Sunday, December 26, 2010

የደርግ ባለሥልጣናት የይሁንታ ቀን ተራዘመ

Source reporter: Sunday, 26 December 2010 10:36   
ለገና መፈታታቸው አጠራጣሪ ሆኗል
በዘካሪያስ ስንታየሁ
የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሥልጣን ዘመናቸው በአገሪቱ ላይ በፈጸሙት በደልና ጥፋት ተጸጽተናል በማለት የኢትዮጵያ ሕዝብና የተጐጂ አካላትን ይቅርታ ለመጠየቅ የተቆረጠው የይሁንታ ቀን ተራዘመ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሃይማኖት መሪዎች በጋራ በመሆን ታኅሣሥ 21 ቀን 2003 ዓ.ም. ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ በሕዝብና በተጐጂ ወገኖች ይቅርታ እንዲደረግላቸው ፕሮግራም ቢያዝም፣ ጉዳዩን አስመልክቶ የተለያዩ ተቃውሞዎች በመነሳታቸው ምክንያት የይሁንታው ቀን ላልታወሰነ ጊዜ ተራዝሟል፡፡


የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ከሕዝብና ከተጐጂ ወገኖች ይቅርታ ካገኙ በኋላ ለገና ይፈታሉ ተብሎ የታሰበ ቢሆንም፣ አሁን ጉዳዩ በገጠመው ተቃውሞ ምክንያት ባለሥልጣናቱ በተባለው ጊዜ የመፈታታቸው ነገር አጠራጣሪ ሆኗል፡፡

የደርግ ባለሥልጣናቱ በመጀመሪያ ይሁንታን ካገኙ በኋላ በይፋ ሕዝብንና ተጐጂ ወገኖችን ይቅርታ ይጠይቃሉ፤ ከዚያም ጉዳዩ ለአገሪቱ የይቅርታ ቦርድ ቀርቦ ባለሥልጣናቱ ከእስር ይፈታሉ ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፣ በተለይ የተጐጂ አካላት በጉዳዩ ላይ ተቃውሟቸውን በማሰማታቸው ብሔራዊ እርቁ በታሰበለት የጊዜ ሰሌዳ ላይካሄድ ይችላል የሚል ስጋት አለ፡፡

የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በፈጸሙት በደልና ጥፋት ተጸጽተው መንግሥትንና ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ እንደሚፈልጉ ለአገሪቱ የሃይማኖት መሪዎች መግለጻቸውን ተከትሎ፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ ከሚገኙ የተጐጂ ቤተሰቦች ጋር ውይይት አድርገን ይሁንታ አግኝተናል ሲሉ የሃይማኖት መሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም በወቅቱ በባለሥልጣናቱ የተለያዩ ግፍና በደሎች ተፈጽመውብናል የሚሉ ተጐጂዎች ማንም እንዳላወያያቸው እየገለጹ ነው፡፡

ታኅሣሥ 21 ቀን 2003 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ፋክሊቲ አዳራሽ ውስጥ ሊካሄድ በታሰበው የይሁንታ ቀን ላይ እንዲሳተፉ 500 የሚሆኑ ሰዎች ተጋብዘው ነበር፡፡ በዚሁ መሠረት በአገሪቱ ከሚገኙ 74 ከተሞች የተመረጡ 177 የስቃይ ሰለባዎች፣ አዲስ አበባ ከሚገኘው የስቃይ ሰለባዎች ማኅበር 118 አባላትና እንዲሁም ሌሎች በይሁንታው ላይ እንዲሳተፉ የተጋበዙ ሌሎች ግለሰቦች እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የስቃይ ሰለባዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተረፈ ኃይሌ ለሃይማኖት መሪዎቹ በይሁንታው ላይ እንደማይገኙ አስታወቀው እንደነበር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ሆኖም አሁንም አካሄዱ ከተስተካከለ ወደፊት በሚደረገው የይሁንታ ቀን ላይ እንደሚሳተፉ አክለው ገልጸዋል፡፡

የሃይማኖት መሪዎቹ በጉዳዩ ዙሪያ ከመንግሥት ጋር ቢወያዩም፣ ብዙ ድጋፍ እንዳላገኙ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ፣ የይሁንታው ቀን መራዘም ዋነኛ ምክንያቶች ሁሉም የተጐጂ አካላት ላለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄዱት ውይይቶች አለመሳተፍና ከመንግሥት በኩልም ድጋፍ አለማግኘቱ ነው፡፡ ምንጮቹ አክለውም መንግሥት ጉዳዩን በማጣራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሽመልስ ከማል ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው አጣርተው እንደሚነግሩን ቢገልጹልንም፣ ሕትመት እስከገባንበት ድረስ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡
አራቱ የሃይማኖት መሪዎች ታኅሣሥ 9 ቀን 2003 ዓ.ም. በኢንተር ኮንቲኔንታል  ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በደርግ ዘመን የተፈጸመውን በደልና ጥፋት በአገራዊ ይቅርታና እርቅ ለመጨረስ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የእርቁና የይቅርታው ተካፋይ እንዲሆን ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment