Saturday, December 12, 2015

በታላቁ አንዋር መስጊድ በደረሰ ፍንዳታ በሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ ደረሰ

(ታህሳስ 2/2008  (አዲስ አበባ))--በታላቁ አንዋር መስጊድ በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ በስግደት ላይ በነበሩ የተወሰኑ ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱን የመንግስት ኮሚንኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ከዓርብ የፀሎት ሥነ-ሥርዓት በኋላ በተከሰተው ፍንዳታ በሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል። ጉዳቱ የደረሰባቸው ዜጎችም ሆስፒታል ገብተው ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛሉ።

ፖሊስ በአካባቢው ጥብቅ ክትትል በማድረግ መረጃዎችን በማሰባሰብ የፍንዳታውን መንስኤ ለማጣራት እየሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የፌደራል የፀረ  ሽብር ግብረ ኃይልም  ትናንት በታለቁ  አንዋር  መስጊድ ህዘበ  ሙስሊሙ  የጁሙዓ  ሶላት ሰግደው  ሲወጡ ለጊዜው ማንነቱ  ባልታወቀ  ግለሰብ  የተወረወረ  ቦንብ በአምስት ሰዎች ላይ ከባድ  ጉዳት ያደረሰ  ሲሆን ፣19  ሰዎች የመቁሰል አደጋ  የደረሰባቸው መሆኑን ገልጿል።

ይሁንና እጅግ ኃላፊነት የጎደውና ዘግናኝ ተግባር በመፈፀም ተዋናይ የነበሩትን አሸባሪዎች ለመያዝ በሚደረገው ጥረት ሕብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠትም ሆነ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የፀረ ሽብር ግበረ ኃይል አሳስቧል፡፡

እንዲሁም በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች በተለያዩ አጀንዳዎች በመሸፈን የሽብርና የአመፅ እንቅስቃሴ ለማካሄድ የሚሞክሩ ኃይሎች እንዳሉም ተደርሶበታል፡፡ በመሆኑም ይህን እኩይ ተግባር ለማክሸፍና ዋና ዋና ተዋናዮችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረገው ጥረት ሕብረተሰቡ ጥቆማ የመስጠቱን ሂደት አጠናክሮ እንዲቀጥል ግብረኃይሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ሰሞኑን አሸባሪው የግንቦት ሰባት አርበኞች ግንባር የዘወትር የሽብር ተግባሩን ለመፈፀም በትግራይና በአማራ ክልሎች የጋራ ድንበር አካባቢ ከአሥር የማያንሱ ኃይሎችን ለማስገባት ጥረት ቢያደርግም፣ የሁለቱ ክልል የፀጥታ ኃይሎችና ሕብረተሰቡ በጋራ በመሆን በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማድረጉንም የፌዴራል ፀረ ሽብር ግብረኃይል መግለጫ አመልክቷል፡፡
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፡፡

No comments:

Post a Comment