Saturday, October 29, 2011

ቴዲ አፍሮ በሞት ልትነጠቅ አንድ ቀን ለቀራት ነፍስ ደረሰ

(ጥቅምት 8 ቀን 2004 .. ሪፖርተር)--ፑንትላንድ ውስጥ የሞት ፍርድ ውሳኔ ከተላለፈበት በኋላ፣ የተጠየቀውን የነፍስ ካሣ ክፍያ በአሥር ቀናት ውስጥ ማለትም ጥቅምት 17 ቀን 2004 .. ድረስ ካልፈጸመ፣ ውሳኔው ተግባራዊ እንደሚሆን የተነገረውን ግለሰብ፣ ግድያው ሊፈጸምበት አንድ ቀን ሲቀረው፣ ድምፃዊው ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) የተጠየቀውን የነፍስ ዋጋ 700 ሺሕ ብር ከፈለ፡፡

አስመሮም ኃይለ ሥላሴ የተባለው ግለሰብ ሊገደል አንድ ቀን ሲቀረው ድምፃዊው የደረሰለት ሲሆን፣ ራሷን ከሶማሊያ አግልላ ዕውቅና የሌለው መንግሥት መሥርታ በምትኖረው ፑንትላንድ ቦሳሳ ከተማ ውስጥ ይኖር ነበር፡፡

ጥቅምት 14 ቀን 2004 .. ከሰዓት በኋላ በሪፖርተር ዝግጅት ክፍል በድንገት የተገኘችው የአስመሮም ኃይለ ሥላሴ ታናሽ እህት ሉዋም ኃይለ ሥላሴ፣ ወንድሟ ሊገደል የቀረው ሁለት ቀን ብቻ መሆኑን ከመናገር ውጭ ዝርዝር ጉዳዮን ለማስረዳት አልቻለችም፡፡

ወንድሟ ለምን እንደሚገደል፣ ማን እንደሚገድለውና የት አገር እንደሚገደል ሉዋም እምባ እየቀደማት መናገር ቢያቅታትም፣ አብሯት መጥቶ የነበረው ዘመዷ ጉዳዩን ያውቀው ስለነበር ባለፈው ረቡዕ የሪፖርተር ዕትም ላይ የተዘገበውን አስረዳ፡፡

አስመሮም ፍርዱን ሊቀበል ሁለት ቀናት ብቻ በቀሩት ረቡዕና ሐሙስ፣ "ምናልባት ሪፖርተር ጋዜጣን ያነበቡ ኢትዮጵያዊያን ወይም የመንግሥት አካላት ይታደጉታል" የሚል ሙሉ እምነት ቢኖርም፣ በማተሚያ ቤት የማተሚያ ማሽን ብልሽት በማጋጠሙ የረቡዕ ዕትም በዕለቱ ሳይወጣ ቀርቶ፣ ፍርደኛው ለሞት አንድ ቀን ሲቀረው ሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን 2004 .. ለንባብ በቃ፡፡

ምንም የሚከፍለው የነፍስ ዋጋ የሌለው አስመሮም ከአንድ ቀን ያነሰ ጊዜ ቢቀረውም፣ ሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን 2004 .. በሲኤምሲ አካባቢ ባለ አንድ ካፌ ሻይ ቡና ለማለት ጐራ ያለው ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ሪፖርተር ጋዜጣን ያገኛል፡፡ "ጋዜጣውን አንስቼ እንደያዝኩት በፊት ለፊቱ ገጽ ካሉት ዜናዎች አንዱ ስለ አስመሮም የተጻፈው ሳበኝና ትኩረቴን በእሱ ላይ አደረኩኝ፤" ሲል ቴዲ ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡

የዜናውን ዝርዝር ሳይመለከት አስመሮም ያለበትን ጭንቀትና ሁኔታ ማሰላሰል የጀመረው ቴዲ አፍሮ፣ "እጅግ በጣም አሳዘነኝ፤ ደጋጋሜ አነበብኩት፤ አሁን የምነግርህ እውነቴን ነው እጄ ላይ ምንም ገንዘብ የለኝም፤ ወደ ጓደኞቼ ስልክ መደወል ጀመርኩኝ፤" ብሏል፡፡

ሞት የተፈረደበት ኢትዮጵያዊ የተጠየቀውን ቢከፍል እንደሚለቀቅ፣ በጐሳ መሪዎቹ የተጠየቀውን ያህል ገንዘብ ሊሰጠው የሚችልን ሰው ማፈላለግ የጀመረው ቴዲ አፍሮ፣ ሦስት ጓደኞቹ ዘንድ ሲደውል፣ ባጋጣሚ አገር ውስጥ አለመኖራቸውን ያረጋግጣል፡፡

"ይኼንን ልጅ ለማዳን የትም ድረስ መሄድ አለብኝ ብዬ ተነሳሁ፤" ያለው ቴዲ አፍሮ፣ አንድ ፈቃደኛ ግለሰብ ማግኘቱንም ገልጿል፡፡ "እግዚአብሔር ሁሉን ያደርጋል፤ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፤" በማለትም መልሶ የሚከፍለው ቢሆንም፣ ገንዘብ የሰጠውን ግለሰብ አመስግኗል፡፡

ቴዲ አፍሮ ሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን 2004 .. ገንዘቡን ማግኘቱን ካረጋገጠ በኋላ፣ የሪፖርተር ጋዜጣ አዘጋጆችን ሲያፈላልግ የሪፖርተር ጋዜጣ አሳታሚና ሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ አረጋዊን አግኝቶ ሁሉንም ነገር ይነግረዋል፡፡

የሞት ፍርድ ሊፈጸም ሰዓታት ብቻ የቀረውን አስመሮም ኃይለ ሥላሴን ለመታደግ በሪፖርተር ዝግጅት ክፍል አማካይነት እህቱን ሉዋም ኃይለ ሥላሴ አፈላልጐ ካገኘ በኋላ፣ አብሯት በመሆን ጥቅምት 17 ቀን 2004 .. ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በመሄድ የነፍስ ዋጋ ክፍያው መገኘቱን ያረጋግጣል፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ባደረጉት ቀና ትብብር  ፑንትላንድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ በኩል በተደረገ ርብርብ አስመሮም ከሞት ሊተርፍ ችሏል፡፡

ቴዲ አፍሮ የነፍስ ዋጋ እንዲከፍል ለተጠየቀው አስመሮም ማስለቀቂያ 700 ሺሕ ብር በቼክ ቁጥር H7134375 ለወ/ሪት ልዋም ኃይለ ሥላሴ አስረክቧል፡፡

አስመሮም ጥቅምት 17 ቀን 2004 .. ሊፈጸምበት ከነበረው ሞት የዳነ መሆኑን ያረጋገጥን ቢሆንም፣ ለካሣ ተከፋዮቹ ገንዘቡ ደርሷቸው ከእስር መለቀቅ አለመለቀቁን ለሕትመት እስከገባንበት ድረስ ማረጋገጥ አልቻልንም፡፡   

አስመሮም ፑንትላንድ ከተማ ቦሳሶ ውስጥ የግድያ ውሳኔ የተላለፈበት በጎሳ መሪዎች ሲሆን፣ ቤተሰቦቹ እንደሚሉት በመኖርያ ቤቱ ላይ ዝርፊያ ለመፈጸምና ባቤቱን ለመድፈር የመጡ ግለሰቦች ቤቱን ሰብረው ሲገቡ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት በተደረገ ግብግብ አንደኛውን ግለሰብ ገድለሃል በመባሉ ነው፡፡
Source: ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment