Saturday, September 29, 2018

አዳመጠች አረገዘችን አይሆንም

አንዳንድ ታሪክ ሲቆይ ተረት ይመስላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን እንድ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ድንቅ መምህር ነበሩ፡፡ ለተማሪዎቹ የሚሰጧቸው ቋሚ ትዕዛዛት ነበሩ፡፡ ተማሪዎቹም ያከብሩዋቸውና ይወዷቸው ስለነበር ለጥ ሰጥ ብለው ትዕዛዛቱን ይቀበሉና ይተገብሩ ነበር፡፡

1ኛው ትዕዛዝ - የቤት ሥራህን አትርሳ
2ኛው ትዕዛዝ - ለሂሳብ አሰራር ቦታ ተው
3ኛው ትዕዛዝ - መልሱን ጥርት አርገህ ፃፍ
4ኛው ትዕዛዝ - አትኮርጅ
5ኛው ትዕዛዝ - ከኮረጅክ በትክክል ኮርጅ ግን መልስ ብቻ አትኮርጅ፤ አሰራሩን
በትክክል እይ፡፡ ቢያንስ ሥራውን አውቀህ ትገለብጣለህ፡፡
6ኛው ትዕዛዝ - የቅሪላ ማልፊያ (የኳስ) ጊዜህን ቀንስ፡፡ የቤት ሥራህን እንዳያዘናጋህ
አስብ፡፡
7ኛው ትዕዛዝ - ግብረገብነትን ውደድ
8ኛው ትዕዛዝ - ከክፍልህ አታርፍድ
9ኛው ትዕዛዝ - የክፍል ሥራህን ቀጥ ብለህ ሥራ
10ኛው ትዕዛዝ - እኔ ሥነግርህ አጠንጥን፤ “ፈተና ሲሰጥህ ተርትር”
11ኛው ትዕዛዝ - እናት አባትህን አክብር፡፡
*   *   *
ሀገራችን ብዙ ትዕዛዛትን ትሻለች፡፡ ትዕዛዝ አክባሪ ዜጋም ሊኖራት ይገባል፡፡ ከወሬ መላቀቅ ያስፈልጋታል፡፡ ሹም ሽር፤ የሥራ ኮንትራት መሆኑን ጠንክሮ ማስረዳት፣ መቆጣጠርና መከታተል የግድ መኖር አለበት፡፡ ሥርዓተ - አልባነት የወቅቱ አደጋ መሆኑንና ፈጦ - ገጦ መምጣቱን አስተውለን - “እናቴ ዕንቁላል ስሰርቅ ዝም ባላልሺኝ፤ በሬ ስሰርቅ ባልተያዝኩኝ” ያለውን ልጅ ማስታወስ ነው፡፡

የሥራ ባህላችንን ማጠንከር ግዴታ ነው፡፡ ግዴታችንን እንወቅ፡፡ የቤት ሥራችንን ለአፍ ወረት ብቻ አናውራ፡፡ የአሠራር ቦታ እንተው፡፡ መልሶቻችንን በግልፅ እናስቀምጥ! ህዝብ “የሥርዓት - ያለህ!” ብሎ እስኪጮህ አንጠብቅ፡፡ ትናንሽ የክፍል ሥራዎች ተጠራቅመው የአገር ችግር እስኪሆኑ ድረስ ዕድል አንስጥ፡፡

ከሁሉም በላይ ልብ መባል ያለበት የአገራችንን መላ - ችግር እንፍታ ካልን እንኳን ተጣልተን፤ ተፋቅረንና ተቧድነንም በቀላሉ የምንገላገለው እንዳይደለ ነው፡፡ ብዙዎች ከውጪ አገር ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆናቸውን አይተናል፡፡ ይሄ አንድ ሁነኛ ነገር ነው፡፡

ብዙ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንድ ፀሐፊ እንዳለው፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ እያንዳንዱ ተቃዋሚ እኪሱ ውስጥ ትንሽ ዘውድ ይዞ የሚዞር ነው፡፡ መቼ እንደምነግሥ አይታወቅም ባይ ነው!” ነገሩ ግን የመንገሥ ጣጣ ሳይሆን የሀገሪቱን ችግሮች አውጠንጥኖ ማወቅና አልጋ ባልጋ አለመሆኑን ተገንዝቦ መክሮ፣ ዘክሮ፣ ተቀናጅቶ፣ በጠላትነት ሳይፈራረጁ፤ ቅራኔ አፈታት አውቆ፤ ሽንፈትንም ድልንም ተቀብሎ መጓዝን መገንዘብ ነው፡፡

ዛሬ ዳር ቆሞ ተመልካች የማትፈልግ አገር ዘንድ እየደረስን ነው፡፡ ድርሻዬን እንዴት ላዋጣ? ከማለት ጀምሮ፣ እንዴት በአንድ ልብ እንሥራ? አንድ ትልቅ የአገር ጉዳይ ውጤት ባለው መልክ ዳር ለማድረስ አንዱ እየታገለ፣ ሌላው ዳተኛ እየሆነ፣ ፍሬ እናፈራለን ብሎ ማሰብ ዘበት ነው! የግድ ሀቀኛ ተዋናይ ሆኖ መድረኩ ላይ መገኘትን ይጠይቃል፡፡ ውሃ ዋና፤ ዳር ቆሞ አይሳካም፡፡ ያም ብርቱ ድካምን ይጠይቃል!  

የሁሉንም ተሳትፎ በሚሻ መልኩ የሁሉንም ርብርብ የሚፈለግበት ጊዜ ነው፡፡ አለበለዚያ፤ “አዳመጠች አረገዘችን አይሆንም” የሚለውን የአባቶች ብሒል መዘንጋት ነው! 
አዲስ አድማስ

No comments:

Post a Comment