Tuesday, July 14, 2020

አገር የፖለቲካ ቁማርተኞች መቀለጃ መሆን የለባትም!

(July 14, (አዲስ አበባ))--ኢትዮጵያን አልላቀቃት ካለ የችግር አዙሪት ውስጥ ለማውጣት የሚረዱ ሁነኛ መፍትሔዎችን ማፈላለግ፣ አማራጭ የሌለው ተግባር መሆን አለበት፡፡ ከወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ከመቼውም ጊዜ በላይ አገሪቱ በገጠማት ፈተና ላይ መነጋገር የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በርካታ የሆኑ የጋራ ጉዳዮች እያሉዋቸው ለምንድነው እርስ በርስ የሚጋጩት? የፖለቲካ ሰዎች በሠለጠነ መንገድ ከመነጋገር ይልቅ ለምን የአመፃ መንገድ ይመርጣሉ?

ለዘመናት አብረው የኖሩ ኢትዮጵያዊያን መሀል ምን ቢገባ ነው ጥላቻ የበረታው? በእኩልነት፣ በነፃነትና በፍትሐዊነት የሚኖሩባት ትልቅ አገር በጋራ መገንባት ሲቻል ለምን ትንንሽ ጎጆ መምረጥ ተፈለገ? ማንነትን፣ ቋንቋን፣ ባህልን፣ እምነትንና የመሳሰሉትን ጥቃቅን ልዩነቶች በማስተናገድ በአንድነት ኅብረ ብሔራዊት አገር መገንባት እየተቻለ፣ ልዩነት ብቻ እየተቀነቀነ አገር ለማፍረስ ለምን ሴራ ይጠነሰሳል? ከአፍሪካ አልፎ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት የሆነ ፀረ ኮሎኒያሊስት ድል በታላቁ ዓድዋ ጦርነት ያስመዘገበች አገር፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እርስ በርሱ የሚተላለቅ ትውልድ ለምን ተገኘባት? ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው ባሻቸው ሥፍራ የመኖርና ሀብት የማፍራት ሕጋዊና ተፈጥሯዊ መብታቸው እየተገፈፈ፣ ሲገደሉና ንብረታቸው ሲወድም ምን ዓይነት መልዕክት እየተላለፈ ነው?

የፌዴራል ሥርዓት አቀንቃኝ ነን የሚሉ ወገኖች ዘወትር ልዩነትን ብቻ እየሰበኩ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶችን ሲንዱ የመጨረሻ ግባቸው ምንድነው? በልዩነት ውስጥ መኖር የሥልጣኔ ምልክት መገለጫ እንደሆነና በልዩነት ውስጥ አንድነት እንዳለ መገንዘብ እንዴት ያቅታል? ወደፊት በመራመድ አንፀባራቂ ታሪክ መሥራት ሲቻል፣ ወደኋላ እየተጎተቱ ከሙታን መንፈስ ጋር መታገልና ተጨባጭ ባልሆነ የታሪክ ትንተና ትውልዱን ማባላት ዓላማው ምን ይሆን? በርካታ ጥያቄዎችን በማንሳት በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡

በአገር ላይ አደጋ ተጋርጦ ዝምታ አይበጅም፡፡ የአፍሪካ ኅብረትንና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ጭምር ከኢትዮጵያ አስደንብሮ ለማስወጣት የተቀነባበረ የጠላት ሴራ ጭምር ስለሆነ፣ ቆፍጠን ያለ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ተግባራዊ ምላሽ የግድ ይላል፡፡

በዚህ ወሳኝ ወቅት የአገሪቱን አብዛኞቹን ፖለቲከኞች ባህሪ አንስቶ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ ከራሳቸውና ከጥቅም ሸሪኮቻቸው ፍላጎት በላይ አገር እንዳለች ለአፍታ ማሰብ የማይፈልጉና ከአገር ክብርና ህልውና በላይ የራሳቸውን ተክለ ሰብዕና የገነቡ፣ አገር ከማተራመስ ጀምሮ እስከ ማፈራረስ ሥራ ላይ እንደተጠመዱ በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡

