በሚኪያስ ሰብስቤ
ለአንድ ሲኒ ቡና የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ደረሰኝ ሳይቆረጥ ግብይት ፈጽሟል በሚል ባለፈው ሳምንት የጥፋተኝት ውሳኔ የተላለፈበት ቶሞካ ቡና ላኪ፣ አምስት ሺሕ ብር እንዲቀጣ ሲል የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት ከትናንት በስቲያ ወሰነ፡፡
በወንጀሉ ተካፋይ ናቸው ተብለው ክስ የተመሠረተባቸው የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅና ገንዘብ ተቀባይ እያንዳንዳቸው በ750 ብር እንዲቀጡ ፍ/ቤቱ ወስኗል፡፡
ሁለት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቁጥጥር ሠራተኞች ታህሣሥ 7 ቀን 2002 ዓ.ም. ከጧቱ 3፡30 አካባቢ ተስተናጋጅ መስለው ወደ ቶሞካ ቡና ገብተው አንድ ሲኒ ቡና ካዘዙ በኋላ፣ አራት ብር ሲከፍሉ የቫት ደረሰኝ አልተቆረጠም በሚል ነበር የባለሥልጣኑ ዓቃቤ ሕግ ባለፈው ዓመት ድርጅቱ ላይ ክስ የመሠረተው፡፡ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ወ/ሮ ውባየሁ ውቤ የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነታቸውን አልተወጡም፣ እንዲሁም የድርጅቱ ገንዘብ ያዥ የሆኑት አቶ አካሉ ውቤ የመርዳትና የመተባበር ሥራ ሠርተዋል በሚል ዓቃቤ ሕግ ድርጅቱን ጨምሮ ክሱን መስርቶ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ባለፈው ሣምንት የጥፋተኝነት ውሳኔ ሲያስተላልፍ፣ የባለሥልጣኑ ዓቃቤ ሕግ ወንጀሉ በተደጋጋሚ የተፈጸመ በመሆኑና ከዚህ በፊት ድርጅቱ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ባለመግዛቱ ምክንያት፣ የንግድ ፍቃዱ ተሰርዞ እንደነበርና በተደረገለት ምህረት ፈቃዱ መመለሱን ገልጾ፣ ጥፋቱን በከባድ ደረጃ እንዲመደብለት ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር፡፡
የተከላካይ ጠበቃ አቶ ቸርነት ወርዶፋ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ በመልካም ሥራው ከተለያዩ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት የመልካም ሥራ አፈጻጸም የምስክር ወረቀት ማግኘቱን፣ የጥፋተኝነት ሪከርድ የሌለበት በመሆኑና የተለያዩ ማኅበራዊ አስተዋጽኦ ያደረገ በመሆኑ፤ ፍርድ ቤቱ እንደ ቅጣት ማቅለያ ወስዶ በገንዘብ ብቻ እንዲቀጣ ይህ ካልሆነ ደግሞ የእስር ቅጣቱ በገደብ እንዲደረግለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ነበር፡፡
በዳኛ ማሕመድ ሲራጅ የተሰየመው ችሎት የወንጀሉን ደረጃ በመካከለኛ መድቦ፣ የድርጅቱን ሶስት የቅጣት ማቅለያዎችና የሁለተኛና የሶስተኛ ተከሳሾችን አራት የቅጣት ማቅለያዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ድርጅቱ የተፈጥሮ ሰው ባለመሆኑ በእስር ስለማይቀጣ አምስት ሺሕ ብር እንዲከፍል ሲወስን፣ ሁለቱ ተከሳሾችም እያንዳንዳቸው 750 ብር እንዲከፍሉ ወስኗል፡፡
በፍርድ ቤቱ ውሳኔ እፎይታ የተሰማቸው ተከሳሾች ከዘመድ ጓደኞቻቸው ጋር በመተቃቀፍ ደስታቸው ሲገልጹ፣ የተከሳሾች ጠበቃ አቶ ቸርነት በጥፋተኝነት ውሳኔው ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹የቀረበብንን ክስ በአግባቡ ተከላክለን ነበር፤ ተቆጣጣሪዎቹ በመጡበት ጊዜ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኑ ይሠራ እንደነበር ተመስክሯል፡፡ ከማሽኑ የሚወጣው ቀሪ ወረቀት ላይም 3፡28 ደቂቃ ለአንድ ሲኒ ቡና ደረሰኝ መቆረጡን፣ በመሐል ክፍተት ያልታየበትና ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ደረሰኝ እንዳልተቆረጠ ያሳያል፡፡ ይህም ተቆጣጣሪዎቹ መጡ በተባለበት ጊዜ ደረሰኝ እንደተቆረጠላቸው ያሳያል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
‹‹ነገር ግን የቅጣት ውሳኔው ላይ ፍርድ ቤቱ በደንብ ተንትኖና ተርጉሞ የቅጣት ማቅለያዎቹን ከግምት ውስጥ አስገብቶ በተከሳሾች ላይ እስራት ሳይደርስባቸው በመወሰኑ ግን ደስ ብሎኛል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩት የባለሥልጣኑ ዓቃቤ ሕግ አቶ ተስፋማርያም ገብረትንሳኤ በቅጣት ውሳኔው ላይ ቅር መሰኘታቸውን ገልጸው፣ የውሳኔውን ዝርዝር ከሕጉ ጋር አገናዝበው በቀጣይ የሚያዩት ጉዳይ እንደሚሆን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የቫት ደረሰኝ ባለመቁረጥ ድርጊት በርካታ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ከሶ ማስቀጣቱ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህም መካከል አቶ ጠና ከበደ የቲኬ ኢንተርናሽናል ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከሌሎች ሦስት ሰዎች ጋር ኤክሴል ፕላስቲክስ የተባለው ድርጅታቸው ባደረገው የ24 ብር ግብይት የቫት ደረሰኝ ባለመቆረጡ፣ በሁለት ዓመት እስራት እንዲቀጡ ከተወሰነ በኋላ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እስራቱ በገደብ እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል፡፡
No comments:
Post a Comment