Sunday, January 28, 2018

ከጥላቻ እንውጣ

(Jan 28, (ኢትዮጵያ ))--በሀገራችን ባልተጠበቀ ሁኔታ እየተከሰተ ያለው ሁከትና ብሄር ላይ ያተኮረ ግጭት፤ ይህንንም ተከትሎ የሚስተዋለው አመጽ፣ ንብረት ማውደምና የሰው ሕይወት መጥፋትን የመሳሰሉ ቀውሶች መፈጠራቸው መንግስትንም ሕዝብንም ከልብ ያሳዘነ ድርጊት ሆኗል፡፡

ለዚህ ከመነሻው ጀምሮ የዚህ አይነቱ ግጭት እንዲነሳ ሆን ብለው በመስራት እልቂትና ደም መፋሰስ እንዲከሰት ሲጥሩ የነበሩ አንዳንድ አካላት የተጫወቱት ሚና ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ለጉዳዩ መባባስና መልኩን ቀይሮ መከሰት የተጫወቱት የዘረኝነት ሚና፤ የረጩት የከፋ የጥላቻ መርዝ ሰውን በሰውነቱ፤ በዜግነቱ ከማየትና ከመመልከት፤ ለሰውኛ መብቱ ከመቆምና ከመከራከር ይልቅ የግለሰቦችን የግል አለመግባባትና ግጭቶች ሁሉ ወደ ጎሳና ብሄር እየለወጡ የተሳሳተ ትርጉም በማስያዝ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ እንዲወጡ ለማድረግ ይህ ቀረው የማይባል ጥረት አድርገዋል፡፡

ከአብሮነትና ከተለመደው ተከባብሮ የመኖር ኢትዮጵያዊነት ውጪ ሙሉ በሙሉ ባፈነገጠ መልኩ ለአንድ ዘር ወይንም ጎሳ ከእኛ በላይ ተቆርቋሪ የለም በሚል፤ የሌላውን ብሔር ብሔረሰብ በማጥላላትና በማንቋሸሽ ስሜታዊ ሆኖ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲሄድ የበቀልና የኃይል እርምጃ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ረገድ በየሶሻል ሚዲያው የተጫወቱት ሚና ሊገለጽ ከሚችለው በላይ ነው፡፡

ተው አደጋው ለሁሉም ይተርፋል፤ የሚበጀው በሰላምና በፍቅር አብሮ መኖር ነው ተብለው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ቢነገራቸውም የሚሰሙ አልሆኑም፡፡ እንዲያውም ይህንኑ ነውረኛና ዘረኛ ስራቸውን እንደ ጀግንነት ቆጥረው በይፋ ድፍን ሕዝብ እስከ መዝለፍ መሳደብ የእኛ ዘር የተለየ ነው እስከማለት የደረሱ፤ ከጣሪያ በላይ የገዘፈ ጩሀት የሚያሰሙበት በአምሳያዎቻቸው አይዟችሁ የሚባሉበት ሁኔታ መከሰቱን ሁሉ ተመልከተናል፡፡ ቢያስቡ ኖሮ ሕዝብ ይከበራል እንጂ አይሰደብም፤ አይንቋሸሽም ነበር።

አንድ ሰው ሲበደል ግፍ ሲፈጸምበት ሰው በመሆኑ ብቻ ልንቆምለት ለመብቱም ልንከራከርለት ይገባል፡፡ ሁሉም የሰው ዘር በሕግ ፊት እኩል ነው የሚለው ብሔራዊም ሆነ አለም አቀፋዊ መርሕ ተገቢና ትክክለኛም ነው፡፡ ከእከሌ ጎሳ ከእከሌ ዘር ስለተፈጠረ ስለተወለደ የምንጠብቀው፤ ከሌላ ዘርና ጎሳ በመወለዱ በመፈጠሩ የምንጠላው የምናጠቃው ከሆነ ለሀገርም ለሕዝብም አብሮነት፤ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ አደጋን ያስከትላል፡፡ አሁን የተከሰተው አካሄድም ይሄው ነው፡፡ ፈጥነን ተረባርበን ልንመክተው ካልቻልን በስተቀር፡፡

በሕዝብ ስም የሚነግዱ አንዱን ከአንዱ የሚያጋጩ ወንጀለኞች የመጨረሻው ግባቸው እልቂትና የእርስ በእርስ ግጭት ተፈጥሮ ሀገር ሰላምዋ ተናግቶ ሕዝቡ እንዲተላለቅ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ የኖረ የእነ ግብጽ የእነ ኤርትራ ቀዳሚ አላማና ኢትዮጵያን እንበታትናል ብለው ሲሰሩበት የኖሩት ሴራ ነው፡፡ሴራውም ኢትዮጵያን ለማጥፋት የታቀደ  ነው፡፡

በውስጥ ያለውና መፈታት ያለበት ሀገራዊ ችግር በውስጥ የሚፈታ ቢሆንም ይሄንን እንደ ማቀጣጠያ ነዳጅ በመጠቀም የራሳችንን ዜጎች በውስጥ በማሰለፍ በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ ወኪሎችን በመመልመል የእርስ በእርስ የጎሳ ግጭት እንዲነሳ በተማሪዎች መካከል ግጭትና መጠፋፋት እንዲከሰት የሶሻል ሚዲያ ሠራዊት በማሰማራት ሰፊ ስራ እየሰሩ ያሉት ግብጽ ከኤርትራ ጋር በመቀናጀት ነው፡፡

ይሄንን የኖረና ግዜን ጠብቆ እየተከወነ ያለ ሀገር አጥፊ ሴራ ኢትዮጵያውያን በቅጡ ተረድተን ልንመክተው ካልቻልን ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሴራ ሀገራችንን አሳልፈን ሰጥተናል ማለት ነው፡፡ ይህን ቀድሞ አውቆ መከላከል ሀገርንና ሰላምዋን መጠበቅ ጠላቶቻችን በዘረጉት ወጥመድ ተጠልፈን ሀገራችንን ለውደቀት ከመዳረግ መቆጠብ ይገባናል፡፡

የዘርና የጎሳ ፖለቲካ በሽታን ማስወገድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ በየትኛውም ማእዘን ሰርቶም ሆነ ተምሮ ንብረት አፍርቶ ወልዶ ከብዶ ተዘዋውሮ የመስራት፤ የመኖር መብቱ እንደቀድሞው ሁሉ በፍቅር በመተሳሰብ በቤተሰባዊነት እንዲቀጥል ማድረግ መቻል አለብን፡፡ እርስ በእርስ በመናቆር፣ ሀገራችንን በማጥፋት ለግብጽና ለሻእቢያ ሴራ ሲሳይ መሆን የለብንም፡፡

አንድ ሰው ጥፋት  አጥፍቶ ቢገኝ መጠየቅ ያለበት በግለሰብነቱ ራሱ በፈጸመው ድርጊት እንጂ በጎሳው ወይም በዘሩ መሆን የለበትም፡፡ ይህ በየትኛውም አለም ሕግ የጸደቀና የሚሰራበትም ነው፡፡ ሕዝብ ከሕዝብ አይጋጭም፡፡ አይጠላላም፡፡ መነሻ ምክንያት የሚሆኑት ሁልግዜም በተሳሳተ መንገድ የሚራመዱ ግለሰቦች ናቸው፡፡ የግለሰቦች ስሕተትና ጥፋት እንደ ሕዝብ ጥፋት ሊታይ፤ ሊወሰድ የሚችልበት የሕግ መሰረትም የለም፡፡

ሰው ከእንስሳት ተለይቶ የማሰብና የማመዛዘን ባሕርይ ያለው ፍጡር ነው፡፡ መጠፋፋት፣ መበላላት፣ መገዳደል፣ ጎራ ለይቶ መፋጀት በተለይ የአውሬዎች አይነተኛ ባሕርይ ቢሆንም ምክንያታዊነት በሌለበት፣ ማስተዋልና ሚዛናዊነት በጠፋበት በጅምላ በስሜት መነዳት በሚነግስበት ወቅት ሰውም ልክ በሩዋንዳ እንደተፈጠረው የሁቱና የቱሲ ጎሳዎች ትርጉም በሌለው ሁኔታ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ እንደተላለቀበት የዘር ፍጅት አይነት  ሲፈጥር አይተናል፡፡

ከዚያ ሁሉ ሰቅጣጭ እልቂት ርዋንዳ በኋላ እንደገና ሀገሪቱ አንድ ብላ አቧራ አራግፋ ተነሳች፡፡ እንደገና ሕይወት ቀጠለ፡፡ ዛሬ ላይ ለምን ያ ሁሉ ሆኖ በፍቅር መኖር እያቻልን መቻቻል ተስኖን ነበር ብለው ቢጸጸቱም ያለቀውን ሕዝብ፣ የወደመውን ንብረት ሊመልሱት ግን አልቻሉም፡፡ የውጭ ኃይሎችም ያ ሁሉ እልቂት ሲፈጸም ፈጥነው በመድረስ ሊገቱት አልቻሉም፡፡ እንዲውም ዛሬ ላይ የነበራቸውን ሚና የሚገልጹ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡

ይህ አይነቱ  አስከፊና ዘግናኝ ሁኔታ በሀገሩ ላይ እንዲከሰት የሚፈልግ ማንም አይኖርም፡፡ በዚህ የከፋ ተግባር የተጠመዱትን ሕዝብን ከሕዝብ ማናቆር፣ ማጋጨትና ማባላት የሚፈልጉትን ከወዲሁ ሳይረፍድ ማስታገስ ተገቢ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎቻችን የተፈጠረው ሁከትና ተቃውሞ መነሻም ከዚሁ አይነት የብሄር ግጭት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ በጎሳው በዘሩ ምክንያት ለጥቃት መዳረግና መሞት የለበትም፡፡ ይሄንን ያደረጉትን መንግስት ተከታትሎ ሕጋዊ ተጠያቂነትን ማስፈን መቻል ይጠበቅበታል፡፡ በአደባባይ ለፍርድ መቅረብም አለባቸው፡፡ ሌላው ሊማር የሚችለው በዚህ መልክ ብቻ ነው፡፡

የትምህርት ተቋማት እውቀት የሚቀሰም ባቸው አብሮ መኖር መቻቻል መተዋወቅ ማሕበራዊ ሕይወትን በጋራ መካፈል የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ልጆች በጋራ አንድ ማእድ የሚቆርሱበት እንጂ እጅግ ኋላቀር በሆነ የጎሳ ፖለቲካ መነሻነት የሚባሉበት መድረክ ከቶውንም ሊሆን አይገባውም፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የሰው ልጅ ከምድር አልፎ ሕዋ ላይ ለመኖር እየታገለ ባለበት፣ ምጡቅ ቴክኖሎጂ በሰፈነበት ዘመን የዘርና የጎሳ ፖለቲካን ማቀንቀንን ቀዳሚ አጀንዳ ማድረጋችን ምን ያህል ከአለም ወደኋላ የቀረን መሆናችንን ያሳያል፡፡

ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ክቡር ነው፡፡ በመሰረቱ ማንኛውም ሰው ከእከሌ ጎሳ ልወለድ ብሎ ማመልከቻ አቅርቦ የተወለደ በአለም ላይ የለም፡፡ ከየትኛው ዘር ጎሳ ይወለድ ሰው ሁሉ በእኩልነት ሰብአዊ መብቱ ሊከበርለት፤ ሊጠበቅለት ይገባል፡፡ ይህ የሞተ፣ ያረጀና ያፈጀ አስተሳሰብ ሀገርንና ትውልድን ይገድላል፡፡ በመሆኑም “ሳይቃጠል በቅጠል” ሊሆን ይገባልና ከወዲሁ ማሰብ ተገቢ ይሆናል።
ይልቃል ፍርዱ (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)
 

No comments:

Post a Comment