Sunday, October 30, 2011

‹‹ማንም ሰው [ይዞታዬ ነው ብሎ] መሬትን ከንብረት ጋር ቀላቅሎ መሸጥ አይችልም›› አቶ ደሳለኝ አምባው፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ

(Sunday, 30 October 2011,ሪፖርተር)--የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሰንበቻውን የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ ያወጣው አዋጅ በኅብረተሰቡ ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

በኢትዮጵያ 1986 .. ጀምሮ የሊዝ ሥሪት ተግባራዊ መሆን በመጀመሩ ለኅብረተሰቡ አዲስ ጉዳይ ባይሆንም፣ አዲሱ አዋጅ ነባር ይዞታዎችንም በሊዝ ሥሪት የሚገቡበት አግባብ መፍጠሩ መነጋገሪያነቱን ከፍ አድርጎታል፡፡ ይህንን በተመለከተ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታን አቶ ደሳለኝ አምባውን ውድነህ ዘነበ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- 1994 .. የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣ አዋጅ መኖሩ ይታወቃል፡፡ ሰሞኑን ይህንን አዋጅ የሚሽር አዲስ አዋጅ ወጥቷል፡፡ የዚህ አዋጅ መውጣት በዋናነት ያስፈለገው ለምንድነው?

አቶ ደሳለኝ፡- አሁን ከፀደቀው በፊት የነበረው አዋጅ በሥራ ላይ ሲተረጎም ብዙ ክፍተቶች ነበሩበት፡፡ የተፈጠሩትን ክፍተቶች በሙሉ ለመድፈን የተዘጋጀ ነው፡፡ በነገራችን ላይ መነጋገር ያለብን አዲሱ አዋጅ ከመዘጋጀቱ በፊት የከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ሰነድ ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህ ሰነድ ላይ በከተማ መሬቶች ላይ ክፍተቶች ተብለው የተቀመጡ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህም የፖሊሲ፣ የሕግ ማዕቀፍና የአቅም ግንባታ ክፍተቶችን ክልሎችን ባሳተፈ መልኩ ለይተናል፡፡ ከክልሎች 62 ባለሙያዎችን በየካቲት 2003 .. መርጠን ከአዲስ አበባ አስተዳደር ባለሙያዎች ጋር ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በማስገባት አወያይተናል፡፡ የከተማ መሬት ክፍተቶችን፣ ከልምዶቻቸው የፖሊሲ አቅጣጫው ክፍተቶች ካሉበት፣ ክፍተቶቹን ለማስወገድ ስትራቴጂ ስለመንደፍ፣ ስልት የመንደፍ ሥራ፣ የአቅም ግንባታና የሕግ ማዕቀፍ ክፍተቶችን ለይቶ የሚያስቀምጥ ስትራቴጂ ነው የተዘጋጀው፡፡ ሰነዱም በየደረጃው ባሉ አካላት ፀድቆ ከዚያም እንደ አገር ፀድቋል፡፡ የባለሙያዎች ቡድኑ ሌት ተቀን ሠርቶ ነው ይህንን ሰነድ ያዘጋጀው፡፡ በዚህ ሰነድም በየደረጃው ሕዝብ ተወያይቶበታል፡፡ በየከተሞቹ አወያይቶ ሐሳብ አሰባስቦበታል፡፡ በረቂቁ ላይ ሕዝብ ተወያይቶበታል፡፡ ከዚህ በመነሳት ነው አዲሱ አዋጅ የተዘጋጀው፡፡ እናንተም ግንቦት ውስጥ በዚህ ሰነድ ላይ ኮንፈረንስ መካሄዱን ተከትሎ የቀድሞውን የሊዝ አዋጅ ‹‹አወዛጋቢው የሊዝ አዋጅ በአዲስ ሊተካ ነው›› ብላችሁ ጽፋችኋል፡፡ አዲሱ አዋጅ ሲፀድቅ ሕዝብ እንዳልተወያየበት አስመልስላችሁ ነው ባለፈው ዕትም የጻፋችሁት፡፡

ሪፖርተር፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደተለመደው የሊዝ አዋጁን ለቋሚ ኮሚቴ ሳይመራው ነው እንዳለ ተቀብሎ ያፀደቀው፡፡ ለኮሚቴ ቢመራ ኖሮ ሕዝቡ በአዋጁ ረቂቅ ላይ ለመወያየት አጋጣሚው ይፈጠርለት ነበር፡፡ ለዚህ ነው ለውይይት ሳይቀርብ ፀደቀ የተባለው፡፡

አቶ ደሳለኝ፡- ከስትራቴጂክ ሰነዱ ጋር በሊዝ አዋጁ ረቂቅ ላይ ሕዝብ አወያይተናል፡፡ በሕዝብ አስተችተናል፡፡ በቂ ላይሆን ይችላል፡፡ ግን እኔ ራሴ በተደጋጋሚ በሚዲያ ቀርቤ ማብራርያ ሰጥቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሕዝብን በምን መንገድ ነበር ለውይይት የጠራችሁት?

አቶ ደሳለኝ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ በየከተሞቹ ሐሳብ ሊሰጡ የሚችሉ ሰዎች ናቸው እንዲጠሩ የተደረገው፡፡ አልፎ አልፎ በዚህ ዙርያ ያሉና የሚሠሩ ሰዎች ናቸው እንዲመጡ የተደረጉት፡፡ ምናልባት በቂ ላይሆን ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለድርሻ አካላትን ማለት ነው?

አቶ ደሳለኝ፡- አዎ፡፡ ግን በቂ አይደለም፡፡ ግንዛቤ ፈጠራው አሁንም በደንብ መሠራት አለበት፡፡ የመሬት ጉዳይ ነው ሁሉንም ሰው ይነካል፡፡ ሰፊ ውይይት ላይሆን ይችላል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አጣዳፊ አዋጅ በመሆኑ ነው በፍጥነት አንዲፀድቅ የተደረገው፡፡ ሥራው በአፋጣኝ ሊተገበር ስለሚገባ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ቀደም ሲል በተለያዩ መድረኮች በረቂቅ አዋጁና በፖሊሲው ዙርያ ውይይት እንደተረገበት ታሳቢ በማድረግ ነው አዋጁን ያፀደቀው፡፡

ሪፖርተር፡- አጣዳፊ ነው ሲባል?

አቶ ደሳለኝ፡- አጣዳፊ የሚያደርገው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ድርጊት በልማት ላይ ተፅዕኖ የሚያደርግ ነው፡፡ መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች በዚህ ላይ ሰፊ ሥራ እየሠራ ነው፡፡ በየከተሞች በርካታ የማጥራት ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ መዋቅሩን በማጥራት፣ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው ያለው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ወደ ተግባር እየተገባ ነው፤ ለዚህ ነው አጣዳፊ የሆነው፡፡ ምክር ቤቱ አጣዳፊነቱን ተረድቶ ነው ያሳለፈው፡፡ በፊት የተሠራውን ሥራ ግምት ውስጥ በማስገባት ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሰነዱ ያስቀመጣቸው ክፍተቶች የትኞቹ ናቸው?

አቶ ደሳለኝ፡- አንዱ ክፍተት የከተማ መሬትን በጨረታ፣ በድርድርና በስጦታ መስጠት የሚለው ነው፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮች ይታወቃሉ፡፡ አንዱ መሬት ነው፡፡ ሌላው ግዢ ነው፡፡ ሌላው ግብር አካባቢ ነው ያለው፡፡ አንዱ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ መሬት እንደመሆኑ በድርድር መሬት መስጠትን አስቀርቷል፡፡ አሁን የከተማ መሬት ሙሉ ለሙሉ በጨረታ ብቻ ነው ለልማት የሚውለው፡፡ አሁን ሽልማት፣ ድርድር የሚባል ነገር የለም፡፡ በልዩ ሁኔታ ምደባ ይካሄዳል፡፡ ምደባዎቹ ተዘርዝረዋል፡፡ እነሱም የመንግሥት ሕንፃዎች ግንባታ፣ የልማት ተቋማት፣ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ፣ አሁን በቅርብ በይፋ የሚጀመረው የቁጠባ ቤቶች ግንባታ ናቸው፡፡ የቁጠባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ኅብረተሰቡ 40 በመቶ ቆጥቦ 60 በመቶ ደግሞ ከባንክ ተበድሮ ቤት የሚሠራበት ነው፡፡ በዚህ አግባብ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የቤት ባለቤት የሚሆኑበት አሠራር ስለሚኖር ተደራጅተው የሚመጡ ሰዎች ቦታ በምደባ የሚያገኙበት አሠራር ይኖራል፡፡ ሌሎች የግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ የዕምነት ተቋማትና ለራስ አገዝ የሚሠሩ የልማት ሥራዎች በምደባ ቦታ ያገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በክልል ፕሬዚዳንት ወይም በከተማ ከንቲባዎች እየታየ ለካቢኔ የሚመሩ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች ቦታ በልዩ ሁኔታ ይወሰንላቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ እኮ ለክልል ፕሬዚዳንቶችና ለከንቲባዎች የመሬት ጥያቄ ቀርቦ በካቢኔ ሲወሰን ድርድር ማለት አይደለም እንዴ?

አቶ ደሳለኝ፡- እነዚህ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም እንዳሉት ፕሮጀክቶች ሳይሆን መንግሥት ለሚያወጣቸው ፕሮጀክቶች ለምሳሌ እንደ ማዳበርያ ፋብሪካና እንደ ስኳር ፋብሪካ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የትምህርትና የጤና ተቋማትን የሚገነቡ ባለሀብቶችስ?

አቶ ደሳለኝ፡- አንድ ባለሀብት ዩኒቨርሲቲ ልገንባ ብሎ ይመጣል፡፡ የሚስተናገደው በጨረታ ብቻ ይሆናል፡፡ በቦታው ላይ ባለሀብቱ ብቻውን የሚወዳደር ሊሆን ይችላል፡፡ ተወዳዳሪ ከሌለ ባለሀብቱ በልዩ ሁኔታ ቦታውን እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በሽልማት ቦታ መስጠት በአዋጅ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ በአገሪቱ በየጊዜው የሚከሰቱ ብሔራዊ ጀግኖች መሬት አይሸልሙም ማለት ነው?

አቶ ደሳለኝ፡- ሽልማት መሬት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ሌሎች ሽልማቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሽልማት መኖሩ አይቀርም፡፡ ዝም ብሎ በየአካባቢው ሽልማት እየተባለ ያለውን ውስን ሀብት ማባከን ተገቢ አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው ሊገባው የሚገባው መሬት ውስን ሀብት ነው፡፡ ልንጠብቀው ይገባል፡፡ ስለዚህ ይህንን ለመጠበቅ ጠንከር ያለ ሕግ ወጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የሊዝና የነባር ይዞታ የሚባል የመሬት ስሪት ነበር፡፡ የእርስዎ ሚኒስቴር መሥርያ ቤት አንድ ደንብ አውጥቶ እነዚህን አሠራሮች ወደ ሊዝ አሠራር ብቻ ለማስገባት አቅዷል፡፡

አቶ ደሳለኝ፡- አሁን በኢትዮጵያ ወደ 900 ከተሞች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ በሊዝ ይተዳደራሉ ማለት አይደለም፡፡ ደረጃ በደረጃ ነው፡፡ አሁን 100 ከተሞች በሊዝ የሚተዳደሩ አሉ፡፡ ደንቡ ሲወጣ ክልሎቹም ከዚህ አዋጅ ተነስተው ደንብ ያወጣሉ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ተግባራዊ የሚሆነው ክልሎች የራሳቸው ሥልጣን ስላላቸው ደንብ ያወጣሉ፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ መነሻነት ማለት ነው፡፡ ወደፊት ሁለት ሥርዓት ይኖራል፡፡ የይዞታና የሊዝ፤ አሁን እነዚህ ለቀጣይ አራት ዓመታት ይቀጥላሉ፡፡ አቅም ባላቸው ከተሞች ማለት ነው፡፡ በሁሉም ከተሞች አንድ ጊዜ ተግባራዊ አይደረግም፡፡ በአዲስ አበባ ሊዝም ነባር ይዞታም ይቀጥላል፡፡ እስከ አራት ዓመት ጊዜ፡፡ ምክር ቤቱ ደንቡን ሲያፀድቅ ቀጣዩ ሒደት የሚወሰን ይሆናል፡፡