በተሳሳተ የታሪክ ትርክት ወጣቶችን በማነሳሳትና አገር የማተራመስ መርሐ ግብር በማውጣት፣ ወጣቶች ከብሔራቸው ውጪ የሆነውን ኢትዮጵያዊና ንብረቱን ድምሰሳ ውስጥ እንዲገቡ በተደጋጋሚ አድርገዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ግብፅ በህዳሴ ግድቡ ውኃ ሙሌት ምክንያት ኢትዮጵያን ሰንጋ በያዘችበት ወቅት፣ ጠንካራ ተደራዳሪ መንግሥት እንዳይኖር የተላላኪነት ሚና በመጫወት ኢትዮጵያን ቀውስ ውስጥ የሚከቱ ድርጊቶች ፈጽመዋል፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በአገር ሀብት ዘረፋ ከሚታወቁ እኩዮች ጋር ሳይቀር ግንባር በመፍጠር፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስ በርሱ የሚያናክስ ሰይጣናዊ ድርጊት ውስጥ ተገኝተዋል፡፡

 ኢትዮጵያዊያን ለችግሮቻቸው መፍትሔ ለማፈላለግ ሲነሱ፣ እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮችና ሌሎችም በግልጽ ተወስተው የማያዳግም ዕርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀት አለባቸው፡፡ አሁን በሚታየው አደገኛ ሁኔታ በፍፁም መቀጠል አይቻልም፡፡ ጥቂት ግለሰቦች ጡንቻቸውን አፈርጥመው በ110 ሚሊዮን ሕዝብ ህልውና ላይ መወሰን የለባቸውም፡፡ ለአገር ህልውና ሲባል ማንኛውም ዕርምጃ ተወስዶ ሕግና ሥርዓት መስፈን አለበት፡፡ የብዙኃን ኢትዮጵያዊያን ዕጣ ፈንታ በጥቂት ግለሰቦች ቁጥጥር ሥር ሊወድቅ አይገባም፡፡ ጥቂት ግለሰቦችና ግብረ አበሮቻቸው እንዳሻቸው የሚፈነጩበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊከበር ይገባዋል፡፡ ሕዝብ የማያከብር የዕብደት ፖለቲካ ተቀባይነት የለውም፡፡ የኢትዮጵያን ገጽታ በማበላሸት ተደማጭነት እንዳይኖራት የሚያደርግ ሴራ መበጣጠስ አለበት፡፡

በአገሪቱ ከ130 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው ቢነገርም፣ ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኞቹ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በምርጫ ሕግ መሠረት አነስተኛ የሚባሉትን መመዘኛዎች የማያሟሉና የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ የማይችሉ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ፓርቲዎች በቤተሰብ አባላትና በጥቅም ተባባሪዎች የተመሠረቱ ከመሆናቸውም በላይ፣ የረባ ጠቅላላ ጉባዔ ማከናወን የማይችሉ ናቸው፡፡ በአግባቡ ኦዲት ስለመደረጋቸው እንኳ ማስረጃ አያቀርቡም፡፡

 እዚህ ግባ የሚባል ፕሮግራም፣ ሕገ ደንብ፣ የምርጫ ማኒፌስቶ፣ አማራጭ አጀንዳና የመሳሰሉት የሌላቸው ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ሕዝብ ፊት ይዘውት የሚቀርቡት የረባ ነገር ስለሌላቸው፣ አሁንም መኖር የሚፈልጉት ቀድሞ በነበራቸው ስም ወይም ዝና ነው፡፡

 ሕዝብን ከድህነትና ከኋላቀርነት ለማላቀቅ የሚረዱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥናቶችን አስጠንተው ለውይይት ለማቅረብ ቀርቶ፣ ለአባላትና ለደጋፊዎቻቸው እንኳ መለስተኛ ሥልጠና መስጠት እንዳለባቸው አያውቁም፡፡ በብሔር ከተደራጁት ውስጥም ብዙዎቹ የዘመናት ቁስሎችን እየነካኩ ወጣቶችን ስሜታቸውን በመኮርኮር በደምፍላት ማነሳሳት እንጂ፣ አንድም ቀን ለጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥተው ሐሳብ ሲያዋጡ አይታወቁም፡፡ ወጣቶችን ከመንደራቸውና ከአካባቢያቸው ከፍ አድርገው እንዳያስቡ አዕምሮአቸውን በማገት ለጥፋት መሣሪያነት ይጠቀሙባቸዋል፡፡ ሰብዓዊ ፍጡርነታቸውን ዘንግተው በገዛ ወገናቸው ላይ የጭካኔ ድርጊት እንዲፈጽሙ ይገፋፏቸዋል፡፡

ከፊት ረድፍ በማይገኙበት የውድመት አመፅ ላይ በማሳተፍ ይማግዷቸዋል፡፡ እነሱ የውጭ አገር ፓስፖርት ይዘው የገዛ አገራቸውን እንዲያወድሙ ይቀሰቅሷቸዋል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ኋላቀር ፖለቲካ ጥርሳቸውን ከነቀሉት ጀምሮ አፍለኞቹ ድረስ የሚረባረቡት ለአገር ዕድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ ሳይሆን፣ አገርን በማፈራረስ ኢትዮጵያዊያንን መነጣጠል ነው፡፡ ይህ ደባ ደግሞ ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የተያያዘ ለመሆኑ በቅርቡ የደረሰውን ፍጅትና ውድመት ዋቢ ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ይሉኝታ ሳይኖር እውነቱን አፍረጥርጦ መነጋገር የግድ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟን በቀውስ መዝገብ ውስጥ የሚያሠፍር የታሪካዊ ጠላቶችን ደባ ማክሸፍ ይገባል፡፡

ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ግቡ ሥልጣን መያዝ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን ሥልጣን እንዴት ነው የሚያዘው የሚለው ነው፡፡ ሥልጣን በኃይል ለመያዝ የሚፈልግ ማንኛውም ነፃ አውጭ ወይም ሌላ ስያሜ ያለው ድርጅት፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ሊገኝ አይችልም፡፡ ከተገኘም ሰላማዊነትንና ፀብ አጫሪነትን ቀላቅሎ እንዲንቀሳቀስ መፍቀድ አይገባም፡፡ የሰላማዊ ፖለቲካ የጨዋታ ሕግም አይፈቅድለትም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከስደት የተመለሱም ሆኑ አገር ውስጥ ሆነው ሲውተረተሩ የነበሩ ፖለቲከኞችና ድርጅቶቻቸው፣ ከጥቂቶቹ በስተቀር ምን ዓይነት ድርጊቶችን ሲያከናውኑ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ገና ከመግባታቸው የኢትዮጵያዊያንን ደም ያፈሰሱና በሕዝብ መካከል መተማመን እንዲጠፋ ያደረጉ ኃይሎች፣ በአገሪቱ ሕግ የሌለ እስኪመስል ድረስ ከሚገባው በላይ ከባድ ችግሮች አድርሰዋል፡፡

ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ፉክክር የማይመች ባህሪ ከዕብሪትና ከጥጋብ ጋር አደባልቀው፣ በፈለጉት ጊዜ አመፅ እየቀሰቀሱ ለንፁኃን ዕልቂትና ለደሃ አገር ሀብት ውድመት ምክንያት ሆነዋል፡፡ ከሥልጣኔና ከማስተዋል ጋር ለመተዋወቅ ፈቃደኞች ባለመሆናቸውም፣ ሰላማዊውን የፖለቲካ ፉክክር በመናድ በጉልበት ውሎ ማደርን ተጎናፅፈው አገር አመሰቃቅለዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጋጠ ወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ አገር በዚህ ሁኔታ መቀጠል አይቻላትም፡፡ ሕዝቡም እንዲህ ዓይነት የአገር ዕዳዎችን የሚሸከምበት ጫንቃ እንደሌለው መገንዘብ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያም በጠላቶቿ ደባ ተገቢ ያልሆነ ምሥል እየተፈጠረባት ሰላሟ ሲቃወስ የጨነገፉ አገሮች ተርታ መመደቧ አይቀሬ ነው፡፡

ሽግግሩን እየመራ ያለው መንግሥት የኮሮና ወረርሽኝ የሕዝብ ጤና አደጋ መሆኑ ካበቃ በኋላ ይካሄዳል ለተባለው መጪው ምርጫ አስቻይ ሁኔታዎች እስኪፈጠሩ ብቻ ሳይሆን፣ ከወዲሁ መደላድሉን ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያተረፈ ሰላማዊና እውነተኛ ምርጫ እንዲካሄድና የሥልጣን ቅብብሎሹ የሰመረ እንዲሆን፣ ከመንግሥት በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ተሳትፎ በመተማመን ላይ የተመሠረተና ሁሉን አቀፍ እንዲሆንም ሁሉም አካላት ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው፡፡

በተቻለ መጠን ከሸፍጥና ከነውረኛ ተግባራት በመቆጠብ በኢትዮጵያ ምድር ዓለም አቀፋዊ መመዘኛዎችን ያሟላ ምርጫ ይካሄድ፡፡ ሕዝብ በድምፁ መወሰን እንደሚችል ለመጀመርያ ጊዜ ይታይ፡፡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፉክክር ተደርጎ የሐሳብ ገበያው ይድራ፡፡ ጉልበተኝነት ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ይወገድ፡፡ የሚፈለግባቸውን ኃላፊነት ሳይወጡና ራሳቸውን ሳያዘጋጁ ሰበብ የሚደረድሩ የፖለቲካ ፓርቲ ተብዬዎች ሥፍራ አይኑራቸው፡፡ ወጣቶችን በደቦ እያደራጁ ንፁኃንን የሚያስፈጁና ንብረት የሚያስወድሙ በሕግ ይጠየቁ፡፡

የሕግ የበላይነት በንድፈ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባር ይረጋገጥ፡፡ በዚህ መንገድ ፖለቲካው እንዲመራ ከተደረገ ጥቂቶች አገር ማመስ አይችሉም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በአፅንኦት መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብ የጥጋበኞች የውድመት ፖለቲካ ሰልችቶታል፡፡ ለመንግሥትም በግልጽ አስታውቋል፡፡ አገሩም በዓለም አቀፍ የሚዲያ አውታሮች በቀውስ ዘገባዎች መታወቋ እያንገበገበው ነው፡፡

እንደሚታወቀው አገር ችግር ሲያጋጥማትና ሕዝብ ሥጋቱ ከመጠን በላይ ሲሆን፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች ጥፋተኞችን መገሰፅ አለባቸው፡፡ ጽንፈኛ ብሔርተኞች ኢትዮጵያዊያንን እርስ በርስ ሲያናክሱና አገር ሲያፈርሱ ዝምታ አይገባም፡፡ የሰሞኑ አደገኛ ድርጊት አገርን የሚያፈርስና ሕዝብን እርስ በርሱ የሚያፋጅ እንደነበር የሚስተባበል አይደለም፡፡

ጽንፈኞች የአንድ ብሔር ወጣቶችን በሌሎች ላይ አስነስተው ንፁኃን ሲያስጨፈጭፉና ንብረታቸውን ሲያስወድሙ፣ እየተላለፈ የነበረው መልዕክት አገር አፍራሽ እንደነበር በግልጽ ታይቷል፡፡ ከዚህ ቀደም የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች ያከናወኑትን ታላቅና አንፀባራቂ ተምሳሌትነት ሩቡን ያህል ጥረት ማድረግ ባለመቻሉ ግን፣ አገርና ሕዝብ በየጊዜው በሚቀሰቀሱ ግጭቶች እያደር ወደ አዘቅት እያመሩ ነው፡፡

የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች የፖለቲከኞችን ግንባር መቋጠርና መፈታት እያዩ ሳይሆን፣ በህሊናቸውና በእምነታቸው እየተመሩ እውነት ላይ ተመርኩዘው አገርን መታደግ አለባቸው፡፡ በስመ አገር ሽማግሌነትና የሃይማኖት ወኪልነት የፖለቲከኞች ተላላኪ የሆኑትንም አደብ ያስገዙ፡፡ አገር በጥቅም ፈላጊዎች የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ ስትሆን ቆመው መታዘብ የለባቸውም፡፡ መንግሥትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ሲያጠፉ በድፍረት መገሰፅ ይጠበቅባቸዋል፡፡

አገር የሥርዓተ አልበኞች መጫወቻ የምትሆነው የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች በዝምታ ሲሸበቡ ነው፡፡ በመሆኑም ደፈር ብለው ወጥተው የኢትዮጵያን ሕዝብ ይታደጉ፡፡ በሕግ አለመጠየቅን የለመዱ ኃይሎች በሚጭሩት እሳት አገር መቃጠል የለባትም፡፡

በኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል ላይ ለመነጋገር የሚቻለው በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ አግባብ መሆኑን ማጤን ተገቢ ነው፡፡ በሰላም ማስከበርና በተለያዩ አበርክቶዎቿ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በጠላት ተላላኪዎች ዘወትር ቀውስ ውስጥ እንድትገኝ መደረጉ የሚያስከትለው መዘዝ ቢጤን ጥሩ ነው፡፡ የታላላቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በሴረኞች ተቀባይነቷ እንዲያከትም ሲደረግ ቆሞ ማየት አይገባም፡፡ ከአሁን በኋላ አገር የፖለቲካ ቁማርተኞች መቀለጃ መሆን እንደሌለባት የጋራ አቋም መያዝ አለበት!
ሪፖርተር, አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

No comments:

Post a Comment