Thursday, November 09, 2017

ችግር ሁሉ የሚነሣው ከአጥንት በላይ ማሰብ በማይችሉ ውሾች የተነሣ ነው

(ኅዳር 1, 2010, (አጀንዳ))--በኦሮምኛ እንዲህ የሚል አንድ ተረት አለ። አንድ የኦሮሞ መንደር ውስጥ ሮቤል መገራ የሚባሉጥበበኛ ሽማግሌ ነበሩ፡፡ አንድ ቀን የሁለት ጎረቤታሞች ንብረት የሆኑ ሁለት ውሾች ሲጣሉ ያያሉ፡፡ እኒህ ጥበበኛ ሽማግሌም «እነዚህን ውሾች እንገላግላቸው፤ ያለበለዚያ ችግራቸው ለሁላችንም ይተርፋል።

በዓለም ላይ ችግር የሚነሣው ከአጥንት በላይ ማሰብ በማይችሉ ውሾች የተነሣ ነው» ይላሉ፡፡ በአካባቢው የነበሩ ሽማግሌዎች እና መንገደኞችም በሽማግሌው አባባልተገርመው «ሁለት ውሾች ተጣልተው ምን ሊያመጡ ነው» እያሉ ሳቁባቸው፡፡ በዚህ መካከል ከሁለቱ ጎረቤታሞች መካከል አንድ ልጅ ወጣና የውሾቹን ጠብ ተመለከተ፡፡ የእርሱ ውሻ የተበደለ ስለመሰለው ፍልጥ አምጥቶ ያኛውን ውሻ ደበደበው፡፡

ወዲያውም ከሌላኛው ቤት ሌላ ልጅ ወጣና ያኛውን ውሻ መደብደብ ጀመረ፡፡ ነገሩ ወደ ሁለቱ ልጆች ተዛመተና በውሾቹ ምትክ ልጆቹ ይደባደቡ ጀመር፡፡ ሽማግሌውም «እባካችሁ እነዚህን ልጆች አስታርቁ» አሉ፡፡ በሥፍራው የነበሩትም «ተዋቸው ይዋጣላቸው» ብለው እንደ ቀልድ አለፉት ልጆቹ እየተደባደቡ እያሉ የአንዱ እናት ብቅ አለች፡፡ ወዲያውም ያኛውን ልጅ በፍልጥ ታንቆራጥጠው ጀመር፡፡

የልጇን ጩኸት የሰማችው ሌላዋ እናትም መጣች፡፡ የልጆቹ ጠብ ቀረና ድብድቡ_በሁለቱ እናቶች መካከል ሆነ። ሮቤል መገራም «እባካችሁ ይህ ጠብ ተዛምቶ ሁላችንንም ከማካተቱ በፊት ገላግለን እናስማማቸው» አሉ፡፡ ተመልካቾቹ ግን የሁለቱን ጠብ እንደ ነጻ ትግል እያዩ ይዝናኑ ነበር፡፡ አንዳንድ ሽማግሌዎችም «ሁለት ሴቶች ተጣልተው የት ይደርሳሉ» እያሉ ንቀው ተውት፡፡

በግርግሩ የከበቡትንሰዎች እየጣሰ አንድ ሰው ወደ መካከል ገባ፡፡ ያንደኛዋ ባል ነበር፡፡ እንዴት ሚስቴን ትመ ቻታለሽ ብሎ ያቺኛይቱን ሴት መደብደብ ያዘ፡፡ ይኼኔ ነገሩን የሰማው ሌላኛው ባልም ሲሮጥ መጥቶ ድብድቡን ተቀላቀለ፡፡ ሮቤል መገራ አሁንም «እባካችሁ ገላግሏቸው፤ይህ ጠብ ለሀገር ይተርፋል» ሲሉ ተናገሩ፡፡ ሰሚ ግን አላገኙም፡፡

ሁሉም የራሱን ልጅ፣ ሚስትና ቤት ብቻ ይጠበቅ ነበር፡፡ ወንዶቹም ልጆቻቸው እና ሚስቶቻቸው እንዳይገቡ ይቆጡ ነበር፡፡ የሁለቱ ባሎች ጠብ ተባባሰ፡፡ ሕዝቡም ከብቦ ያይ ጀመር፡፡ በዚህ መካከል የሰውዬው ወገኖች ነን ያሉ ያንደኛዋን ባል መደብደብ ያዙ፡፡ ተመልካች ሆነው ከቆሙት መካከል የዛኛው ወገን ነን የሚሉ ደግሞ ያኛውን ይዘው ይደበድቡ ጀመር፡፡ እንዳጋጣሚ የሁለቱ ሰዎች ጎሳዎች የተለያዩ ስለነበሩ ጠቡ ወደ ጎሳ አደገ፡፡

ዱላ እና እጅ ብቻም ሳይሆን የጦር መሣሪያም ተጨመረበት፡፡ ቤት ንብረት መዝረፍ፣ ማቃጠል እና መግደል እየተባባሰ መጣ፡፡ መንደሩም የጦርነት አውድማ ሆነ፡፡ከሁለቱም ወገን ሰዎች ሞቱ፡፡ ይኼኔ ሮቤል መገራተ ነሡ። «ቀድሞ እኔን ሰምታችሁኝ ቢሆን ኖሮ መልካም ነበር፡፡ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን እንጂ ስለ ሌሎ ችግድ ስለሌለን ዕዳው በመጨረሻ እኛው ላይ መጣ፡፡ ውሾቹን ተው ማለት አቅቶን እዚህ ደረጃ ደረስን፡፡ ምን ጊዜም ጦርነቶች የሚነሡት ውሾቹን ተው የሚል እየጠፋ ነው፡፡ ጎረቤት እና ጎረቤት፣ ጎሳ እና ጎሳ፣ ንጉሥ እና ንጉሥ፣ ሀገር እና ሀገር፣ እስላም እና ክርስቲያን፣ መንደር እና መንደር፣ የሚጣላው ውሾቹን ተው የሚል እየጠፋ ነው፡፡

የጦርነት መነሻ ውሾች ናቸው፡፡ ውሾቹ በአጥንት የጀመሩት ጠብ ሕይወት አስከፈለን። እነዚህ ውሾች እኮ ከአጥንት በላይ አርቀው ማሰብ የማይችሉ ውሾች ናቸው፡፡ ዓላማቸው አጥንት መጋጥ ብቻ ነው። አገር ቢጠፋ፣ ሕይወት ቢጠፋ፣ ንብረት ቢጠፋ እነርሱ ምን ጨነቃቸው፡፡ እንዴት ከአጥንት በላይ ማሰብ የማይችሉ ውሾች ይህንን ሁሉ ዋጋ ያስከፍሉናል? በማለት ጥበበኛው ሽማግሌ እርቅ አወረዱ ይባላል። (ከዳንኤል ክብረት የጡመራ ገጽ ላይ በጥቂቱ ማሻሻያ ተደርጎበት የተወሰደ)።

እኔ እንደ ተረቱ ጠቢቡ ሮቤል ነገሮችን አስቀድሞ የመመልከት ጥበብ በእጄ የለም። አሁን ያለንበት የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ከተረቱ ጋር ሲበዛ ተመሳስሎብኛል ለማለት ግን ጠቢብ መሆንን የግድ አይለኝም። ምክንያቱም ዛሬ ከውሻዎች የዘለለ ፀብ እየተመለከትን ነንና።

በሰዎች መካከል እየተፈጠረ ያለውን ጸብ ተመልክቶ ይሄ አገርና ህዝብ ወደዬት እያመራ እንደሆነ መናገርም የራስን ስም የማወቅ ያህል ቀላል ነው። እንደ ቀልድ የተጀመሩ የሚመስሉ ነገሮች ከመስመር እየወጡ እንደሆነ እየታዘብንም ነን። በግሌ ይህ አገር ወደማይወጣው ቀውስ ውስጥ ሊገባ እየተንደረደረ ያለም ይመስለኛል። አብዛኛዎቻችን ዳር ላይ ቆመን እኔን እስካልነካኝ ምን ቸገረኝ በሚል ዝምታን መርጠናል። አሊያም ዳር ላይ ቆመን እሳቱን እየሞቅን ነን።

ከአምና በፊት ባሉት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ግጭቶች ሲከሰቱ አይተን እንዳላየን አለፍነው አምናም በጎንደር በሚኖሩ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ላይ ችግር ሲፈጠር እጃችንን አጣጥፈን በመመልከታችን፤ ጉዳዩንም የሁለቱ ክልሎችና የሥርዓቱ ጥፋት አድርገን በመቁጠራችን ይሄውና ስር ሰድዶ ወደ ሌላ ክልል ሊሻገር ቻለ።

በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ ብዙዎች ህይወታቸውንና ንብረታቸውን አጥተዋል፤ ከኖሩበት ቀዬም ተፈናቅለዋል። በዚህ ወቅት አብዛኛዎቻችን አሁንም ካለፈው ጥፋት ባለመማራችን ጉዳዩን የመንግሥትና የሁለቱ ክልሎች ጣጣ አድርገን በመቁጠር እጃችንን አጣጥፈን ተመለከትን። ይህ ግን ስህተት መሆኑን ለመረዳት ወርም አልፈጀብን። ምክንያቱም ወዲያውኑ ነበርና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባሉ የአማራ ክልል ተወላጆች ላይ ተመሳሳይ ችግር የተፈጠረው።

አሁንም ይሄንን ችግር የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች እና የፌዴራሉ መንግሥት ችግር ብቻ አድርገን የምንመለከት ሰዎች ጥቂት አይደለንም። በተለይም ጉዳዩ የሚመለከተን አካላት ዝምታን በመምረጣችን ወይንም ማድረግ ያለብንን ማድረግ ባለብን ልክ ባለማድረጋችን ወደቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሊሻገር ችሏል። ደግነቱ ችግሩ ብዙም ሳይዛመት በአካባቢው ህዝብ አርቆ አሳቢነት ጸቡ በርዷል። ስለሆነም እላለሁ የጥበበኛውን ሮቤል አይነት ጥበብ ሁላችንም ሊኖረንና እንደ አገርን እየገጠመን ያለውን ችግር በጋራ ልንመለከትና ልንመክት ይገባናል።

ይህ ካልሆነ ችግሩ ቀስ እያለ የእያንዳንዳችንን በር ማንኳኳቱ የማይቀር ነው። ምክንያቱም እየተጣላን ያለነው በእኛ አጀንዳ አይደለም፤ ይልቁንም ከሚግጡት አጥንት በላይ ማሰብ በማይችሉ፣ የእዚህችን አገር እድገትና ልማት በማይሹ የውስጥና የውጭ ኃይሎች እንጂ።

እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብዬ የማምን ከሆነ በሰሜንም ይሁን በደቡብ አሊያም በምስራቅ እና በምዕራብ ያለው ወገኔ ጉዳይ ሁሉ ሊገደኝ ይገባል። እውነታውም ይሄ ነው። አሁን እያየን ያለነው ግን ከዚህ የተለየ ነው። በእንትን ክልል ውስጥ የሚኖር የእኔ ክልል ነዋሪ ጉዳት ደረሰበት በሚል ያዙኝ ልቀቁኝ እያልን ሰላማዊ ሰልፍ ሳይቀር የምንጠራ ከሆነ ኢትዮጵያ ዊነታችን ጥያቄ ውስጥ ይገባል።

በተቃራኒው ደግሞ በዚያ ክልል የእኔ ክልል ነዋሪ ምንም ስላልሆነ ጉዳዩ የእኔ አይደለም፤ ምን አገባኝ በሚል ዝምታ ውስጥ የገባንም ዝምታችንን ልንሰብር ይገባናል። በአጠቃላይ ግን እንደ አገር እየገባንበት ያለው «እኔ ብቻ» የሚል ስሜት ስህተት ነው ብዬ ብናገር ስህተት የሆንኩ አይመስለኝም።

ጠቢቡ ሮቤል የውሻዎችን ጠብ አይተው ተዉ ሲሉ ማስጠንቀቃቸው መጪው አደጋ ቢታያቸው ነው። ዛሬም መንግሥት በደህንነት መዋቅሩም ይሁን በሌላ መንገድ ባገኘው መረጃ እየተካሄደ ያለው አደጋ ቀላል እንዳልሆነ፤ ጉዳዩ አገርን ሊያጠፋ እንደሚችል ሲናገር ሰምተን እንዳልሰማን መሆናችን ወይንም ምን አገባኝ እኔን እስካልነካኝ በሚል በምን አገባኝ ስሜት መዋጣችን ስህተት ነው። በጣም በሚያሳዝን መልኩ ይህ ግጭት ምን ሊያመጣ እንደሚችል እያወቅን ወይንም ለማወቅ ባለመፈለግ ዝምታን መምረጣችን ደግሜ እናገራለሁ ስህተት ነው።

አንድ አንዴ ደግሞ ዝምታ ይሻላል የሚያስብል ተግባር በሚዲያዎችና በአመራሮች ሳይቀር ሲፈጸም እያየን ነን። ህዝብን በትክክለኛው አቅጣጫ ይመራሉ የሚባሉት አመራሮችም ሆኖ ሚዲያዎች የአንድን ክልል ነዋሪዎች ጉዳት መዝዞ በማውጣት አገር የፈረሰ ያህል ጉዳዩን ካለልኩ ማስተጋባት የለባቸውም። ችግሩ መነገር አለበት? አዎን አለበት።

ግን እንዴት የሚለውን መመዘን ተገቢ ይመስለኛል። አንድ አንዱ አዘጋገብና አወራር «ተነስ አንተም አጠገብህ ያለውን በለው» አይነት ይዘት ያለው በመሆኑም ጭምር ይመስለኛል ከፍተኛ የመንግሥት አካላት ሳይቀር የግል አስተያየት ነው የመንግሥት አቋም ነው ወደሚል የግል አስተያየት ውስጥ የገቡት። ከመነሻው ሁሉም በኃላፊነት ጉዳዩን ቢመለከተውና ቢያስተናግደው ኖሮ ይሄ ባልተከሰተ ነበር።

እውነት እናውራ ከተባለ ኢ ኤን ኤን ዘገባውን ያቀረበበት መንገድ በየትኛውም መስፈርት ትክክል ነው ሊባል አይችልም። አለመዘገቡ ይሻል ነበር የሚልም ካለ ትክክል ነው ሊባል አይችልም።

ምክንያቱም እንደ ሚዲያ ያንን መዘገቡ ትክክል ነው፤ ነገር ግን የዘገበበት መንገድ ያውም ለህዝብ ቅርብ የሆነን የእግር ኳስ ስርጭት አቋርጦ በሰበር ዜና መልክ ማቅረቡ በየትኛውም መለኪያ ትክክል ነው ሊባል አይችልም። ያንን ዘገባ በንጹህ አዕምሮ የማይመዝን ሰው ቢኖር ኖሮ በቀጥታ ወደ ሌላ ጥፋት ላለመግባቱ ምንም ዋስትና የለም ነበር። እንደመታደል ሆኖ ግን አገሪቷ ኢትዮጵያ፤ ህዝቡም ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ምንም ሳይፈጠር አለፈ።

ፈሪሀ ፈጣሪ የነገሰበት አገርና ህዝብ ስለሆነ ምንም ነገር ከማድረጉ በፊት ወደ ጎን ሳይሆን ወደላይ ቀና ብሎ ፈጣሪውን የሚያይ ጨዋ ህዝብ ስለሆነ ጉዳዩን አለፈው እንጂ የኢኤን ኤን ዘገባም ሆነ የአንዳ ንድ ክልል የመንግሥት ቃል አቀባዮች አዘጋገብ መውጫ ወደሌለው ማጥ ውስጥ ከትቶን ይሄኔ የምናወራው አሁን የምናወራውን ባልሆነ ነበር። ስለሆነም ሁሉም ወገን እንደ ጠቢቡ ሮቤል ነገሮችን አስቀድሞ መመልከት ባይችል እንኳን የውሻዎችን ጸብ አይቶ ዝም አይበል።

ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዳሉን ይሄ ሁሉ ሁከት እየተነሳ ያለው የኮንትሮባንድና የህገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር መፈናፈኛ ስላጣም ጭምር ነው። እነዚህ ከሚግጡት አጥንት በላይ ማሰብ የማይችሉ ሰዎች የጨለማ ሥራ እና ሴራ ፀሐይ መምታት ሲጀምርባቸውና ማንነታቸው ሲገላለጥባቸው አርፈው ይቀመጣሉ ማለት ዘበት ነው። ስለሆነም በአንድም በሌላም መልክ እዚህም እዚያም የሚያቀነባብሩትን ሴራ ልንረዳና ልጆቻችን፣ ወንድሞቻችንንና ጎረቤቶቻችንን አድቡ ልንል ይገባናል።

እኔን እስካልነካኝ በሚል ከገባንበት የዝምታ ባህር ልንወጣ፤ ዝምታው ይሻላል ከሚያስብል አፍራሽ አካሄድም ልንገታ ጊዜው አሁን ነው። ሰርቶ ለመኖርም ብቻ ሳይሆን ዘርፎ ለመኖርም አገር ሲኖር ነውና ቅድሚያው ለአገር ይሁን በሉ! ለባለሴረኛዎቹም እንደዚህ በሏቸው።
አርአያ ጌታቸው ((አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment