Thursday, January 13, 2011

በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ላለቁት ኢትዮጵያውያን የተሠራው ሐውልት እሑድ ይመረቃል

(Wednesday, 12 January 2011, Reporter)--የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ለግንባታው ተባባሪ እንደነበረ አስታወቀ በጋዜጣው ሪፖርተር አምና በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ ተከስክሶ በወደቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላለቁት ኢትዮጵያውያን በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተገነባው ሐውልት የፊታችን እሑድ ጥር 8 ቀን 2003 ዓ.ም. ይመረቃል፡፡

ጥር 16 ቀን 2002 ዓ.ም. ከቤይሩት ራፊቅ ሐሪሪ አውሮፕላን ማረፊያ ተነሥቶ ወደ አዲስ አበባ በመብረር ላይ ሳለ በደረሰበት ድንገተኛ አደጋ በሜዲትራንያን ባሕር በወደቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ላይ ተሳፋሪ የነበሩ 82 መንገደኞችና 8 የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ሕይወት መጥፋቱ ይታወሳል፡፡

የአውሮፕላኑ ሠራተኞች በሙሉ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ከመንገደኞቹ መካከል 23ቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡት የአውሮፕላኑ ሠራተኞችና መንገደኞች የመታሰቢያ ሐውልት በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አሠርቷል፡፡

ሐውልቱ የፊታችን እሑድ ጥር 8 ቀን 2003 ዓ.ም. የአደጋው ሰለባ ቤተሰቦች፣ የአየር መንገዱ ማኔጅመንትና ቦርድ አባላት፣ ሠራተኞች፣ የሃይማኖት መሪዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት በሚገኙበት እንደሚመረቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አመራሮችና አባላቱ በወቅቱ በተፈጸመውን አሰቃቂ አደጋ የተሰማቸውን ብርቱ ሐዘን መግለጻቸውን፣ ለአርበኞቹ በተዘጋጀው ቦታ ላይ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው እንዲፈጸም ጥያቄው በቀረበበት ጊዜ ሐሳቡን ያለምንም ማመንታት በመቀበል ሥራውን ማስፈጸማቸውን በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የሐውልቱ ሥራ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስም ሥራው ተፈጻሚ እንዲሆን ከማድረግ ውጭ በተጎጂ ቤተሰቦች ዘንድ ውዝግብ ፈጥረዋል ተብሎ በሪፖርተር የወጣው ውንጀላ እንዳሳዘናቸው በመግለጫው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
Source:  Reporter

1 comment:

Post a Comment