አገራችን እያሰበችው ያለውን ልማትና ዕድገት እውን ለማድረግ፣ ልንጠቀምበት የምንችለው ሀብትና እውቀት ሁሉ መጠቀም ይገባናል፡፡
ሀብትና እውቀቱ የኢትዮጵያውያን ሊሆን ይችላል፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች ሊሆን ይችላል፡፡ የውጭ መንግሥታትም ሊሆን ይችላል፤ ብቻ ለእድገቱና ለልማቱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኑረው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያዊውን ዲያስፖራ ሀብትና እውቀት ለመጠቀም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በብዛትም ሀብት አለው፤ በብዛትም እውቀት አለውና፡፡
በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን፣ በግልም ሆነ በመንግሥት ዘርፍ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ አንድ ሚሊዮን ዲያስፖራ እያንዳንዱ በዓመት አሥር ሺሕ ዶላር አጠራቅሞ ለአገር ልማት ቢያውል፣ ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ብቻ አሥር ቢሊዮን ዶላር ሊገኝ ይችላል፡፡ ይህም ለጋሾች፣ ዓለም ባንክ፣ አይኤምኤፍ ከሚሰጡን በላይ ነው፡፡ አንዳንዱም ከዚያም በላይ በዓመት ለልማት መመደብ ስለሚችል፣ የገንዘቡ መጠን እጅግ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡
ኢትዮጵያዊው ዲያስፖራ የራሱን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ በየአገሩ ያሉትን የውጭ ኢንቨስተሮች ይዞ እንዲገባ ቢበረታታም፣ የሚያስገባው ገንዘባዊ አቅም እጅግ በጣም ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥም ይገኛል፡፡
ከእውቀት አንፃር ሲታይ ደግሞ፣ የዲያስፖራው ኢትዮጵያዊ እውቀት ለኢትዮጵያ ልማት እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው፡፡ በሕክምና መስክ የሚገኙ ዶክተሮች፣ በኢንጂነሪንግ ዘርፍ ያሉ ኢንጂነሮች፣ በየአገሩ ያሉ አርክቴክቶች፣ ኮንትራክተሮች፣ የኮምፒውተር ሳይንስ ምሁራን፣ የሥነ ጥበብ ተመራማሪዎች፣ የገንዘብ ሠራተኞች ወዘተ. አንፃር ሲታይ እጅግ ጠቃሚ የሆነ እውቀት በዲያስፖራው ይገኛል፡፡
በገንዘብም፣ በእውቀትም ያለው አቅም በእጅጉ ያስመካል፡፡ ለኢትዮጵያ እድገትና ልማት የሚውል ከፍተኛ ሀብትና እውቀት አለ፤ ስንል ግን፣ ሀብቱንና እውቀቱን ለአገር ልማት እንዳይውል የሚያደርጉ እንቅፋቶች የሉም ማለት አይደለም፡፡ በርግጥ አሉ፡፡
ጽንፈኛ አመለካከት አንዱ እንቅፋት ነው፡፡ ጽንፈኛ አመለካከቱም በመንግሥትም፣ በተቃዋሚዎችም፣ በዲያስፖራው ራሱም ይንፀባረቃል፡፡
በዲያስፖራው አካባቢ ያለው የአንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጽንፈኛ አመለካከት፣ ዲያስፖራው አገሩን እንዲያለማ የሚገፋፋ ሳይሆን፣ በአገሪቱ ልማት ላይ እንዳይሳተፍ የሚያደርግ ነው፡፡ ኢሕአዴግን ጠላሁ ብሎ፣ ኢትዮጵያን አታልሙ፤ የሚል ተቃዋሚ አለ፡፡ የኢትዮጵያን ጥፋትና ውድቀት ከሚመኙ ኃይሎች ጋርም የሚሰለፍ አለ፡፡ በቅርቡ ደግሞ በሕጋዊ መንገድ የውጭ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ አትላኩ፤ በኮንትሮባንድ ብቻ ላኩ፤ መንዝሩ የሚል ጽንፈኛም፣ አደገኛም የተቃዋሚዎች ቅስቀሳ በውጭ እየተደመጠ ነው፡፡ በእጅጉ ያሳዝናል፤ የመደናቆር በሽታውም ወደ ካንሰርና ጋንግሪን እየተሸጋገረ ነው፡፡
ይህ የተቃዋሚዎች የአታልሙ ጽንፈኛ ፖለቲካ ቅስቀሳ፣ በአቅሙ የድርሻውን አሉታዊ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡
ዲያስፖራው በአጠቃላይ ሲታይም፣ አሁን አሁን አንዳንድ የመጠራጠርና የመጠየቅ ሁኔታዎች ማሳየት ቢጀምርም፣ የጥላቻ ጎርፍ ማጥለቅለቁ አልቀረም፡፡ ኢትዮጵያን አትርዱ፤ ኢትዮጵያን አታልሙ፤ የሚል መፈክርም ተጠናውቶታል፡፡ ይህ ጽንፈኛ አመለካከት ግን ይፈታል፡፡ ጭላንጭልም እየታየ ነው፡፡
ሌላው እንቅፋት፣ ዲያስፖራው ካለው ጽንፈኛ አመለካከት በመነሣት በመንግሥትም ውስጥ ዲያስፖራው አዎንታዊ አመለካከት ይዞ፣ በአገሩ ልማት የመሳተፍ እድሉ እጅግ ጠባብ ነው የሚል አመለካከት መኖሩ ነው፡፡ የዲያስፖራውን ሚና በጥርጣሬ ያየዋል፡፡ ጽንፈኛ አመለካከት ይዞ በአገር ውስጥ ከሚገባ፣ እዚያው ቢቀር ይሻላል የሚል መንግሥታዊ አመለካከትም አለ፡፡
መንግሥት ለእንደዚህ ዓይነት አመለካከቱ መነሻ አለው፤ ግን በዲያስፖራው ካለው አንዳንድ አሉታዊ አመለካከት በመነሣት፣ መንግሥት የዲያስፖራው ሚና ችላ እንዳይለው መጠንቀቅ አለበት፡፡
በርግጥ ዲያስፖራው እየተንጠባጠበ አንዳንድ ጠቃሚ ሥራዎች ሲሠራ ይታያል፡፡ ይህም ያመነ ይመጣል፤ ያላመነ ይቀራል፤ ሊያስብል ይችላል፡፡ ነገር ግን መንግሥት በብዛት አሳምኖ፣ በብዛት እንዲመጡ ማድረግ ይችላል፡፡ አቋማችንና መፈክራችን የዲያስፖራው አመጣጥ ከመንጠባጠብ ወደ መጉረፍ ይቀየር ነው ፡፡
ሁላችንም ድክመታችንን እናርም፡፡ ተቃዋሚዎችም በስመ ተቃዋሚነት ወደ ጠላት መሣርያነት እንዳይሸጋገሩ ይጠንቀቁ፡፡ ዲያስፖራው ራሱ የሚያመዛዝን እንጂ ጭፍን መሆን የለበትም፡፡ መንግሥትም ልዩ ዝግጅትና እንቅስቃሴ በማድረግ ዲያስፖራውን ያጉርፍ እንላለን፡፡
ዋናው የመንግሥት አሠራርና የፖሊሲ ጉዳይ ነውና በዚህ ዙርያ መንግሥት ልዩ ኃላፊነት ሊሸከም ይገባል እንላለን፡፡
ለዚህም ዲያስፖራን የሚከታተል ጠንካራና አንድ ወጥ ቢሮ፣ ወይም ማዕከል፣ ወይም ሚኒስቴር ሊቋቋም ይገባል፡፡ አሁን ካለው በእጅጉ የተጠናከረ ሊሆን ይገባል፡፡ የተለያዩ አጓጉል ፖሊሲዎች ነቅሶ ልዩ ቅስቀሳና ግንኙነት በማካሔድ ዲያስፖራውን ሊያሳምንና ሊያስገባ ይገባል፤ እንላለን፡፡ ይቻላልም፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከሕንድ ጋር ለየት ያለ ግንኙነት እያደረግን ነው፡፡ እግረ መንገዳችን ደግሞ የሕንድ ዲያስፖራ ሕንድን እንዴት እንደገነባ መማር ይገባል፡፡ የዲያስፖራ ሚኒስቴር ብለው በሚኒስቴር ደረጃ መሥርያ ቤት አቋቁመው፣ ልዩ ቅስቀሳ በማድረግና ልዩ ፖሊሲ በማውጣት ዲያስፖራው ሕንድን እንዲያለማ አድርገዋል፡፡
የሕንድ ዲያስፖራ ሀብትና እውቀት ሕንድን እንደገነባ ሁሉ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ሀብትና እውቀትም ኢትዮጵያን ይገነባል፡፡
ይቻላልም ! !
No comments:
Post a Comment