Wednesday, September 28, 2011

የመስቀል ደመራ በዓል ዛሬ ተከበረ

(መስከረም 16 ቀን 2004 (አዲስ አበባ) -- የመስቀል ደመራ በዓል አዲስ አበባ ውስጥ በደማቅ ስነስርዓት ዛሬ ተከበረ፡፡

በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መስቀል የሰላም ምልክት መሆኑን ገልጸው ምእመናን በሰላምና በፍቅር እንዲሁም በመቻቻል በጋራ ድህነትን ሊዋጉ ይገባል ብለዋል፡፡

የእምነቱ ተከታዮች በተለይም ወጣቶች ሐይማኖታዊ በዓላትን ከማክበር ጎን ለጎን ለአገር እድገትና ለልማት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባቸውም ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ በበኩላቸው በዓሉን ብሔር ብሔረሰቦች ከጥንት ጀምሮ ያከብሩት እንደነበር አስታውሰው በዚህ በዓል ላይ የሚታየውን አንድነት በጸረድህነት ትግሉም ላይ አጠናክረን ልንቀጥልበት ይገባል ብለዋል፡፡

የሐይማኖት ተቋማትም ተከባብረው መንግስት የዘረጋውን የፀረ ድሕነት ስትራቴጂና የአምሰት አመቱን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማስፈፀም ከመንግስት ጎን ሊቆሙ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በበአሉ ላይ ተረኛ የሆኑት የማህደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርምና መድሃኒአለም ቤተክርስቲያን ካህናት እና የሰንበት ተማሪዎች ዝማሬ ያቀረቡ ሲሆን የፌዴራል ፖሊስ ማርሽ ባንድም በአሉን አስመልክቶ መንፈሳዊ ዝማሬዎችን አሰምቷል፡፡

በብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እና በብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ስርአተ ጸሎቱ ከተካሄደ በኋላም ደመራውን ብጹእ አቡነ ጳውሎስና ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ በጋራ ለኩሰዋል፡፡

በመስቀል አደባባይ በተከበረው በዚህ በዓል ላይ ጥንግ ድርብ የለበሱ መዘምራን፣ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካሕናት፣ ዩኒፎርም የለበሱ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና በአገር ባህል ልብስ የተዋቡ ምእምናን እንዲሁም በርካታ የውጭ አገር ጎብኝዎችና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  

No comments:

Post a Comment