Wednesday, December 15, 2010

ከኖርዌጂያዊው ዜጋ ጋር የምትከራከረው ኢትዮጵያዊት ስድስት ወራት ተፈረደባት

Wednesday, 08 December 2010 13:55 
(በታምሩ ፅጌ)
የሁለት ዓመት ሕፃን ልጇን ኖርዌጂያዊው አባቱ እንዲያገኘው በኢትዮጵያዊቷ ወ/ሮ መስከረም ከተማ ላይ ትዕዛዝ ሰጥቶና አፈጻጸሙ ተግባራዊ እንዲሆን፣ ለሕዳር 27 ቀን 2003 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት፣ ትዕዛዙን ባለማክበሯ በስድስት ወራት እንድትቀጣ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ 


የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝና አፈጻጸም ተግባራዊ ባለመደረጉ በእስራት እንድትቀጣ ውሳኔውን ያስተላለፈው ከትናንት በስትያ ከሰዓት በኋላ ነው፡፡
ወ/ሮ መስከረም ከተማና ኖርዌጂያዊው ሚስተር ቱር ኤድቫርድ ቱርጌሰን ተገናኝተው አብረው መኖር የጀመሩት ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ሁለቱ ግለሰቦች  ባልና ሚስት መሆናቸውን ፍርድ ቤት አረጋግጧል፡፡
ወ/ሮ መስከረም የመጀመርያ ልጇን ከኖርዌጂያዊው ያረገዘች ቢሆንም የልጁ ዕድሜ ከስምንት ወራት አላለፈም፡፡ ‹‹ለልጁ ሕልፈት ምክንያቱ በማላውቀውና ምንም ባልሆንኩበት ሁኔታ ኦፕራሲዮን ሆኜ ያለግዜው በመውጣቱ ነው፤›› ካለች በኋላ፤ ለዚህም ተጠያቂው ሚስተር ቱር መሆኑን ትናገራለች፡፡

ሁለተኛ ልጇንም ከሚስተር ቱር ከወለደች ጊዜ ጀምሮ ሁለቱ መስማማት ባለመቻላቸው ለአራት ወራት ያህል ለብቻዋ ተዘግቶባት ከቆየች በኋላ ወደ ቤተሰቦቿ መቀላቀሏን ታስረዳለች፡፡

ከግለሰቡ ተለይታ ከቤተሰቦቿ ጋር በመኖር ላይ እያለች በፍርድ ቤት ክስ መሥርታ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የወ/ሮ መስከረምና የሚስተር ቱር ግንኙነት የባልና ሚስት መሆኑን አረጋግጦ፣ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 102/1/ መሠረት ያፈሯቸውን ንብረቶች ሸጠው እንዲካፈሉ ተወስኗል፡፡

ሕፃኑን በሚመለከት (አሁን 2 ዓመቱ ነው) ከእናቱ ጋር እንዲሆን፣ አባቱ ከሰኞ እስከ ዓርብ ከቀኑ 9 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት፣ ቅዳሜና እሁድ ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ወስዶ እንዲያዝናና በየወሩ 1000 ብር ተቆራጭ እንዲያረግ ተወስኗል፡፡

ሚስተር ቱር ወልዳ በተኛችበት ወቅት የተለያዩ ማስፈራራቶችን ያደርግባት እንደነበር የገለጸችው መስከረም፤ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሕፃኑን ሚስተር ቱር ወስዶ እንዲያዝናና የተፈቀደለትን ውሳኔ በመቃወም ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ብላለች፡፡

ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኙን ተመልክቶ ሕዳር 15 ቀን 2002 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን በመሻር ሚስተር ቱር ልጁን ቅዳሜና እሁድ ብቻ ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት እንዲያዝናና ሲል ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

‹‹እኔ በሌለሁበትና ባልሰማሁበት ሁኔታ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሄዶ የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ በማሻር የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲጸና አስደርጓል፤›› የምትለው ወ/ሮ መስከረም፤ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ መሠረት ልጇን ለአባቱ ለሚስተር ቱር እንድታስረክብ ለሕዳር 27 ቀን 2003 ዓ.ም. ታዛ የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤት የቀረበችው ግን ልጇን ይዛ ሳይሆን ብቻዋን ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ ሲጠይቃትም፣ ‹‹ቤተሰቦቼና እኔ ባለሁበት መጎብኘት ይችላል፡፡ ለሕይወቱ ስለምፈራ ልጄን መስጠት አልፈልግም፤›› በማለቷ ስድስት ወራት እንድትታሰር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በመስጠቱ፣ ለጊዜው ቀጨኔ መድኀኒዓለም አካባቢ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ታስራ ትገኛለች፡፡ የወ/ሮ መስከረምና የሚስተር ቱር ግንኙነትንና ውጣ ውረድን በሚመለከት በሰፊው መዘገባችን ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment