Sunday, October 23, 2011

ኢሳያስ አፈወርቂ የቀይ ባሕር አፋርን ዘር በማጥፋት ወንጀል ክስ እንዲመሠረትባቸው ተጠየቀ

(23 October 2011, ሪፖርተር)--ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና ግብረ አበሮቻቸው በኤርትራ ቀይ ባሕር አፋር ሕዝብ ላይ በፈጸሙት አሰቃቂ ድርጊት፣ በዓለም አቀፍ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ለመመሥረት የሚያስችል ሰነድ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) መቅረቡን የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት አስታወቀ፡፡

የቀይ ባሕር አፋር ሕዝብን ከኤርትራ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት የትጥቅ ትግል በማካሄድ ላይ የሚገኘው ድርጅቱ፣ ባለፈው ሰኞ በአፋር ክልል በሰመራ ከተማ  ባካሄደው 3 ሕዝባዊ ኮንፈረንስ ላይ እንደገለጸው፣ በሰብዓዊ መብት ዙርያ ከሚሠራ ካንጎ አፋር ከሚባል ካናዳ ውስጥ ከተመሠረተ ተቋም ጋር በጋራ በመሆን፣ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና ተባባሪዎቻቸው በአፋር ሕዝብ ላይ በፈጸሙት የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ለመመሥረት የሚያስችል በቂ ማስረጃዎች ተሰባስበዋል፡፡ የሰነዱ የመጀመርያ ሪፖርትም ለተባበሩት መንሥታት ድርጅት ቀርቧል፡፡ 

በዚህ ኮንፈረንስ 3,500 በላይ የቀይ ባሕር አፋር ተወላጆች የተገኙ ሲሆን፣ የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ኢብራሂም ሐሮን ሐሰን፣ "ትግል በማድረግ ላይ ያሉ ሌሎች ድርጅቶች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማረጋገጥ ነው፡፡ እኛ ሕዝባችን በአደጋ አፋፍ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ህልውናውን ለማረጋገጥ ነው የምንታገለው፤" ብለዋል፡፡  

አቶ ኢብራሂም እንዳሉት፣ የኤርትራ መንግሥት በሚከተለው የዘር ማጥፋት ፖሊሲ መሠረት የቀይ ባሕር አፋሮችን ከቀያቸው በማፈናቀልና በማባረር ሌሎችን እያሰፈረበት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም የቀይ ባሕር አፋር ህልውና ለመታደግ ጎረቤት ሕዝቦችና መንግሥታት እንዲሁም ደግሞ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነው የአፋርና የካናዳ ወዳጅነት ማኅበር (Cango Afar) ፕሬዚዳንት ዶክተር ዋረን ክሬኤትስ በበኩላቸው፣ ወደ አካባቢው አምስት ጊዜ መምጣታቸውን ገልጸው፣ ዕውቅ በሆነ ባለሙያ ጉዳዩን አስጠንተው ሰነዱ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ የድርጅቱን ምላሽ እየተጠባበቁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩን በመከታተል ላይ የሚገኙት ካናዳዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ፕሮፌሰር ዮሴፍ ማግኔታ በኮንፈረንሱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስና አንዳንድ ተባባሪዎቻቸው የኤርትራ ባለሥልጣናት በቀይ ባሕር አፋር ሕዝብ ላይ እየፈጸሙት ያለው የማሳደድና የዘር ማጥፋት ወንጀል እጅግ በጣም ዘግናኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ክሱ በቅርቡ በሄግ በሚገኘው የዓለም አቀፍ ወንጀለኛ ፍርድ ቤት ለማቅረብ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከበቂ በላይ የማስረጃ ሰነድ መሰብሰቡንና ለተመድ መቅረቡን አክለው ገልጸዋል፡፡

የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ኢስማኢል ዓሊ ሴሮ በበኩላቸው፣ በመድረኩ በእንግድነት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ የኤርትራ መንግሥት በቀይ ባሕር አፋር ሕዝብ ላይ እየተከተለው ያለው የጥፋት ፖሊሲን አውግዘው፣ ድርጅቱ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥልበት አሳስበዋል፡፡

በታህሳስ 1991 የተመሠረተው የኤርትራ ቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ እስከ ሐሙስ ድረስ ሦስተኛ ድርጅታዊ ጉባዔውን ያካሄደ ሲሆን፣ አቶ ኢብራሂም ሐሮን ሐሰንን በድጋሚ ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡ አራት አዳዲስ አባላትን ጨምሮ 37 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና 11 ሥራ አስፈጻሚ አባላትም ተመርጠዋል፡፡

የድርጅቱ ውጭ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊና የአዲስ አበባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነስረዲን አሕመድ ዓሊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጉባዔተኞቹ በድርጅቱ አመራር የሕዝቡን ሕልውና ለማረጋገጥ ዕርምጃ እንዲወሰድ ሙሉ ኃላፊነት የሰጥ ሲሆን፣ በተለይ ወታደራዊ ክንፉ የበለጠ እንዲጠናከርና በኤርትራ መንግሥት ላይ ተመሳሳይ የትጥቅ ትግል  ከሚያካሂዱ ሌሎች የኤርትራ አማፅያን ጋር አብሮ እንዲሠራም ጠይቀዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የድርጅቱ ጉባዔ በተጠናቀቀበት ባለፈው ሐሙስ የድርጅታዊ ወታደራዊ ኃይል ከኤርትራ ብሔራዊ መድን ድርጅት ጋራ በመሆን፣ በዛላምበሳ አቅራቢያ ከርመድ በተባለው አካባቢ በሚገኘው 27ኛው የኤርትራ ብርጌድ ላይ ጥቃት መፈጸሙን፣ የቀይ ባሕር አፋር ዲሞክራሲያዊ ድርጅት የሚድያ ኃላፊ አቶ ያሲን አብደላ ተናግረዋል፡፡ በዚሁ ጥቃት 12 የኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን 15 መቁሰላቸውንና ሁለት ደግሞ መማረካቸውን የድርጅቶቹ የጋራ መግለጫ ያመለክታል፡፡
Source: ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment