Saturday, October 21, 2017

በሃሰት የፌስ ቡክ የወሬ ግርግር እውነት እውነትነቱን አይለውጥም!

( ጥቅምት 10, (አዲስ ዘመን))--«እኔ ፌስ ቡክን የምጠቀመው ጀግንነትን ማሳያ ስለሆነ አይደለም፡፡ የምጠቀመው ሕዝብ ብዙ ሃሳብ አግኝቶ የተሻለውን እንዲመርጥ ለማድረግ ነው፡፡ ይህን ስል የልማት እቅድ አቅጄ ልማት ለማምጣት አይደለም፡፡ ልማት ለማምጣት የተግባር ሥራ ያስፈልጋል፡፡ በተግባር ለአገሬ የበኩሌን አደርጋለሁ፤እያደረኩም ነው፡፡ ፌስ ቡክ ላይ ግን አስተሳሰብን መገንባት ነው.........» የሚል ጽሑፍ አነበብኩ ይህ ጽሑፍ ከጅምሩ ጥሩ የመንደርደሪያ ሃሳብ ይዞ ተነስቶ የጀመረውን በጎ ሃሳብ ጥሎ የራሱን የፌስ ቡክ የጀግንነት ውሎ ሊያሳይ ሞከረ፡፡

የፌስ ቡክ ጀግኖች ቀድሞውንስ ሃሳብን አካፍሎ በምክንያት አሳምኖ መርታትን የጀግንነት መሠረት መች አደረጉት! የእነርሱ ጀግንነት ያለው ብሔርን ከብሔር፣ ሕዝብን ከሕዝብ፣ አገርን ከአገራት ጋር ማጋጨት፣ መንግሥትን ማብጠልጠል፣ ወደቀ ሲሉዋቸው ተሰበረ፤ ማለት እንጂ! መች ሀቅን ለመረጃ ፈላጊው ኅብረተሰብ ማድረስ ሆነ !

የአስተሳሰብ መገንቢያ የሆነውን ማህበራዊ ሚዲያ የሕዝብ ለሕዝብ ቂም መያያዣ፣ የአገር ክህደት መግለጫ፣ የጦርነት መቀስቀሻ፣ የበሬ ወለደ የሃሰት ወሬ ማራገቢያ መድረክ ማድረጋቸው የፌስ ቡክ ጀግኖችና አርበኞች የላቀ የሥራ ውጤት ነው፡፡

በማህበራዊ ሚዲያ የሚካሄድ የሃሳብ ፍጭት የጦርነት አውድማና የተደበቁ ዕኩይ ማንነቶች የሚገለፁባቸው ሳይሆኑ መንግሥትን በአግባቡ የሚተቹ፣ ግድፈቱን የሚያርሙና የማስተካከያ መንገድ የሚያመላክቱ፣ ያላስተዋለውን የሚጠቁሙ መሣሪያዎች ሊሆኑ ሲገባ ፤ እነርሱ የፈሩትን ተግባር ሌላው ምንም የማያውቀውና በስሜት የሚነዳው ሰው እንዲፈፅምላቸው ተንበርክከው የሚለምኑበት መድረክ አድርገውታል፡፡

ከሌሎች አገሮች ልምድ መረዳት የሚቻለው መንግሥታት ወይም ተቋማት በማኅበራዊ ሚዲያ ለሚደርስባቸው ወቀሳ የአፀፋ አስተያየቶችን የሚጽፉ ሠራተኞችን እንደሚቀጥሩና የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳዳቢዎች አደረጃጀት እንደሚፈጥሩ ሁሉ በእኛ አገርም የመንግሥትን ተግባር አወድሰው፣ ልማታዊ ሥራውን አጉልተው ሲገልፁ በተደራጁ የፌስ ቡክ ተሳዳቢ ሰዎች ተሸማቅቀው ዝም እንዲሉ የተጠናከረ የተሳዳቢዎች ኮሚቴ እንደተዋቀረ በጉልህ ይታያል፡፡

ለምሳሌ የቻይናው መሪ ሁጂንታኦ የቻይናን መልካም ገጽታ ለመገንባት ጥራት ያላቸው የድረ-ገፅ አስተያየት ሰጪ ጓዶች መኖር እንዳለባቸው በመግለፃቸው የቻይናው የባህል ሚኒስትር 300,000 የሚሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ አስተያየት ሰጪ “ኮሜንት” አድራጊዎችን በቋሚነት በማሰልጠንና በማሠማራት በቻይና የባህል ሚኒስትር_ ሥር እየሠሩ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ በቁጥር በእጅጉ የላቁት ግን “ባለጌ፣ ከሃዲ፣ አሽከር፣ ተላላኪ፣ ሰላይ” ወዘተ...የሚሉ የተለመዱና እጅግም የባሱ ጋጠወጥነት የሚንፀባረቅባቸውን ስድቦችን በመሳደብ ማኅበራዊ ሚዲያውን እያቆሸሹትና ለኅብረተሰብ በጎ ለውጥ የሚውለውን ታላቅ መሣሪያ አገር ለማፍረስ ተግባር እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

ዛሬ በኢትዮጵያ ብዙ ለውጥ አለ፤ ኅብረተሰቡ ማንኛውንም ክንውን የሚያውቀው ፌስ ቡክ ላይ በሚለጠፍለት የሃሰትና የተጋነነ አሉባልታ ሳይሆን እራሱ በዓይኑ ከሚያየውና ከሚረዳው ገሀድ እውነታ ነው፡፡ በርግጥ አንዳንዶች የአገር ፍቅር ያላቸው፣ የመንግሥትን ጥረት የሚገነዘቡ፣ ካሳለፉት መራራ ታሪክ ዛሬ ያገኙት ሰላምና እድገት ቀጣይነቱ የሚረጋገጠው በሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆኑን የሚረዱ፣ የሚፅፉትና የሚያስተላልፉት መረጃ የማይናቅና ገንቢ መሆኑ እሙን ነው፡፡

ይህንን በጎ ግንዛቤ እየፈጠረ ያለውን ሥራቸውንም ወደፊት በእውነት ላይ በተመሰረተ መረጃ ማድረሳቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ሰሞኑን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየተናፈሱና እየተሰራጩ ያሉ የሃሰት ወሬዎችም የእነዚሁ የፌስ ቡክ አሉባልተኞች ተግባር ናቸው፡፡ ግንባታ ቆመ፣ ሠራተኞች ተባረሩ፣ የሥራ መሣሪያዎች ወደ መሀል አገር እየተጫኑ ነው ወዘተ... ተራ ወሬዎች አሰራጮቹን ከግምት ላይ የሚጥልና ወራዳነት የተላበሰ ተግባር ነው፡፡

የዛሬ ስድስት ዓመት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለትና ሥራውን ለፍጻሜ ለማብቃት በሦስት ፈረቃ ለ24 ሰዓት ርብርብ ላይ የሚገኘው ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የመላ አገሪቱ ሕዝቦች ተስፋ፣ የዜግነት አሻራቸው ያረፈበት፣ የአገሪቱን የወደፊት እድገት የሚያረጋገጥ፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ መስክ የፈጠረ፣ መላው ኅብረተሰብ በተስፋ የሚጠብቀው ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ዕድገት እንደ ውስጥ እግር እሳት የሚያንገበግባቸው ጠላቶቿ እና የራሷ ባንዳና ከሃዲ ልጆቿ በግድቡ ላይ በተለያዩ መንገዶች ሲያሟርቱበት እነሆ ሥራው በስኬት እየተገባደደ እነርሱም የመጨረሻ መፍጨርጨራቸውን ቀጥለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የቱንም ያህል የአሉባልታና የሃሰት ወሬዎች ቢናፈሱ መላ የአገሪቱ ሕዝቦችን ያስተሳሰረ፣ ለአንድ ዓላማ ያሰለፈና አገራዊ መግባባትን በተግባር ያሳየ ታላቅ ግድብ ሥራ ለአፍታ እንኳ እንደማይቆም ማንም ልብ ሊል የሚገባው ነው፡፡ በሃሰት የፌስ ቡክ የወሬ ግርግር እውነት እውነትነቱን አይለውጥም!
ርዕሰ አንቀፅ (አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment