Saturday, February 03, 2018

ብሄር ተኮር ጥቃትና አውዳሚነት ከኢትዮጵያውያን ባህልና እሴት ያፈነገጡ እኩይ ተግባራት ናቸው!

(Feb 03, (ኢትዮጵያ ))--በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ክቡር ሰማዕታት የደምና ህይወት ዋጋ ሀገራችን የዴሞክራሲ፣ የልማትና የብልጽግናን መስመር ይዛ መንጎድ ከጀመረች አስርት ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ በዚህ ሂደት ብዙ የችግር ማጦችን ተሻግረን ተቀብረንበት ከነበረው የድህነት አረንቋ አንገታችንን ቀና አድረገን የብልጽግናን አድማስና መዳረሻ መመልከት ችለናል፡፡

ዛሬ ዓለም ስለእኛ የሚያወራው ተራቡ፣እርስ በርስ ተላለቁ፣ የኋላቀርነት ምሳሌ ናቸው ብሎ ሳይሆን በሰላሟ ተመራጭና ለአፍሪካውያንም መከታ የሆነች፣ በኢኮኖሚ ዕድገትና ብልጽግና ከቀዳሚዎች ተርታ ፊት የተሰለፈች ሀገር በማለት ሆኗል፡፡

የአንድ ብሄር የበላይነትን እንዳይፈቅድ ሆኖ የተገነባው ፌዴራላዊ ስርዓታችን ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቤተኛ አድርጓቸው ለልማቷ በአንድነት ለመትጋት ለሉዓላዊነቷ በጋራ ለመቆምና ለመሰዋት የቆረጡ ህዝቦች ሀገር አድርጓታል፡፡ ክብር ለፌዴራላዊ ስርዓታችን ይሁንና ዛሬ ኢትዮጵያ በቀላሉ የምትቆረጠም ጥሬና በአፍራሽ ኃይሎች ጩኸት የምትበታተን ሀገር ሳትሆን ስትናገር ብዙ ሰሚ ጆሮ ያላት ከራሷም አልፋ ለጎረቤትና ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮችም የሰላም ጠበቃ የሆነች ታላቅና ክቡር ሀገር ሆናለች፡፡ በጀግናው የመከላከያው ሠራዊታችን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እልቂት ስጋት ድነው በአንፃራዊነት ሰላማዊ እንቅልፍን የሚተኙ እልፍ አፍሪካውያንም የፌዴራላዊ ስርዓታችን ፍሬ ተቋዶሾች ናቸው፡፡

ለዘመናት የተከመረብን ድህነትና ሳንሠራ እርስ በርስ ስንተላለቅ የኖረንበት ዘመን ያሸከመን የልማት የቤት ሥራዎች በርካታ ናቸውና ህዝቦችን አሁን ለሚፈልገው ደረጃ የሚመጥን ሀብት አላፈራንም። ዴሞክራሲያችንም ብዙሃነትን መሰረት ያደረገና በእንጭጭ ደረጃ ያለ በመሆኑም በሚፈለገው ልክ የህዝቡን ጥማት አስታግሷል ተብሎ አይወሰድም፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም በተግባር ግብዓተ መሬታቸው የተፈፀመ በአስተሳሰብ ግን ከአንዳንድ ጥገኞች አዕምሮ ያልተፋቁ የጠባብነትና የትምክህት አስተሳሰቦችም አሁንም የሀገሪቱ የህዳሴ ጉዞ ደንቃራ ሆነው አፈር ልሰው ለመነሳት የሚውተረተሩበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡

በዚህ ሂደት የሥራ ዕድል ይፈጠርልኝ፣ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የሚመጣጠን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ይስፈን፣ ዴሞክራሲ ይዳብርን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢም አስፈላጊም ነው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በአንክሮ ማድመጥና ተገቢውን ምላሽ መስጠትም ከመንግሥት የሚጠበቅ ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ነው፡፡ ይሁንና ይህንን አስታኮ በስመ «የመልካም አስተዳደር ችግር አለ»፣«በቂ የሥራ ዕድል አልተፈጠረልኝም» ወዘተ መነሻነት የልማት አውታሮችን ማፍረስ፣ ዘር እየለዩ ዜጎችን ማሳደድና ማጥቃት ግን ከኢትዮጵያዊነት እሴትና ባህል ያፈነገጠ፣ ዕድገታችንን የሚያጠለሽ የጨለምተኝነትና የእኩይነት መገለጫ ነው፡፡ ልማትን እያወደሙ በቂ መሰረተ ልማት አልተገነባልኝም፣ በዜጎች ላይ የብሄር ተኮር ጥቃት እየፈፀሙ መብቴ በበቂ ስላልተከበረልኝ የሚል ሰይጣናዊ ተግባር ግን በማንኛውም መልኩ በጥብቅ የሚወገዝና አስፈላጊውና አስተማሪ ቅጣት ሊጣልበት የሚገባ አስፀያፊ ተግባር ነው፡፡

በቅርቡ በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢዎች በተነሱ ግጭቶችም በድሃ አቅማችን የገነባነውን ታላላቅ የልማት አውታሮችና የግለሰቦችን ሀብት የማውደም ብሎም ዜጎችን በማንነታቸው እየለዩ ማጥቃትን የመሳሰሉ እርኩስ ተግባራት መከሰታቸውን ከየአካባቢው የሚወጡ መግለጫዎች ያመለክታል፡፡

ይህ እኩይ ተግባር ሰይጣናዊ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ጥቂት የጥፋት ኃይሎች ሥራ ቢሆንም ለዘመናት ተፈቃቅረውና ተቻችለው እንኳን የሀገራቸው ልጅ የሆነን ኢትዮጵያዊ ቀርቶ ለየትኛውም የአዳም ዘር በችግር ጊዜ ጥላ ከለላ በሆኑ ጨዋና ታላቅ የሀገራችን ህዝቦች ላይ ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ በቀላሉ የሚፋቅ አይሆንም፡፡ ይህንን ተግባር የሚፈጽሙ ኃይሎችም ያለምንም መሸፋፈንና መደባበቅ እኩይ ተግባራቸውን ከሚወሰድባቸው ተገቢና ህጋዊ ቅጣት ጋር በይፋ ካልተገለጹ በህዝቦች ትስስርና በሀገራዊ ህልውናችን ላይ ሊፈጥር የሚችለው ፈተና ከግምት በላይ ነው፡፡ ከእዚህ የጥቂት የጥፋትና ከኢትዮጵያውያን ባህልና እሴት ያፈነገጠ ተግባር በተቃራኒው ዜጎች በማንነታቸው የተነሳ ጥቃት እንዳይደርስባቸው ፊት ለፊት ተጋፍጦ በመከላከልና ተጎጂዎችን በመርዳትና በማቋቋም ብሎም ከመከላከያና የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ወጣቶችን ከስሜታዊነት እንዲርቁ በመምከርና ሁከትን በመከላከል ረገድ በርካታ ዜጎች ያደረጉት በጎና ኢትዮጵያዊነትን የሚመጥን ተግባር ምስጋና ሊቸረውና አርአያነቱና ትምህርታዊነቱ በሌሎችም ይሰርጽ ዘንድ ሊጎላ የሚገባው ነው፡፡

 እርግጥ ነው! የኢትዮጵያ ህዝብ ክቡር ህዝብ ነው! ስለዚህም ነው ለዚህ ክቡር ህዝብ ልዕልና እና ህልውና ሺዎች በጀግንነት ህይወታቸውን የሰጡትና እየሰጡም ያለው። የዚህን ክቡርና ታላቅ ህዝብን ጥያቄና ፍላጎት ማዳመጥና ተገቢውን ምላሽ መስጠት ምንጊዜም ወደ ኋላ ሊባል የማይቻል ተግባር ነው፡፡ ይሁንና እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባ ዋና ጉዳይ ግን ህዝቡ የሚያነሳው ጥያቄ ሁሉ በአንድ ጀንበር ምላሽ የሚሰጥበትና የሚፈታ ሳይሆን ከሀገሪቱ አቅም ጋር ተያይዞ ወዲያውኑ የሚፈታው ወዲያው፤ አቅምና ጊዜን የሚጠይቀው ደግሞ ጊዜውን ጠብቆ በተገቢው መንገድ የሚፈታ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ህዝቡም ይሄን ጉዳይ በሚገባ ማጤንና ጥያቄዎችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ ማቅረብ ሁሌም ሊተገብረው የሚገባው ጉዳይ ሊሆን ይገባዋል፡፡

ያለፉት 26 ዓመታት ታሪካችን መንግሥትና ህዝብ ከተቀራረቡና ከተወያዩ የማይፈቱት ችግር እንደሌለ በትልቁ አስተምሮናል፡፡ በእስካሁኑ ሂደታችንም የሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት ተጠብቆ እዚህ ደረጃ የተደረሰውም ተግዳሮቶች ጠፍተውና መንገዱ ሁሉ አልጋ ባልጋ ሆኖ ሳይሆን በገጠሙ ችግሮች ዙሪያ መንግሥትና ህዝብ በአንድ ላይ ተቀምጠው ስለመከሩና የጋራ የመፍትሔ አቅጣጫም አስቀምጠው በጋራ በመንቀሳቀሳቸው ነው፡፡

ሀገራችን ብዝሃነት ያለባትና በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የምትገኝ ሀገር እንደመሆኗ ዛሬም ሆነ ወደፊት የህዝብ የልማት፣የዴሞክራሲና የተጠቃሚነት ጥያቄ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጥርጣሬ የለም፡፡ እነዚህን ጥያቄያዎችም በዴሞክራሲያዊ አግባብ በውይይት እየፈቱ የሀገርን ህልውና ሰላም አጠናክሮ ማስቀጠሉ ለአፍታም ቸል ሊባል አይገባም፡፡ ከዚህ በተቀራኒው ግን በስመ የህዝብ ጥያቄ እጅን ወደሀገርና ህዝብ ሀብት ውድመት መሰንዘር ብሎም ዜጎችን ብሄር ለይቶ የማጥቃት እኩይ ተግባር ግን እንዳይደግም ተደርጎ ለአንዴና ለመጨረሻ አስተማሪ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል እንላለን፡፡
ርዕሰ አንቀፅ (ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)                                

No comments:

Post a Comment