Saturday, July 25, 2015

አገሬ ሆይ !«የዓለም መሪዎች ሁሉ ገና ፊታቸውን ወዳንቺ ያዞራሉ»

(25,  Jul 2015, ((አዲስ አበባ))--ባለፉት ሳምንታት ሲነገሩ ከነበሩ ትኩስ መረጃዎች መካከል አንደኛው ጆሮን የሚስብና አጃኢብ የሚያሰኝ ነበር፤ «የልዕለ ኃያሏ አገር ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው» የሚለው መረጃ። ከዚያማ ከግራና ከቀኝ እየተሰጡ ስለነበሩት አስተያየቶች ትችቶችና ሙገሳዎች ማድመጥ የዕለት ተዕለት ሥራ ሆነ። የኋይት ሐውስ የፕሬስ ጉዳዮች ኃላፊ ጆሽ ኧርነስት የኦባማን ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ባበሰሩባት ምሽት «የኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት አሜሪካ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከርና በአፍሪካ ኢንቨስት የማድረግ ቁርጠኝነት ያላት መሆኑን ለማሳየት ያለመ ነው» ሲሉ ተደመጡ።

የፕሬዚዳንት ኦባማ ጉብኝት ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮችና ዜጎች ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲያመጡ፣ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲገነቡና የደኅንነት ይዞታቸውን እንዲያጠናክሩ አሜሪካ የምታደርገው ጥረት አካል እንደሚሆንም ኃላፊው አብረው አክለውበት እንደነበርም ልብ ይሏል። ግን ፕሬዚዳንት ኦባማ አገሬ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ለምን ፈለጉ? የሚለው ጥያቄ የእኔም ነበርና እንደደስታም፣ ያየሁትን መረጃም እንደ አለማመን፤ ሌላም አይነት አዲስ ባህሪ ይንጸባረቅብኝ ነበር። ያም ሆነ ይህ የሰማሁትን መልካም ብስራት እያጣጣምኩና እራሴን ደግሜ ደጋግሜ እየጠየኩ ወደ መኝታዬ አመራሁ።

በእርግጥም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ማሰባቸው ሀገራዊውን ስኬት እና ዓለም አቀፋዊውን ተቀባይነት መጨመር የሚያሳይ እንደሆነ ደረትን ነፋ አድርጎ መናገር ይቻላል። አብዛኞች በሁለቱ ሀገራት የረጅም ጊዜ ግንኙነት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሥልጣን ዘመኑ ሳይጠናቀቅ ኢትዮጵያን የጎበኘ አንድም ፕሬዚዳንት አለመኖሩን በማጣቀስ ይህ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን አጽንኦት እየሰጡ ሲያስረዱም ሰምቻለሁ።

እዚህ ላይ በእነዚህ ረጅም ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን በአንድም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እንዳትጎበኝ ያደረጋት ምን እንደሆነ ማንሳቱ ተገቢ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው ሁሉ አገሪቱ ትታወቅ የነበረው በረሀብና በእርስ በእርስ ጦርነት ብቻ እንደነበር ዓለም የሚያውቀው ታሪካችን ነው። በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ለዓለም ብዙም የማትጠቅም አገር ተደርጋ ትታይ ስለነበር እንኳን የታላቋ አገር ፕሬዚዳንት ይቅርና መለስ ያለ አገር መሪ እንኳን አገራችንን ለመጎብኘት ፍላጎቱ አልነበራቸውም ማለት ይቻላል። አሁን ግን ታሪክ ተቀይሯል። በረሃብና በጦርነት የጠለሸው ስማችንና ገጽታችን ቀስ በቀስ እየተገፈፈ መጥቶ እነሆ ኦባማንም ጎትቶ የማምጣት ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

የፕሬዚዳንቱ የጉብኝት ዜና በተሰማበት ወቅት «የባራክ ኦባማ ጉብኝት በዓለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያስመዘግቡ አምስት ሀገራት አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ማድረጋቸው የሀገሪቱን ስኬት ያመለክታል» ሲሉ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን በጠባቧ ቴሌቪዥን መስኮት ፊት ለፊት ቀርበው ሲናገሩ አድምጫለሁ። ዋነኛውና አስኳላው ርዕሰ ጉዳይ የሚጀምረውም እዚህ ጋር ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን ማንም ይጎበኘናል ብለን ሳይሆን ቀደም ሲል ወደነበርንበት የዕድገት ማማ ዳግም ለመመለስ ባደረብን ጽኑ ፍላጎት ሳቢያ ባለፉት ሃያ አራት ዓመታት በእጅጉ ደክመናል። ትግላችን አንገታችንን ካስደፋው ድህነት ጋር ብቻ አልነበረም። ይልቁንም የምዕራባውያኑን ትንኮሳም በሉት ነቀፌታ እንዲሁም ከርዕዮተ ዓለማቸው ጋር የነበረው ፍትጊያ ቀላል አይደለም።

እኛን የሚያድነንና ወደ ነበርንበት የሥልጣኔ ማማ የሚመልሰን የእናንተው የኒዮ ሊብራሊዝም አስተሳሰብ ሳይሆን የራሳችን የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንገዳችን ነው በሚል በደፋር የኢትዮጵያዊነት ወኔና ጀግንነት ዛሬ ላይ ደርሰናል። ባገኘናቸው መድረኮች ላይ ሁሉ ስለ ትክከለኛነታችን ዘምረናል። ምስጋና ለበሳል የአገራችን መሪዎች ይሁንና «ድህነታችንን አሽቀንጥረን እንጥል ዘንድ ያሉንን አማራጮች በሙሉ አሟጠን እንጠቀማለን፤ ከረዱን እንረዳለን በሰበብ አስባቡ ቀይ መስመራችንን ለማለፍ ከሞከሩ ግን ያመናል» ብለው ባቆዩልን ጎዳና ስንፈስ ይኽው እዚህ ደርሰናል።

ይህ ቆራጥነታችን ታዲያ ምንም እንኳን ዋጋ ቢያስከፍለንም በዓለም ያለንን ተቀባይነት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እንዲል በማድረጉ ረገድ የነበረው አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም። ስለሆነም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ደግመንና ደጋግመን እንድንነሳም በር የከፈተልን ሆኗል። ለአብነት እንኳን ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደው ሦስተኛው ፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ላይ አገራችን በተለያዩ መስኮች ያስመዘገበችውን ድል ለሌሎች አገራት በተሞክሮነት እንድታጋራ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን ሳይቀር ተጠይቃለች። እነዚህ የድል በሮች ከምን የመነጩ እንደሆኑ በተወሰነ መልኩ ማየቱ ለጽሑፉ በጭብጥ መዳበር ወሳኝነት አለውና እንዲህ እናትታለን።

በሰላም ማስከበር ተልዕኮ
ከምንም በላይ የሰላም ጉዳይ ይቀድማልና በሰላም ማስከበር ተልዕኳችን ከአፍሪካ አንጻር ስንመዘን ያለንበት ደረጃ ቀዳሚነትን የሚያሳይ ነው፤ ከዓለም ደግሞ የአራተኝነት ደረጃ። በተለይ ግን ከምንም በላይ በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ውስጥ የነበረን የሰላም ማስከበር ሚና ተወዳዳሪ የማይገኝለት መሆኑን እንኳን ጎረቤቶቻችን መላው የዓለም አገራት ጭምር ጠንቅቀው የሚያውቁት ጉዳይ ነው። ስለሆነም አገሪቱ በተደጋጋሚ ጊዜ ከመወደስም አልፋ በበርካታ የዓለም ሀገራት መሪዎች የመጎብኘት ዕድል አግኝታለች። ልብ ይበሉ ይህን መረጃ ደግሞ አሜሪካንም ጠንቅቃ ታውቀዋለች ማለት ነው።

በተሰማራንባቸው የተለያዩ የሰላም ማስከበር ተልእኮዎች ህይወታቸውን መስዋዕት ላደረጉ ኢትዮጵያውያንም የመንግሥታቱ ድርጅት የተመድ ሰላም አስከባሪዎች ዓለም አቀፍ ቀንን በዘከረበት ወቅት ክብር ሰጥቷል፤ ለሀገራችንም የሜዳሊያ ሽልማት አበርክቷል። ይህም የመንግሥታቱ ድርጅት ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በጋራ ፀጥታ ላይ ባላት ጽኑ እምነት ተመድ በሚመራው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ በንቃት ስትሳተፍ መቆየቷን የሚያሳይ እንደሆነ ምንም አያ ጠራጥርም።

በዓለም አቀፍ ደረጃም ሀገሪቱ ስምንት ሺህ አካባቢ የሚጠጋ የሰላም አስከባሪ ኃይል በማሰማራት በአፍሪካ ቀዳሚ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ትገኛለች። እነዚህ የሰላም አስከባሪ ኃይሎቻችንም በአቢዬ፣ ዳርፉር እና በደቡብ ሱዳን ተሰማርተው ይገኛሉ። በላይቤሪያና ኮትዲቯር ደግሞ በስታፍና በወታደራዊ ታዛቢነት፤ በሶማሊያ በአፍሪካ ህብረት ስር ከሌሎች መሰል አገራት ጋር ሰላም የማስከበር ሥራውን እያከናወነ ይገኛል። ለእዚህም ከአራት ሺህ የሚበልጡ የሀገራችን ሰላም አስከባሪ ኃይሎች በግዳጅ ላይ ናቸው።

የኦባማ ጉብኝትም ለእዚህ ዓለም አቀፋዊ አስተዋፅኦ እውቅና የሚሰጥ ነው። ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿን ብሎም የአህጉሪቷን ሰላም በማስከበርና ሽብርተኝነት በመከላከል ላስመዘገበቻቸው ውጤትና ድል እዚህ ድረስ መጥቶ እውቅና መስጠት ብሎም ማመስገን ከአንድ የሠለጠነ አገር መሪ የሚጠበቅ ተግባር ነውና ኦባማ መምጣታቸው በዚህ አቅጣጫም ተገቢና የሚገባን ክብር ነው።

በአመርቂ የኢኮኖሚ ዕድገት
በእዚህ ወር ይፋ የሆነው የዓለም ባንክ ሪፖርት እንዳመለከተው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት አሥር ዓመታት የ10 ነጥብ 9 በመቶ አማካይ ዕድገት አስመዝግቧል። ይህም ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት አማካይ ዕድገት ጋር ሲነፃጸር ከእጥፍ በላይ ነው። እያደገ የመጣውን የአገሪቱ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያጋጥሙትን እንቅፋቶች መፍታት ከተቻለ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ ያደርጋል ሲልም ዘገባው ሙገሳውን አክሏል። ከዚህ ባሻገርም መንግሥት የአገሪቱን የማምረቻ ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የነደፈውን ዕቅድ የሚደግፍ እንደሆነ ነው የዓለም ባንክ ዘገባ ያሰፈረው። ባንኩ በዘገባው የአገሪቱን የአጭርና የረጅም ጊዜ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም በጥልቀት ዳስሷል።

በተጨማሪም በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የተሳለጠ መዋቅራዊ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ለመገንባት የሚያስችለውን ጠንካራና ብዝሃነት ያለው የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፉን ባንኩ በጥልቀት ተመልክቷል። «ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2025 የኢኮኖሚ መሰረቷን ወደ ኢንዱስትሪ የማሸጋገርና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የመሰለፍ ራዕይ አላት» ያሉት የባንኩ ዋና ኢኮኖሚስትና የፕሮግራም መሪ ክርስቲያን ሞለር ናቸው። «አገሪቷ ትልቅ ስኬት ያስመዘገበች ቢሆንም በታክስ፣ ንግድና በፋይናንስ ህግ እንዲሁም እንደ የኤሌክትሪክ ኃይል ባሉ መሰረታዊ አቅርቦቶች ላይ የሚስተዋሉትን ውስንነቶች በማስተካከል የአገር ውስጥ ገቢን መደገፍና የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ ይገባታል» ነበር ያሉት።

የባንኩ ሪፖርት እውን አንዳንዶች እንደሚሉት ሳንሠራ የተሰጠን ሽልማት ነው? ኢትዮጵያ የዕድገቷን ቀጣይነት ለማረጋገጥና ድህነትን ለማስወገድ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ማስፋፋት ላይ ትኩረት ሰጥታ ስትሠራ እንደቆየች የሚካድ ሀቅ ነው?

ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያማከለ ትምህርትና ሥልጠናን በማሻሻልና የሥራ ፈጠራ ክህሎትን በማሳደግ እንዲሁም ቀላል ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች መሠራታቸውንም የተገነዘበ እንደነበር ለመግለጽ ይቻላል። ይህ የማያቋርጥ ፈጣን የኢኮኖሚ ግስጋሴ ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን ሁሉም የአገሪቱ ዜጋ ባደረገው እልህ አስጨራሽ ርብርብ እንደሆነ ማውሳት ተገቢ ነው። በመሆኑም እነዚህንና መሰል ጥንካሬያችንን ከቤተ መንግሥታቸው ሆነው ሲከታተሉ የነበሩት ኦባማ በፍቅራችን ተነድፈው ቤት ለእንቦሳ ሊሉን ፈቀዱ። እኛም የሥራችን ውጤት ነውና እንቦሳ እሠሩ ልንላቸው የቀሩን ጥቂት ቀናት ናቸው። ደግሞስ እንግዳ ለመቀበሉ ማን ብሎን!

ምናልባት እነዚህን ሁለት ዓበይት ጉዳዮች ያነሳሁት ለሌሎቹም ጥንካሬዎቻችን መሰረት በመሆናቸው እንጂ በትምህርት፣ ጤና፣ በግብርና ወዘተ ያስመዘገብናቸው ማራኪና አማላይ ስኬቶች መኖራቸውንም ልብ ሊሉ ይገባል። የኦባማም ኢትዮጵያን እጎበኛለሁ ውሳኔም የእነዚህ ሁሉ ሥራዎቻችን ድምር ውጤት ነው።

የዛሬውን ጽሑፌን የመንግሥት ኮሚ ዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን ባነሱት አስደናቂ ሃሳብ ልቋጭ፤
«የኦባማ ወደ ኢትዮጵያ አለመምጣት የሀገሪቱን ውድቀት ያሳያል ሲሉ የነበሩ ወገኖች አሁን ደግሞ ሊመጡ ነው ሲባል ለይስሙላ ካልሆነ ምን ይሠራል ሲሉ ይደመጣሉ። የሆነው ሆኖ ግን የባራክ ኦባማም ሆነ ሌሎች መሪዎች ወደ ሀገራችን መምጣት የውስጣችን መሞቅ፤ የሰላማችን መጠበቅ እና የሁለንተናዊ ዕድገታችን ማበብን መሰረት ያደረገ ነው። ሀገራችንን በልኩና በወጉ መያዝ ስንጀምር የስኬቶቻችን አጋሮች እንደሚበረክቱ ቀድሞም ቢሆን ስንናገር ነበር። የኦባማ ጉብኝትም የስኬታችን አጋር መበራከቱን ያሳያል።»

እኛ በርትተን ከሠራንና ለአንድነታችን ዘብ ከቆምን ሌሎች የዓለም መሪዎችም ገና ወደ አገራችን እንደሚመጡ ምንም ጥርጥር የለውም። ለእዚህም ነው አገሬን «የዓለም መሪዎች ሁሉ ገና ፊታቸውን ወዳንቺ ያዞራሉ» ማለቴ።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ  
ጸሐፊ ዮሐንስ ለገሠ

1 comment:

ባለ ቅኔ said...

New job creation is very critical for solving various issues of people in Ethiopia. The number one problem of an increasing of unemployment rate shall be reduced dramatically. However, good governance is so essential in order to attract and persuade both foreign and local investors so as they will be able to open new businesses that can hire millions of Ethiopians in the Nation. Do you know that the policies, directives, rules and procedures of Ministry of trade is discouraging? It is very important to have positive attitudes for changing bad situations to good and record success .

Post a Comment