አሁን ያለው ዓለም አቀፍ ተሞክሮ የሚያሳየው የሊዝ ሥርዓት ጠቃሚ መሆኑን ነው፡፡ ለቀሪው ትውልድም በማሰብ፡፡ ወደ ሊዝ ሥርዓት ሙከራው ሁሉም መግባቱ አይቀርም፡፡ አሁን መጀመር አለበት፡፡ ለመጀመር ነው ዝግጅትና ልዩ ሁኔታን ማስቀመጥ ያስፈለገው፡፡ መሻሻጥ ሲኖር፣ መብት ማስተላለፍ ሲኖር፣ በዚህ ጊዜ ወደ ሊዝ ሥርዓት መሸጋገር ይኖራል፡፡ አንዱ ልዩ ሁኔታ በመሻሻጥ ወቅት የሚፈጠረው የሊዝ ሥርዓት ውስጥ መግባት ነው፡፡ ሁለተኛው በሕገወጥ መንገድ የተያዘ ቦታ ይኖራል፡፡ ኢንቨስት ተደርጎበት ወደ ሕጋዊ ሥርዓት እንዲገባ ሲደረግ ወደ ሊዝ ሥርዓት እንዲገባ ይሆናል፡፡ በሚመለከተው ክልልና ሕግ ውሳኔ ወይ መቀማት ወይ ሕጋዊ መደረግ አለበት፡፡ ሕገወጡ ሕጋዊ ሊሆን የሚችለው ክልሎቹ በሚያወጡት ደንብ ነው፡፡ ሕጋዊ ሊሆን የሚችለው ኢንቨስትመንት ወጥቶበታል፣ ከከተማው ማስተር ፕላን ጋር አይጋጭም፣ የሕዝብን ጥቅም አይቃረንም ሲሉ ሕጋዊ ሆኖ ሊዝ ሥርዓት ውስጥ ይገባል፡፡ ሌላኛው ልዩ ሁኔታ ነባር ይዞታ ያለው ከአጠገቡ ያለውን በሊዝ ቢይዝና ቀላቅሎ ኢንቨስት ቢያደርግ ሁለቱም ወደ ሊዝ ሥርዓት ይገባሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- በውርስ ካልሆነ በስተቀር በሸያጭ ነባር ይዞታ ለሦስተኛ ወገንን ከተላለፈ ይዞታው ወዲያውኑ ወደ ሊዝ ሥርዓት እንደሚገባ አዋጁ ይደነግጋል፡፡ ገዢው እንዴት ነው ክፍያውን የሚፈጽመው?

አቶ ደሳለኝ፡- መብት ማስተላለፍና የዋስትና ጉዳይ ዋነኛው የአዋጁ ክፍል ነው፡፡ መብት ማስተላለፍ ይቻላል፡፡ ባዶም ቦታ ቢሆን እንኳ፡፡ የተቀመጠ የጊዜ ሁኔታ ግን አለ፡፡ ውል ተቀባዩ 18 ወራት ውስጥ ይገነባል ከተባለ 18 ወራት ውስጥ መገንባት የሚችል መሆኑን ሻጭና ገዢ ናቸው መስማማት ያለባቸው፡፡ በግንባታ ጊዜ ውስጥ ሆኖ ነው የሊዝ መብትን ማስተላለፍ የሚችለው፡፡ ነገር ግን መብት አስተላላፊው ቦታውን ሲያስተላልፍ የሚታሰብለት፣ ለቦታው የከፈለው ቅድሚያ ክፍያ ወለዱን ጨምሮ ይታሰብለታል፡፡ ለማበረታታት መሬቱ በመቆየቱ ከሚያስገኘው ዋጋ ላይ አምስት በመቶ ይታሰብለታል፡፡ ይህን መብቱን ነው ሊያገኝ የሚችለው እንጂ እንደ ቀድሞው መሬት እየሸጡ ገንዘብ ማግኘት አይቻልም፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሬት መሸጥና መለወጥ የተከለከለ ነው፡፡ መሬት ዋጋ ያስገኝልኛል ብሎ ተንብዮ ገንዘብ ማግኘት አይቻልም፡፡ በፊት ምንም ሳይሠሩ የሚያገኙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ይህ አሁን አይሠራም፡፡ የተላለፈለት ሰውም ሥራውን በተባለው ጊዜ ባይጨርስ ቦታውን ይቀማል፡፡ ካልሠራ እንደሚቀማ አውቆ ነው ቦታው በሊዝ የሚተላለፍለት፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ አሠራር በጣም መጥበቁ ግብይት እንዲስተጓጎል፣ መንግሥትም ማግኘት ያለበትን እንዳያገኝ አያደርገውም?

አቶ ደሳለኝ፡- ትራንዛክሽኑ (የግብይት እንቅስቃሴው) ሊያንስ ይችላል፡፡ መንግሥት ከዚህ ከትራንዛክሽን ይልቅ ልማቱን ነው የሚፈልገው፡፡ ዋነኛው ተጠቃሚ ባዶ ቦታ እያስተላለፈ የሚያገኘው ግለሰብ እንጂ መንግሥት አይደለም፡፡ መንግሥት ይህንን አያበረታታም፡፡ እኛ መሬት የሰጠነው እንዲሠራበት እንጂ እንዲሸጠው አይደለም፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ ሚና እንዲጫወትና የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ነው፡፡ ሳይሠራ ከሚገኘው ገቢ ይልቅ ቢሠራ የሚገኘው ጥቅም ነው የሚሻለን ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን የግብይት ሰንሰለት የሚቆጣጠሩት የየከተሞቹ የመሬት ባለሥልጣናት ናቸው ወይስ ሌላ አካል አለ?

አቶ ደሳለኝ፡- አስፈጻሚ አካሉ ይደራጃል፡፡ የተደራጀውም በይበልጥ ይደራጃል፡፡ ከዚህ አዋጅ በመነሳትም ከተሞቹ ደንብ ያወጣሉ፡፡ የቁጥጥር አካላቱም በዚያው ደንብ አማካይነት በይበልጥ ያጠናከራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በሊዝ መብት አስተላላፊና በሊዝ መብት ተቀባይ መካከል ያለው ሽያጭ በምን ዓይነት የዋጋ ስሌት ላይ ነው የሚመሠረተው? ወይስ ጨረታ ይወጣል?

አቶ ደሳለኝ፡- በየዓመቱ ወይም በየሁለት ዓመቱ የአካባቢ የሊዝ ዋጋ እየተጠና ይወሰናል፡፡ በዚህ የአካባቢ ዋጋ ላይ ተመስርቶ ነው ሽያጩ የሚካሄደው፡፡ መንግሥትም በዚህ ዋጋ መሠረት የሊዝ ገቢውን ያገኛል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ነባር ይዞታ ያለው ሰው ይዞታውን ሲሸጥ ገዢው በሊዝ ሥርዓት ይታቀፋል ይላል አዋጁ፡፡ ከዚህ በመነሳት የሊዝ አከፋፈሉ ምን መልክ ይኖረዋል? ለይዞታውም ከፍሎ ለሊዝም ከፍሎ እንዴት ይሆናል?

አቶ ደሳለኝ፡- አንድ ሰው ሀብቱን መሸጥ ይችላል፡፡ ከገዢው ጋርም ዋጋውን ይቆርጣል፡፡ ማንም ሰው መሬትን [ይዞታዬ ነው ብሎ] ከንብረት ጋር ቀላቅሎ መሸጥ አይችልም፡፡ የሚሸጠው ንብረቱን ብቻ ነው፡፡ ንብረቱም ቤት ከሆነ ወዲያወኑ ሊዝ ውስጥ ይገባል፡፡ ኪራይ የሚባል አይኖርም ማለት ነው፡፡ ሽያጩ አንድ ሚሊዮን ይሁን ሁለት ሚሊዮን ያው ገዢና ሻጩ እንደተስማሙት ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ገዢው በአካባቢው የሊዝ ዋጋ መሠረት ክፍያ ይጀምራል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ አስተዳደሩና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቦታ ደረጃና ዋጋ ጥናት በጋራ እያዘጋጁ ነው፡፡ በዚህ ጥናት ላይ ነው የሚመሠረተው ወይስ በአካባቢው ከፍተኛ የጨረታ ዋጋ መነሻ ነው?

አቶ ደሳለኝ፡- የአካባቢው ዋጋ ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ እንደ አካባቢው ደግሞ የጨረታ ዋጋም ይለያያል፡፡ ባዶ የሊዝ ይዞታን በሚያስተላልፉት እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው በአካባቢው ከፍተኛ የጨረታ ዋጋ ላይ ይመሠረታል፡፡ ባዶ ቦታ እንዳይተላለፍ ለማድረግ ነው፡፡ ነባር ይዞታ በሚወጣው የአካባቢ የቦታ ደረጃና ዋጋ ላይ ይመሠረታል፡፡

ሪፖርተር፡- ከግለሰብ ነባር ይዞታ ከመግዛት ይልቅ ከመንግሥት በሊዝ ቦታ መግዛት ከዋጋ አንፃር የተሻለ ይሆናል ብለው አያስቡም?

አቶ ደሳለኝ፡- ወደፊት የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ አሠራር ተግባራዊ ሲደረግ የመሬት ጉዳይ ምን መልክ ይኖረዋል? ከዋጋ አንፃር ንረት ነው ወይስ መርከስ ነው የሚታየው? ምን ይገምታሉ?

አቶ ደሳለኝ፡- የመሬት ዋጋ ምንጊዜም እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡

ሪፖርተር፡- ማለቴ አንድ ገዢ በአንድ ሚሊዮን ብር ሊገዛው የሚችለውን ቤት የሊዝ ዋጋ ሲጨመርበት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል፡፡ ይህ ሁኔታ በቀጣይነት በገበያ ውስጥ የመሬት ዋጋ ንረት አይፈጥርም?

አቶ ደሳለኝ፡- የአቅርቦት ጉዳይ ነው፡፡ መሬት በስፋት የሚቀርብ ከሆነ በየከተሞቹ ዋጋ ላይ ብዙም ለውጥ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የሊዝ ገቢው 90 በመቶ ያህሉ ለልማት ነው የሚውለው፡፡ ከተሞቹ የሚያገኙትን ገንዘብ መልሰው መሠረተ ልማት ላይ ነው የሚያውሉት፡፡ መንግሥት እያለ ያለው መሠረተ ልማት አሟልቼ አቅርቦትን አሻሽላለሁ ነው፡፡ አቅርቦት እየተሻሻለ ሲሄድ ዋጋው እየተስተካከለ ይሄዳል፡፡ ፍላጎቱና አቅርቦቱ የተመጣጠነ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ሊዝ ሲባል የዕድሜ ገደብ አለው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሰዎች ሀብት የማፍራት መብት እንዳላቸው ቢደነግግም አዲሱ የሊዝ አዋጅ ይህንን ይፃረራል የሚሉ አሉ፡፡

አቶ ደሳለኝ፡- እንዴት እንደሚፃረር አይገባኝም፡፡

ሪፖርተር፡- በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ድጋሚ የመሬት ልኬት እንደሚካሄድ በአዋጁ ተገልጿል፡፡ በምን መልኩ ነው የሚካሄደው? የመሬት ስፋትና ጥበትስ እንዴት ነው የሚወሰነው? 

አቶ ደሳለኝ፡- እንደ ከተሞቹ የሚለያይና ከተሞቹና ክልሎቹ በሚያወጡት ደንብ ዝርዝር አፈጻጸም ይወሰናል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ እየወጡ ላሉ የመሬት ጨረታዎች ለአንድ ካሬ ሜትር እጅግ ውድ የሆነ የገንዘብ መጠን እየተጠራ ነው፡፡ በካሬ ሜትር እስከ 26 ሺሕ ብር የደረሰበት አጋጣሚ አለ፡፡ ነባር ይዞታዎችም ሲተላለፉ የሊዝ ዋጋ የሚጨመርባቸው በመሆኑ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የቦታ ዋጋ ንረት እንደሚፈጠር እነዚህ ሁኔታዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የከተማው መሬት ወደ ባለፀጋዎች እየሄደ ነው ይባላል፡፡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር አልታሰበም?

አቶ ደሳለኝ፡- ተወዳድረው ቦታ ማግኘት የማይችሉ አቅም የሌላቸው አሉ፡፡ ትላልቅ ኢንቨስትመንት ላይ ተወዳድሮ የሚያሸንፈው ነው ቦታውን የሚወስደው፡፡ ይህ ሁኔታ ዝቅተኛ ገቢ ባለው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ የመኖርያ ቤት ችግርና ጫና ሊፈጥር ይችላል ነው የምትለው መሰለኝ፡፡  አዋጁ እንደሚለው የጋራ መኖርያ ቤቶችም የቁጠባ ቤቶች ግንባታ እንዲካሄድ የሚያስችል ቦታም በምደባ ያገኛሉ፡፡ ይህ የዝቅተኛውን የኅብረሰብ ክፍል ችግር ይፈታል፡፡ የመንግሥት ትኩረት ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ነው በምደባ ቦታ ለእነዚህ ግንባታዎች እንዲዘጋጅ የተደረገው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በጥናታችሁ ይህ የሊዝ አሠራር ተግባራዊ ሲሆን፣ መንግሥት ምን ያህል ገንዘብ በዓመት ማግኘት ያስችለዋል ተብሎ ይጠበቃል?

አቶ ደሳለኝ፡- በዝርዝር የተጠና የለም፡፡ እንደ ክልሎቹ ይለያያል፡፡ ሌሎቹ የገቢ ምንጮች እንደተጠበቁ ሆነው ግን ትልቁና ዋነኛው የገቢ ምንጭ እየሆነ የሚሄደው የሊዝ ገቢ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
Source: ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment