11 January, 2011 በ ስሎሞን አባተ | አዲስ አበባ / ዋሽንግተን ዲ.ሲ.
በውኃ ኃብት የበለፀገችው ኢትዮጵያ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት እና ከ30 እስከ 40 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል የወንዞች ዕምቅ አቅም ቢኖራትም እስከአሁን ግን ያለማችው መሬት ከምትችለው ከ2 ነጥብ 5 ከመቶ የማይበልጥ እና የምታመነጨው ኃይልም 2 ሺህ ሜጋ ዋት የሚሆን መሆኑ ተነግሯል፡፡
ለዚህ የተዳከመ ልማት ምክንያት የሚሏቸው የገንዘብና የቴክኒክ አቅም፣ ለብዙ ዓመታት የነበረ ልማቱን በዕቅድና በፕሮግራም ያለመምራትም ችግር እንደነበረም የውኃና የኢነርጂ ሚኒስቴር የወሰንና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ በየነ አስታውሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወንዞች ከዘጠና ከመቶ በላይ የሚሆኑት ወሰን ተሻጋሪ በመሆናቸውም ዓለምአቀፍ ጫናም የራሱን አስተዋፅዖ እንዳበረከተ አስረድተዋል፡፡ ዘመናዊ የውኃ ኃብት ልማት ሥራ ከተጀመረ ገና ግማሽ ምዕት ዓመት መሆኑንም አቶ ተፈራ ጠቁመዋል፡፡
በተለይ ዓለምአቀፉን ጫና በሚመለከት እንግሊዝ በቅኝ ታስተዳድራቸው የነበሩትን ሱዳንን፣ ኬንያን፣ ታንዛኒያን እና ዩጋንዳን ወክላ እአአ በ1929 ዓ.ም. ከግብፅ ጋር የፈረመችው ውል እና ግብፅና ሱዳን ደግሞ እአአ በ1959 ዓ.ም. ብቻቸውን የፈረሙት ስምምነት ፍትሐዊ አለመሆናቸውን፤ ኢትዮጵያ ከመነሻው ጀምሮ ስትቃወማቸው መኖሯን፤ የተፈፃሚነት አቅምም ሊኖራቸው እንደማይችል አቶ ተፈራ በየነ ተናግረዋል፡፡
ሰባት የአባይ ተፋሰስ የራስጌ ወይም አመንጭ ሃገሮችም ከፊታችን ሰኔ አካባቢ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ያሉትን ስምምነት አውጥተው አምስት ሃገሮች ፈርመውታል፡፡ ግብፅ ግን አባይን መጠቀም በእርሷአጠቃቀም ላይ "ጨርሶ ጉዳት የማያስከትል መሆን አለበት" በማለቷና ሌሎቹ ሃገሮች ደግሞ "በከፋ ሁኔታ የማይጎዳ" ሊሆን ይችላል እንጂ ለግብፅ ፍፁም የበላይነትና ፍፁም ባለቤትነትን በሚያጎናፅፍ ሁኔታ መቀመጥ የለበትም በሚል እንዲያውም እራሷን ከስምምነቱም ውጭ አድርጋለች እስካሁን፡፡
No comments:
Post a Comment