስ ለስዊድናዊያኑ የእንግሊዝኛ አስተርጓሚ፣ ለታጣቂ ሶማሌዎቹ ሶማሊኛ አስተርጓሚ በመመደብ፣ ክሱ እንዲተረጐምላቸው ካደረገ በኋላ፣ ክሱን ለችሎቱ በንባብ አሰምቷል ተጠርጣሪዎቹ የዕምነት ክሕደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተራ በተራ መጠየቅ ጀመረ፡፡

በቅድሚያ የተጠየቁት ሁለቱ የኦብነግ ታጣቂዎች ሲሆኑ፣ አብዲወሊ መሀመድ እስማኤል "ድርጊቱን አልፈጸምኩም" ሲል፣ ከሊፋ አሊ ዳሂር "የኦብነግ ወታደር ነኝ፤ ወታደር በመሆኔ ትንሽ የፈጸምኩት ነገር አለ" በማለት የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ፡፡

በኢኮኖሚክስ ሒስትሪ ሁለተኛ ዲግሪ፣ በፖለቲካል ሳይንስና በጆርናሊዝም የመጀመርያ ዲግሪ ያለውና ጥቅምት 5 ቀን 2004 .. በማረሚያ ቤት ሆኖ 31 ዓመቱን ያከበረው ጋዜጠኛ መርቲን ካርል ሺብዬ በሰጠው የዕምነት ክህደት ቃል፣ "እኔ የስዊድን ጋዜጠኛ ነኝ፡፡ ወደ አካባቢው የሄድኩት ለዘገባ ነው፡፡ የሽብር ወንጀል ተሳታፊም ደጋፊም አይደለሁም፡፡ ጥፋተኛም አይደለሁም፤ ነገር ግን ሕጋዊ የሆነ የመተላለፊያ ሰነድ ሳይኖረኝ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሼ በመግባቴ የኢትዮጵያ መንግሥትንና ሕዝብን ይቅርታ እጠይቃለሁ፤" ብሏል፡፡

የሦስት ዓመት የሕትመት ፎቶግራፍ ትምህርት የተከታተለው 29 ዓመት ዕድሜ ያለው የፎቶ ጋዜጠኛው ጆሃን ካርል ፐርሰንም፣ እንደ ጓደኛው ጥፋተኛ አለመሆኑን በመግለጽ፣ ያለ ሕጋዊ ሰነድ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በመግባቱ ግን የኢትዮጵያን መንግሥትንና ሕዝብ ይቅርታ ጠይቋል፡፡

ጋዜጠኛውና ፎቶግራፈሩ ጥቁር ሙሉ ልብስ በነጭ ሸሚዝ ለብሰው በነጠላ ጫማ የቀረቡ ሲሆን፣ የዕለቱን ችሎት ለመከታተል የጋዜጠኛ መርቲን ካርል ሽብዬ እናት፣ እጮኛውና አባቷ፣ የፎቶ ጋዜጠኛው ጆሃን ካርል ፒርሰን አባት ተገኝተው ችሎቱን ተከታትለዋል፡፡ 

የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞችና በርካታ ታዳሚዎች የተሞላው ችሎት፣ ሥራውን የጀመረው ከጧቱ 310 ሰዓት ላይ ነው፡፡

ችሎቱ እንደተሰየመ፣ ዓቃቤ ሕግ ቀደም ብሎ ባቀረበው ክስ ላይ አንዳንድ ግድፈቶችን ማስተካከሉን በመግለጽ እንዲቀየርለት ሲጠይቅ፣ ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን ጠበቆች አማካረ፡፡ ጠበቆቹ ቀደም ብሎ ቀርቦ በነበረው ክስ መሠረት መቃወሚያ አዘጋጅተው መቅረባቸውን በመግለጻቸው፣ ፍርድ ቤቱ የክስ መስማት ሒደቱ ቀድሞ በቀረበው ክስ እንዲቀጥል አዘዘ፡፡

በክሱ ላይ ጠበቆች ባቀረቡት መቃወሚያ ዓቃቤ ሕግ ደንበኞቻቸው ተያዙ የሚለው አንድ ጊዜ በውጊያ ላይ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ ማለቱ እርስ በርሱ እንደሚጋጭ፣ ተነጣጥሎ የቀረበው ክስ በአንድ ተጠቃሎ መቅረብ እንዳለበት፣ ሰጡ  የተባለው ድጋፍ ምን እንደሆነ አለመገለጹን ጠቁመው፣ ዓቃቤ ሕግ በግልጽ ማስተካከል ካልቻለ ደንበኞቻቸው ተከላከሉ ቢባል መከላከል እንደሚያስቸግራቸው በመግለጽ እንዲስተካከልላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

  ሌላው ጠበቆች ያቀረቡት ተቃውሞ፣ ደንበኞቻቸው የተከሰሱበት የፀረ ሽብር ሕግ አዋጅ ቁጥር 652/2001 እና የተጠቀሰባቸው የወንጀል ሕግ አብሮ የማይሄድ መሆኑን በመጠቆም፣ በአማራጭ ክስ መቅረብ ስለሌለበት እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በክስ 3 እና 4 ላይ ባቀረበው ዝርዝር ሁኔታ ላይ "የተለያዩ ዘዴዎች ይላል" የተለያዩ የሚለው ካልተጠቀሰ ለመከላከል አስቸጋሪ እንደሚሆን ጠበቆቹ አመልክተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ የወንጀሉ ድርጊት ውስብስብ መሆኑን ከገለጸ በኋላ፣ ድርጊቱን በቀጣይ የፍርድ ቤት ሒደት በማስረጃ የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጿል፡፡ በተለይ ጋዜጠኞቹ (የስዊድን ጋዜጠኞች) በአሸባሪነት ከተፈረጀው ኦብነግ ጋር ግንኙነት በመፍጠር እንግሊዝ ሄደው ከአሸባሪ ቡድኑ ቃል አቀባይ ጋር ግንኙነት በመፍጠርና ዓላማውን ለመደገፍ መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡ ወደ ስዊዲን፣ ከዚያም ወደ ኬንያ፣ ከኬንያ ወደ ሶማሊያ በመግባት ከኦብነግ ተዋጊዎች ጋር ከተገናኙ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን በመጥቀስ፣ የነበራቸውን ተሳትፎ በሚመለከት በማስረጃ የሚያረጋግጥ መሆኑን አብራርቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሁለቱ ተከራካሪዎች የቀረበውን የተቃውሞ አስተያየት ካደመጠ በኋላ፣ ለአሥር ደቂቃ እረፍት ወስዶ በመመለስ በሰጠው ብይን፣ ጠበቆች ያቀረቡትን መቃወሚያ እንዳልተቀበለው ገልጾ፣ ተጠርጣሪ ተከሳሰቹ ፈጽመዋል የተባለው ድርጊት ውስብስብ ከመሆኑ አንፃር፣ ዓቃቤ ሕግ በማስረጃ የሚያረጋግጠው መሆኑን፣ ዓቃቤ ሕግ በማስረጃው ማረጋገጥ ካልቻለ ውድቅ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለጥቅምት 21 ቀን 2004 .. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ አብቅቷል፡፡

በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በሰኔ ወር መጨረሻ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞችና የኦብነግ ታጣቂ የነበሩ ሁለት የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች ላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ መመሥረቱንና የክሱን ዝርዝር ጳጉሜን 6 ቀን 2003 .. በወጣው ዕትማችን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
Source: ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment