Sunday, January 28, 2018

ሰላም ! አሁንም ሰላም!

(Jan 28, (ርዕሰ አንቀፅ))--ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው። ሰላም ከሌለ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም። ልማት ፣ ዴሞክራሲ ሌላም ሌላውም ሊኖርና ልናጣጥመው በጎደለውም ላይ ልንሞላበት የምንችለው ሰላም ካለ ብቻ ነው። ሰላም ከሌለ በህይወት መኖርና የትውልድ ቀጣይነት ሁሉ ጥያቄ ውስጥ የሚወድቅ ይሆናል። ስለዚህ ሰላም ለማንም ለምንም ነገር ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለን መደምደም እንችላላን። ይህንን ማወቅ ይገባል። ሰላም ከሌለ ደግሞ የሚመጣውን አደጋ አስቀድሞ ማሰብና ማለም ይገባል።

አገራችን ባለፉት ስርዓቶች ከምትታወቅበት ድህነትና የጦርነት ታሪክ ወጥታ በልማትና እድገት ጎዳና ተጠቃሽ መሆን የቻለችው ከምንም ነገር ቀድሞ በአገራችን ሰላም በመስፈኑ ነው። ሰላማችንን በእጃችን በመጨበጣችን መታወቂያችን የሆነውን ድህነትን ከስር መሰረቱ መገርሰስ ባንችል እንኳን ከአናት አናቱ እየቆረጥን ለመጣል የምንችለውን ሁሉ ጥረት እንድናደርግ ረድቶናል። ለዚህም ነው ፊታችንን ወደ ጦርነት ሳይሆን ወደ ልማት አዙረናል የምንለው። አሁን ላለንበት የዕድገት ደረጃ ለመድረስም በሀገራችን የሰፈነው ሰላም የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝም ለማንም ገልጽ ነው።

ይሁንና በጥባጭ እያለ ማን ጥሩ ይጠጣል እንደሚባለው በሀገራችን ውስጥ ሰላም መኖሩ ፣ለልማት አጀንዳ ሰፊ ጊዜ መስጠታችንና የልማት ባለቤት መሆናችን የቆጫቸው ሃይሎች ግን ትናንትም ሆነ ዛሬም ዝም ብለው አልተኙልንም። ነገም አይተኙም። በውስጠ አሰራራችን ጭምር እየገቡ እገሌ በእገሌ ተጎዳ ዓይነት በሬ ወለደ ወሬያቸውን ጭምር ሲነዙ፤ ተስማምቶና ተሳስቦ የኖረውን ህዝብ አንዱን ብሄር በሌላው ላይ ለማነሳሳት ሲቆፍሩ በየዕለቱ እያስተዋልናቸው ነው። ይሄ ተግባራቸው እናንተ አይናችሁን ጨፍኑ እኛ እናሞኛችሁ ከሚል የዘለለ እንዳልሆነ ልብ ማለት ይገባል።

 የፌዴራል ስርዓቱ ለአገሪቱም ሆነ ለህዝቧ ብቸኛውና የተሻለ አማራጭ መሆኑ ታምኖበት ወደ ስራ ሲገባ በአገሪቱ የነበረው የልማት እንቅስቃሴ ፣ የኢኮኖሚ ደረጃ ፣ የጤናና የትምህርት ዘርፉ እንዲሁም ሌላውም ማህበራዊ አገልግሎት ጭምር በምን ደረጃ ላይ እንደነበር ራሱ ህዝቡ የሚመሰክረው ጉዳይ ነው። ይሄ ማለት ግን በዚህ ሁሉ ልማትና የዕድገት ሂደት ውስጥ ምንም አይነት ችግሮች አልነበሩም ማለት አይቻልም። የመልካም አስተዳደር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ ከዛም አልፎ የጎጠኝነት፣ የጠባብነትና ትምክህት አስተሳሰቦች ነበሩ። ህዝብን እንደ ህዝብ ከማየት ይልቅ የወገንተኝነት ስሜቶችም ተንፀባርቀዋል።

ያላግባብ ተጠቃሚነትም ማሳያ የሆነ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርም እንዳለ ከህዝቡ በሚሰሙ ቅሬታዎች ማረጋገጥ ይቻላል። ይህንን መንግሥትም እንደመንግሥት ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም እንደ ፓርቲ ያመኑት ነው። ችግሩን አምነው ብቻም አልተቀመጡም፤ ህዝባዊ ሃላፊነት፣ ተጠያቂነትም አለባቸውና ችግሩ ምንድነው መፍትሄውስ በማለት ጥልቅ ተሀድሶ አድርገው የችግሮቻቸውን መፍቻ ቁልፍ ለይተዋል። እርምጃም መውሰድ ጀምረዋል።

በሙስናና በመልካም አስተዳደር የተጠረጠሩትን ህግ ፊት በማቅረብ ጭምር ጅምር ስራዎች ታይተዋል። ሆኖም ግን አሁንም የችግሩ ሰንኮፍ አልተነቀለም የሚል የህዝብ ቅሬታዎች በየአቅጣጫው እየተደመጠ ነው። ሁከትና ብጥብጥ ቢቀንስም አልፎ አልፎ ብልጭ ድርግም የሚልበት ሁኔታ አለ። ይሄ ደግሞ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እያስከተለ ለሰላም መደፍረስ ምክንያት እየሆነ ነው።

 አሁን አንድ ነገር ላይ መነጋጋር ይቻላል። የፖለቲካ አመራሩም ሆነ መንግሥት በመልካም አስተዳደር፣ በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ በሌሎችም በኩል የሚታዩ ችግሮች አሉ ብሎ በማመን ይሄንን ለመፍታት እየሰሩ መሆኑን፤ እስካሁንም ለተፈጠሩት ችግሮች በወቅቱ መፍትሄና ተገቢነት ያለው ምላሽ አለመሰጠቱ ስህተት መሆኑን በመቀበል ህዝብንም ይቅርታ በመጠየቅ ጭምር ወደ ሥራ ተገብቷል።

ሆኖም ግን ለብዙ ዓመታት የቆየን ችግር በአንድ ቀን መፍትሄ መስጠት እንደሚከብድም ሊታወቅ ይገባዋል። ለሁሉም ሥራ የሚፈልግ ዜጋ የስራ ዕድል በአንድ ሌሊት ተፈጥሮ አያድርም። ጊዜን ይጠይቃል በጀትንም ይፈልጋል። ብሎም አመራር መስጠትን እንዲሁም ቁርጠኛ ፈፃሚና ቅን ልቦና ያለው ተገልጋይ ያስፈልጋል። ይሄ ሲሆን በጊዜ ሂደት ችግሮች እየተቃለሉ ይሄዳሉ። የሥራ ዕድሎችን ለማስፋፋት የውጪ ባለሀብቱን ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ሰላም ያስፈልጋል። ለሀብት ንብረታቸው ዋስትናን ይፈልጋሉ። ይሄ የሚሆነው ደግሞ በሁሉም አካባቢ ሰላም ሲሰፍን ነው።

 ነገር ግን የስራ ዕድል በአንድ ወቅት በአንድ ጀንበር አልተፈጠረም ብሎ በየሀይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ላይ ፀብያለሽ በደቦ ብሎ መነሳት ለማንም አይጠቅምም። የጥምቀት በዓልን ተከትሎ ሰሞኑን በወልዲያና በቆቦ በተፈጠረው ብጥብጥ የሰው ህይወት ጠፍቷል። ንብረትም ወድሟል። የሞቱት ወንድም እህቶቻችን ናቸው። በእነሱ ሞት አገርም እንደ አገር ዜጋም እንደ ዜጋ ተጎጂ እንጂ ተጠቃሚ የሆነ የለም።

ምናልባትም ተጠቃሚዎቹ ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት ህዝብን በህዝብ ላይ የሚያነሳሱት ጠላቶች ይሆናሉ። የእኛ ሰላም ማጣት ለእነሱ ሰርግና ምላሽ ነውና በዜጎች ሞትና ቁስል ሲሳለቁና ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለመሸመት ሲራወጡ እያስተዋልን ነው። ስለሆነም እንደ ዜጋ ይሄን መረዳትና ከአፍራሽ ተልዕኳችሁ ታቀቡ ልንላቸው ይገባል። ከብጥብጥ የሚተርፍ ነገር የለምና ሁሌም ለራሳችንና ለአገራችን የሚበጀውን እናድርግ። ያሰብንበት ለመድረስ ፣በልማት ጎዳናዎች ለመገስገስ ሰላም መተኪ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ደግመን ደጋግመን እናጢን። ዛሬም ነገም ሰላም ወሳኝ ጉዳይ ነውና ለሰላም ዘብ እንቁም እንላለን!
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

No comments:

Post a Comment