Sunday, March 04, 2018

የዓድዋ ታሪክ ድል ብቻ ሳይሆን ዕዳም ነው

(Mar 04, (ኢትዮጵያ))--ምዕራባውያኑ አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመቀራመት በጀርመን በርሊን ከተማ ተማምለው ሲያበቁ ኢትዮጵያ በጣሊያን እጅ እንድትወድቅ ተፈረደባት፡፡ ጀግኖች አባቶቻችን ግን ዓድዋ ትፍረደን አሉ፡፡ የውጫሌ ስምምነት ይሏት አንቀፅ 17 እሳት አስጫረች፤ ጦር አማዘዘች በኢትዮጵያውያንና ጣሊያን መካከል 1888 ዓ.ም፡፡

በዚያን ወቅት ኢትዮጵያውያን ጦርና ጎራዴ ይዘው ለዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች እንግዳ የነበሩ አያቶቻችን፤ ከታንከኛና ከመድፈኛ ጋር ጦርነት የገጠሙ እጆች የሰማይ በራሪ አውሮፕላኖችን እያዳሸቁ እንኩትኩት ሲያደርጓቸው ዓለምን ጉድ አስብለው አፋቸውን አስያዙ፡፡ ፀሀፍትም ታሪኩ መራራ ቢሆንም ሊከትቡት ከብዕር ተናነቁ፡፡

የዓድዋ ድል ጦርነት ዝምብሎ ጦርነትን አሸነፈ ተብሎ የሚፃፍ፤ የሚዘከር አልነበረም፡፡ አንዲት ጠብታ ውሃ፤ ሰደድ እሳትን ከምድረ ገጽ እንዳጠፋች የሚነጻፀር እንጂ፡፡ በዓድዋ ጦርነት ወቅት በርካታ የክፍለ አገር ገዥዎች እኔ እገዛ እኔ እገዛ በሚል ጦር ተማዝዘው ጠዋትና ማታ እርስ በእርስ ይጠዛጠዙ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይሁንና ጠላት በመጣ ጊዜ የፖለቲካ ሽኩቻ አላገዳቸውም፤ የሃይማኖት ልዩነት አልታያቸውም፤የፆታ ነገር አልገደ ባቸውም፡፡ ሁሉም እምነቱ፤ ሃይማኖቱ፤ ሚስቱ፤ ርስቱ፤ ማንነቱ ሁሉ አገር ነበር፡፡ ማን በአገር ይደራደራል፡፡

አብዛኞቹ ጦርነቱ ሲጀመር ነገሩ የዳዊት እና ጎልድ ጨዋታ ይሆናል ብለው ገምተው ነበር፡፡ እንደ ነዲድ እንጨት ለእሳት ተማግደው፤ ‹‹ማን ያሸንፈኛል›› ብሎ ከፊታቸው ተሰልፎ የነበረውን የጠላት ጦር አብረከረኩት፡፡ ስንት ሕይወት ገብረው፤ በስንት መከራ ተፈትነው ይኸው ነፃ ትውልድ ተፈጠረ፡፡ አይ ጀግንነት፤ አይ ወኔ!

የዓድዋ ድልን ለኢትዮጵያውያን ሲያወሩት የሚያምር ለጠላት ግን እንኳንስ ሊያወሩት ቀርቶ ሲያስቡት መራር ነው፡፡ የዓድዋ ድል በእርግጥ ዘላለማዊ ድል ነው፡፡ የማይደበዝዝ፤ ፍትህ ለተጠሙ የሚያበረታታ የማይጎመዝዝ የፅናት ተምሳሌት ነው፡፡ ስለ ዓድዋ ዘላለም ቢጻፍ ቢተረክ የማያሰለች ከክፍለ ዘመን በፊት በጎልያድ እና ዳዊት መካከል የተካሄደ የጦርነት አምሳል ነው፡፡

በጦርነት ወቅት ንጉሠ ነገሥት ኢትዮጵያ አፄ ምንሊክ ጠላት በአገራቸው በመጣ ጊዜ ክብሬ፤ ማዕረጌ አላሉም፡፡ በሃሳብ የማይስማሟቸውን ሰዎች አላራቁም፡፡ በአገር ጉዳይ የጋራ ጠላት መጥቶብናል እና ኑ! አገራችንን ከወራሪ እናድናት ብለው ነበር ነጋሪት የጎሰሙት፡፡

የዓድዋ ድል ማለት ልዩ ክስተት ነው፡፡ በመሞት ውስጥ የኖረ ሕይወት ነው፡፡ የዓድዋ ድል ማለት በማይነገር ረቂቅ ትዕይንት ውስጥ በሚጣፍጡ ቃላት፤ አፍ በሚያስከፍት ድርሰት ተከሽኖ ጀግኖች የሚግባቡበት ቅቡል ቋንቋ ነው፡፡ ዓድዋ ማለት ለጨለመባት አፍሪካ የብርሃን ወጋገን ያሳየ ማለት ነው፡፡ ብቻ ዓድዋ! ማለት ከኢትዮጵያውያን በስተቀር ለቀሪው የዓለም ህዝብ ህልም የሚመስል ግን የተጨበጠ እውነት ነው፡፡ በቃ ዓድዋ ብዙ ነው!

በዚያን ወቅት የሮምን አደባባይ አስቧት፡፡ በሀዘን ማቅ ተውጣለች፡፡ በዚያን ወቅት አስቡት በዓድዋ ለአገራቸው ክብር መስዋዕት የሆኑ አባቶችና እናቶች አስከሬን ተረፍርፏል፤ ግን የጀግና አስከሬን! እንኳንስ በሕይወት ኖረው ሞተው የሚያርበደብዱ የሀበሻ ጀግኖች!

አባቶቻችን ለትናንት ማንነታቸው ሲጨነቁ የዛሬ ማንነታችንን አቆዩልን፡፡ የትናንት ታሪክን ላለማጉደፍ ሲዋደቁ፤ የእኛን ዛሬ ታሪክ አደመቁት፤ ለዛ አበጁለት፡፡

ዓድዋ ላይ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ደማቸውን አፍስሰው ነው ዛሬ የምንኖርባትን ምድር ያስረከቡን፡፡ የምንግባባበትን ቋንቋ፤ የምንጽፍበትን ፊደል፤ የምንቀኝበትን ዜማ፤ ያቆዩልን፤ ከባዕዳን ባህልና ቋንቋ የታደጉን በትዕግስትና በብልሃት እንጂ በለው፤ በለው! አሳድደው በሚል መርህ አይደለም፡፡

ወጣቱ ከቀደምት አባቶች አንዳች ነገር ሊማር ግድ ይለዋል፡፡ በዚህ ዘመን ጦርነት የለም፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓት ተዘርግቶ ብዙሃንን ጨፍልቆ የሚኖርበት እድል የተመናመነ ይመስለኛል፡፡ አባቶቻችን ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው አገርን ሊገነባ በሚችል አጀንዳ ላይ እንዴት እንደተጠመዱና ስምና ዝናቸውን አስከብረው እኛንም አስከብረው የኖሩ ስለመሆናቸው ማጤን ይገባል፡፡

ታዲያ ይህ ለዛሬው ትውልድ ዕዳ ነው፡፡ ወራሪን ከአገር ለማስወጣት በአንድነት ያበረ ክንድ በአሁኑ ወቅት የተገላቢጦሽ ሆኖ አንዱን ሰው ከሌላ ክልል የመጣህ ነው ብሎ ማሳደዱ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ሆኗል፡፡ ለመሆኑ ይህ ምን ይሉት ፈሊጥ ነው? አንዱ ያፈራውን ንብረት ሌላው እያወደመ አገሬ ብሎ ማቀንቀን ከወዴት የመጣ ፈሊጥ ነው? ታዲያ! ከ122 ዓመት በፊት የነበረ ንቃተ ህሊና ዛሬ ላይ ወደዬት ተሰወረ? እንኳንስ ለኢትዮጵያውያን ቀርቶ ለሚሊዮኖች የአፍሪካ ወንድምና እህቶች አርዓያ የሆ ነች አገር ስለምን ውጥንቅጦች ውስጥ እየገባች መጣች ብለን መጠየቅ ይገ ባል፡፡

እንደ ቅጠል ረግፈው ያቆዩልንን አገር እንደ ቄጠማ አለምልመን ማስቀጠል እንጂ ጊዜው እንዳለፈበት የባህር ዛፍ ቅጠል ከመሬት ላይ መወ ርወር የለብንም፡፡ ያሻገሩንን ባህር አል ፈን፤ ትንሽዋ ኩሬ አስምጣን እንዳታ ስቀረን ሁላችንም በንቃት ማየት አለ ብን፡፡ በእኔ እምነት ይህ ትውልድ በዓድዋ ድል ብቻ የመጣ ከፍሎ የማይጨርሰው ዕዳ አለበት፡፡ በዚያን ዘመን አንድነቱን አጠናክሮ ጠላቱን ያልፈለሰፈ ህዝብ ዛሬ እንደምን ድህነትን ማሸነፍ ይሳነዋል፤ እንዴት በባዶ እጁ በዓለም ጦረኛ የተባለን ሰራዊት ድባቅ የመታ ህዝብ የእለት ጉርስ ይቸግረዋል? እነዚያ አባቶቻችን ዛሬ ቀና ብለው ቢያዩን ምንኛ ባዘኑብን፤ ምንኛ በተቀየሙን! አፅማቸው ይወቅሰናል፡፡

በነገራችን ላይ የዓለም ታሪክ የአሸና ፊዎች ናት፡፡ ዓድዋ ላይ አሸን ፈናል፡፡ ግን ደግሞ አሁን ተሸንፈናል፤ ቁጭት ርቆናል፤ እልክ እና መነሳሳት ያንሰናል፡፡ በጉንጭ አልፋ ክርክሮች ተጠ ምደናል፡፡ ነገን ብሩህ ከማድረግ በዘለለ ትናንት ላይ ተጥደናል፡፡ ዓድዋን መድገም እንዴት ይሳነናል? ይህን ግን መለወጥ ግድ ይለናል፡፡ ሁላችንም በተመደብንበት ሞያና ኃላፊነት ላይ በአግባቡ ከሠራን ሁሌም ዓድዋ አለ፤ ከምንምነት ወደ ስልጣኔ ማማ ከወጣን ሁሌም ድል አለ፡፡

እኛ ለዚች ዓለም ህዝብ በውድ ዋጋ መሸጥ ከምንችለው ትልቁ ሃብታችን አንዱ የዓድዋ ድል ነው፡፡ ማንም ሰው ቢመጣ ‹‹ኮፒ ራይቱ›› የእኛ ብቻ የሆነ ነው የዓድዋ ድል፡፡ የዓድዋ ድል ብንሸጠው የማያልቅ ሃብታችን ነው፡፡ እናማ ኑ! እንሽጠው፡፡ ዓድዋን እናስ ተዋውቅ፡፡ ስለ ዓድዋ በተናገርን ቁጥር አልሸነፍባይነት ስነልቦናን በትውልድ ልብ ውስጥ ማኖር ነውና፤ በወጣቱ ልብ ውስጥ አይበገሬነትን ማንገስና ታሪካችንን መና ገራችን ነውና፡፡ የዓድዋን ድል ስንሸጠው ስንለውጠው ብንውል አይሰለችም፤ ምክንያቱም ውድ፤ ብርቅና ድንቅ ነው፡፡ የጠንካራ ስነልቦና ተምሳሌትና የማይ ንበረከኩ አልሞ ተኳሽ አባቶቹን ጀብድና ገድላቸውን ማን አልሰማ ይላልና! ዓድዋን እንዘክረው፤ እናስተዋውቀው፤ እንማ ርበት፡፡

ስለዓድዋ ድል ከተናገርነውና ብዙዎች ከተናገሩት፤ የታሪክ ድርሳናት ፍንትው አድርገው ከፃፉትና ከፃፍነው ሁሉ ገና ያልተነገረ፤ ገና ያልተጻፈ አለ፡፡ ወዲህ ደግሞ ይህን ታሪክ የሚያኮስስ ድህነት የሚባል ደንቃራ ከፊታችን ተገትሯል፡፡ እናም ታሪካችን ሙሉ ይሆን ዘንድ ዛሬም ነገም መትጋት አለብን፡፡

ዛሬ እየሞትን ሳይሆን እየኖርን ታሪክ መስራት የምንችልባቸው አጋጣ ሚዎች በርካቶች በመሆናቸው ሁላችንም ኃላፊነ ታችን ልንወጣ ይገባል፡፡ በትናንት ታሪክ ብቻ የምንኩራራ ህዝቦች ሳንሆን፤ ከትናንት ታሪክ የሚቀጥል ሌላ የታሪክ ምዕራፍ መክፈት ይገባናል፤ ግዴታችንም ነው፤ እርሱም ድህነትን ታግሎ ማሸነፍ፡፡ የሆነው ሆኖ ግን በ21ኛው ክፍለዘመን ውስጥ ሆነን እንደ 19ኛው ክፍለ ዘመን ማሰብ ግድ ባይለንም ታሪክን መዘንጋት ግን አይገባም፡፡ በዚያን ዘመን ግፍ እና ሰቆቃ ያደረሱብንን ሰዎች አንርሳቸው፤ ቂም ግን አንያዝባቸው፡፡
(ክፍለዮሐንስ አንበርብር, (ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት))

No comments:

Post a Comment