Tuesday, September 13, 2011

ለምሥራቅ አፍሪካ ለድርቅ ተጐጂዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አስታወቀ

(2011-09-14, አዲስ አበባ)፡- በምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አስታወቀ። ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ስብሰባውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።

ስብሰባው ባለፈው ሰኞ በግዮን ሆቴል ሲከፈት የሥራ አስፈፃሚው ኮሚቴ አባላት እንዳስታወቁት፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በምሥራቅ አፍሪካ በተከሰተው ድርቅና በሶማሊያ በተፈጠረው ረሃብ ለተጎዱ ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮመቀጠል ይጠበቅበታል።

የሕብረቱ ዋና ፀሐፊ ቄስ ዶክተር አላቭ ፍይክስ ቲቬት እንደተናገሩት፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት በአካባቢው የተከሰተውን ድርቅ በቅርብ ሲከታተልና የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል። በቀጣይም ይህንን ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል።

«የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሶማሊያ በተከሰተው ረሃብ ተጐጂ ለሆኑ ወገኖች እያደረገ ያለው ድጋፍ ጥሩ ቢሆንም በቂ አይደለም» ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ በመላው ዓለም የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ለተጎጂዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቀዳማዊ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፤ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ለድርቁ ተጎጂዎች ከሚደረገው ድጋፍ ጎን ለጎን በሶማሊያ ያለውን አለመረጋጋት ለማሻሻል ጥረት መደረግ አለበት።

«በሶማሊያ ያሉ ኃይሎች የሚፋለሙበት የጦር መሣሪያ በሶማሊያ የሚመረት አይደለም። የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ወደ ሀገሪቱ የጦር መሣሪያው እንዳይገባ በመጣር በአገሪቷ ሰላም እንዲሰፍን መንቀሳቀስ አለበት» ብለዋል።
የጀርመን ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን የምሥራቅ አፍሪካ ተወካይ ሚስተር ሮበርት ሄድለይ በበኩላቸው የሶማሊያን ረሃብ በተመለከተ ባቀረቡት ጽሑፍ፤ በተባበሩት መንግሥታት መለኪያ መሠረት በአንድ አካባቢ ረሃብ ተከሰተ ለማለት በየቀኑ 10 ሕፃናት ሁለቱ ሲሞቱ መሆኑን አስታውሰው፤ በሶማሊያ በአሁኑ ወቅት 10 ሕፃናት 15 ሕይወታቸው እያለፈ ነው ብለዋል።

በሶማሊያ በአሁኑ ወቅት 40 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ለረሃብ መጋለጡን ገልጸዋል። የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ጉባዔ ቄስ ዶክተር አንድሬ ኮርማን በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ሕብረትና የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ጉባዔ በአፍሪካ ያሉትን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማስወገድ በጋራ መሥራት አለባቸው።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዋቅስዩም ኢዶሳ እንደተናገሩት፤ ቤተክርስቲያኗ መንግሥት የቀየሰውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ በማድረግ የአገሪቱን ህዳሴ ዕውን መሆን ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል። የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት 349 አባል አብያተ ክርስቲያናት እና120 አባል አገራት እንዳሉት በዕለቱ ተገልጿል።

No comments:

Post a Comment