Tuesday, July 31, 2018

ፍትህ እንጠብቃለን፤ ህልሙን እናሳካለን!

(July 31, (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት))--የዘመናት ቁጭት እና ቁዘማን ድል አድርገን ከሰባት ዓመት በፊት መገንባት ከጀመርነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በስተጀርባ ዘወትር ስማቸውን እናነሳለን፡፡ የጉባን ሃሩር፣ የቤተሰብን ናፍቆት ከፍተኛ የስራ ጫና በሚጠይቀው ፕሮጀክት የሚያጋጥመውን ውጣ ውረድ ተቋቁመው የቁርጥ ቀን ልጅ መሆናቸውን በማስመስከራቸው መላው የአገራችን ዜጎች በስስት ስናያቸው ቆይተናል፡፡

ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም ማለዳ በመስቀል አደባባይ በመኪናቸው ውስጥ በጥይት ተመትትው ሞተው መገኘታቸውን በሰማን ወቅትም ለማመን የተቸገርነው ለእዚህ ነበር፡፡

 የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ህልፈተ ሕይወት መራር እውነት ቢሆንም፤ እየተናነቀንም ቢሆን ተቀበልነው፡፡ እናም ትናንት እንደ ዓይን ብሌናችን የምንሳሳለት የታላቁ ፕሮጀክታቻንን ዋና መሃንዲስ ለዘላለም ተሰናበትናቸው፡፡ ሲቃ ከሚተናነቃቸው፤ እንባ ከሚያዘሩ ቤተሰባቸው፣ ወዳጆቻቸው፣ የስራ ባልደረቦቻቸውና ከበርካታ ዜጎች ጋር ሆነን ህይወታቸውን ካጡበት መስቀል አደባባይ ተገኝተን ለዘላለም ሸኘናቸው፡፡ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበትም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን በክብር እስከወዲያኛው አሳረፍናቸው፡፡

 እርግጥ ነው ጀግና ቢያልፍም በስራው ህያው እንደሚሆን እናውቃለን፡፡ ኢንጂነር ስመኘውም የሁሉም ዜጋ የላብ አሻራ ባረፈበት የህዳሴ ግድብ አማካኝነት ህያው ሀውልት ገንብተዋል፤ አቁመዋል፡፡ በእዚህም ለዘላለም በሁላችንም ልብ ይኖራሉ፡፡ ይሁንና መልሰን ላናገኛቸው የተሰናበትናቸውን የሀገር ባለውለታ በሸኘን ማግስት በተደጋጋሚ እየጎበኙን ያሉትን ችግሮች የምንረታባቸውና የጀግናችንን ህልፈተ ሕይወት የምንበቀልባቸው ሁለቱ ጉዳዮች ከፊት ይጠብቁናል፡፡

 የመጀመሪያውና ወሳኙ፤ ሀዘኑ ልባቸውን የሰበረውን ቤተሰብ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠብቀውን ከድርጊቱ በስተጀርባ ያለ ግለሰብም ሆነ አካል በፍጥነት በማጣራት በፍትህ አደባባይ የማቅረብ ጉዳይ ነው፡፡ አገሪቱ በህግ የምትገዛና የህግ የበላይነት የሰፈነባት ሆና እንድትቀጥል እስከተፈለገ ድረስ፤ በአደባባይ ወንጀል የሚፈጽሙ አካላት እንዳሻቸው የሚመላለሱባትና የሚፈነጩባት፣ እኩይ ድርጊት ፈጽመው የሚሸሸጉባትም መሆን የለባትም፡፡ ስለዚህ ያልዘገየ ፍትህ እንጠብቃለን፡፡

 በኢንጂነር ስመኘው ላይ የተፈፀመው ግድያ ተራ ወንጀል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያውያን ዓይን ያረፈበት የተስፋ ፕሮጀክት በመሆኑ ከበስተጀርባው ሚስጥር እንዳዘለ መገመት አይቸግርም፡፡ ከድርጊቱም በስተጀርባ እኩይ ዓላማ ያነገቡ ግለሰቦችና አካላት መኖራቸውን መገመት ቀላል ነው፡፡ ይህን በመፈፀም የእርስ በእርስ መጠፋፋት ድግስ ለሚያዘጋጁልንና በቀደዱት የጥፋት ቦይ እየፈሰስን አገር እንድትበታተን ለሚዶልቱልን፤ የቅርብ ሩቅም የውስጥም የውጭም ጠላቶች በራችንን በርግደን ከመክፈታችን በፊት ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት ብልሃት ወንጀለኞቹን መያዝ ተገቢ ነው፡፡ በእዚህም የቤተሰቡን እንባ ማበስ ያስፈልጋል፡፡ የፍትህ ያለህ የሚለውን ዜጋ ጥያቄ በፍጥነት ሊመለስ ይገባል፡፡

 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀከት የመላ አገሪቱ ዜጋ አደራ ነው፡፡ ለጋሾች ፊታቸውን ሲያዞሩብን ሳይተርፈን ከልጆቻችን ነፍገን፣ የራሳችን ምቾት ይቅር ብለን ከልጅ እስከ አዋቂ ገንዘባችንን እያዋጣን ጀምረነዋል፡፡ ‹‹እንችላለን!›› ብለን ጀምረን ዛሬ ለሚገኝበት ደረጃ አድርሰነዋል፡፡ ሁላችንም ፍጻሜውን ለማየት የምንጓጓ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ድርብ አደራ ተጥሎብናል፡፡

ኢንጂነር ስመኘው የኖሩለትና የሞቱለትን ዓላማ ከግብ በማድረስ የህዳሴውን ግድብ በማጠናቀቅ ህልፈታቸውን ህልማቸውን እውን በማድረግ መበቀል የትውልዱ ኃላፊነት ነው፡፡ ለእዚህም ከቀደመው በላቀ የእኔነት መንፈስና የሥራ ተነሳሽነት ግድቡን ከፍፃሜ ማድረስ ይገባል፡፡

 መላው የአገራችን ዜጎች በኢንጂነር ስመኘው ሕልፈት የተሰማንን ሀዘን የምንረታበት ትልቅ አደራ ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡ የፕሮጀክቱ ዋና መሃንዲስ ከጎናችን ቢለዩም፤ ሲጓጉለት የኖሩትን ሥራ ከፍፃሜ በማድረስ ሞታቸውን ድል መንሳት የእኛ ኃላፊነት ነው፡፡ ለእዚህም ልዩነታችንን አቻችለን በተባበረ ክንድ የከበቡንን ችግሮች ማስወገድ ይጠበቅብናል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ርዕሰ አንቀፅ )

No comments:

Post a Comment