Tuesday, July 14, 2015

የኤርትራ ጉዳይ «ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል» እንዳይሆንብን

(14 Jul 2015, ((አዲስ አበባ))-ኢትዮጵያ የራሷን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ አልፋ ለጎረቤት አገሮች አለኝታ መሆን ከጀመረች ዋል አደር ብላለች። ይህ ለሩቁም ሆነ ለቅርቡ ትልቅ ግርምትን የፈጠረ፤ ወዳጆችን ሲያስደስት ጠላቶችን ያስከፋና ያስደነገጠ ውጤት ሆኗል። ይህ ከራስ አልፎ ለሌላ እስከመብቃት ያደረሰ ተግባርም የአገሪቱ የውጭ ጉዳይና ደህንነት ፖሊሲ ውጤት ነው።

ከዚህ ጎን ለጎን በውስጥ ተቋማት የአሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነት እየተላበሰ መምጣቱም እንዲሁ። የአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እየጎለበተና የህዝቦች ተሳትፎ እያደገ፣ ወሳኝ አካልነቱ እየተረጋገጠ መምጣቱም በሰፊው ይዘገባል። እነዚህን መሰል አገራዊ ስኬቶች እንዴት ተገኙ? በቀጣይስ በምን መልኩ ይቀጥላሉ በሚለው ዙሪያ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተናገሩትን በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል።

•የውጭ ዲፕሎማሲው

ኢትዮጵያ በጎረቤቶቿ ላላት ተቀባይነት ዋናው ምንጩ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዋ ነው። በመሆኑም በአካባቢው ሰላም እንዲረጋገጥ፣ የጋራ ጉርብትና እንዲጠናከር፣ ልማት እንዲከናወን፣ ትስስሩም እየጎለበተ ሄዶ ወደከፍተኛው ደረጃ የጋራ ኢኮኖሚ ትብብርና ቅንጅት የማሸጋገር እንዲሁም በሂደት ውህደትን የመፍጠር ስትራቴጂ ተይዞ ሲሠራ ቆይቷል። ከሻዕቢያ መንግሥት ውጪ ካሉት ጎረቤት አገሮች ጋር የሚደረገው የትብብር እንቅስቃሴም እጅግ ውጤታማ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ከዚህ አኳያ ከኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን ጋር የተፈረሙና በተግባር እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ትብብሩ በኢጋድ ማዕቀፍም ሆነ በሁለትዮሽ የሚደረጉ ስምምነቶች እጅግ አመርቂ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በመሆኑም ይህ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

•የኤርትራ ጉዳይ

የሻዕቢያ መንግሥት አካባቢውን የማተራመስ አባዜውንና ፖሊሲውን እስካሁን አልቀየረም። ይህንን ፖሊሲ የማይቀይርበት መሰረታዊ ምክንያቱም በአገር ውስጥ የተከሰቱ ችግሮችን ውጫዊ አድርጎ ለህዝቡ ለማሳየት ብቸኛው መንገድና አማራጭ የመኖሪያው አጀንዳ በመሆኑ ነው።ይህን አማራጭ አድርጎ የወሰደውን ፖሊሲ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያቆማል ተብሎ አይገመትም። ይህን ፖሊሲውን መቀየር ካለበት መጀመሪያ በውስጥ ጉዳዩ በማተኮር መሥራት ይገባዋል። ካልሆነ ግን በተለይ ኢትዮጵያና ጅቡቲን በማተራመስ አጀንዳውን ውጫዊ ለማድረግ መሥራቱን ሊቀጥል ይችላል።

ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ በፊት የያዛቸውን ፖሊሲዎች አሁንም አጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ዋናው ጉዳይ የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ ህዝቦች የሚጠቀሙት ከሰላም በመሆኑ ሰላም ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ምርጫ ይሆናል። ነገር ግን የኤርትራ መንግሥት አሁን በያዘው ፖሊሲ ቀጥሎ ኢትዮጵያንና ሌሎች አጎራባች አገሮችን ለማተራመስ የያዘውን ስትራቴጂ የማይቀይር ከሆነ ተገደን እርምጃ የምንወስድበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ምክንያቱም፣ ሁልጊዜ ሰላምን የሚያውክ ጎረቤት ባለበት ሁኔታ «ከአጋም የተጠጋች ቁልቋል» እንዳይሆን ሁልጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ ስለሚገባ፤ ጊዜው ሲደርስ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማሳወቅ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ የምንገደድበት ሁኔታ ይኖራል።

የኤርትራን መንግሥት ተግባር ለዓለም ህብረተሰብ በማሳወቅ ማዕቀብ እንዲጣልበት ተደርጓል። ማዕቀቡም ወደተግባር እንዲሸጋገር ኢትዮጵያ በየጊዜው እየጠየቀች ትገኛለች። በዚህም ገሚሱ ወደ ተግባር ሲሸጋገር ገሚሱ ያልተሸጋገረ በመሆኑ ይሄ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ምክንያቱም፣ የኤርትራ መንግሥት ፖሊሲውን በመቀየር ወደ ሰላማዊ በመንገድ እንዲመለስ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመደራደር ዝግጁ እንዲሆን የሚያደርጉ እርምጃዎችን የዓለም ህብረተሰብ ሊወስድ ይገባዋል።

•ስደተኛን ተቀብሎ ከማስተናገድ አኳያ

ከኤርትራ ህዝብ ጋር ችግር የለንም። ወንድምና እህት የሆነው ይሄ ህዝብ ሲሰቃይ ዝም ብሎ ማየት ስለማይቻል፤ ስደተኞችን ከመቀበል አኳያ የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰዳቸውን ኃላፊነቶች ልንቀበለው የሚገባ ኃላፊነት አድርጎ ማየት ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ህዝብም ይሄንን በሚገባ የሚያውቀው ነው። ይህ ለኤርትራውያን ብቻ ሳይሆን ከደቡብ ሱዳንና ከሶማሊያ የሚመጡትን ወንድሞችና እህቶች ማስተናገድ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊና ሞራላዊ ኃላፊነትን መወጣት እንደመሆኑ ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

• የ2006 የኦዲት ግኝትና አንድምታው

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለተከበረው ምክር ቤት ያቀረበው የ2006 የኦዲት ግኝት መንግሥት የፈጠረው አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓት ተግባራዊ የመሆኑ ውጤት ነው። ይህም ከዚህ በፊት ተሸፋፍነው የቆዩ ነገሮች መገለጥ መጀመራቸው፤ በሌላም በኩል የኦዲት መሥሪያ ቤቱን አቅም በመጎልበቱ ከዚህ በፊት ይደረግ ከነበረው የፋይናንስ ኦዲት በተጨማሪ አሁን የክዋኔ ኦዲት የሚደረግ የመሆኑ ውጤት ተደርጎ ነው መወሰድ ያለበት። ስለዚህ መንግሥት ለህዝብ የሚሠራቸውን ሥራዎች ግልጽ ማድረግ አለበት የሚለውን ህገ መንግሥታዊ መርሆና እንዲሁም የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህ ተግባራዊ በማድረግ የመጣ ውጤት ነው። መንግሥትም የዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት ውጤት መሆን የሚገባውና መሆን ያለበት የሥራ ውጤት እንደሆነ ያምናል።

በቀጣይም የዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ የተረጋጋ ተቋም እንዲሆን መንግሥት ይሠራል። ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱም ጉድለቶቹን ለይቶ የበለጠ እየተጠናከረ ከሄደ የመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓቱ የበለጠ ግልፅነትን የተላበሰና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን መሥራት ይጠበቅበታል። ከዚህ አኳያ መንግሥት ይሄ ሥርዓት ጎልብቶና ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት ይሠራል። ህዝቡ የሚጠቀመው መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ልማት የተቀላጠፈባት አገር ውስጥ ሲኖርና መንግሥትም ይሄን ሲተገብር ነው። ስለዚህ እስካሁን ያመጣናቸው ለውጦች ቀጣይና ፍትሐዊ እንዲሆኑ ለማድረግ የጀመርነው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ከዚህ አኳያ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በሥራው ሊመሰገን የሚገባው ነው።

•ምርጫ 2007ና ጉርምርምታው

የ2007 ጠቅላላ ምርጫ ዋነኛ ባለቤት ህዝቡ ነው። የውጤቱም ዋነኛው ባለቤት እራሱ ህዝቡ ነው። በምርጫው ወቅት በነበሩ ሂደቶች ውስጥ ህዝቡ በነቂስ ተሳትፏል። በምርጫው ዕለትም በዓለም ደረጃ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ 96በመቶ የሚሆነው መራጭ ድምጹን ሰጥቷል። በዚህም ህዝቡ ውሳኔውን አስተላልፏል። በመሆኑም ውጤቱን አስመልክቶ ሌሎች ምን አሉ? የሚለው የሚያሳስብ አይሆንም። ሌሎች ምንም ሊሉ ይችላሉ። ምክንያቱም እነርሱ ዓላማቸው የተለያየ ስለሆነ። ዋናው ጉዳይ ህዝቡ ምን አለ? የሚለው ነው። ህዝቡም የሚለውን በውሳኔው አሳይቷል። በዚህም ህዝቡ ካለፉት ምርጫዎች ልምድ መውሰዱንና መማሩን፣ ከምንም በላይ ሰላምን የሚፈልግ መሆኑን እንዲሁም ጥላቻን፣ ቂም በቀልን፣ የተዛቡ አስተሳሰቦችን፣ ዘለፋንና ሥነምግባር የጎደላቸውን ተግባሮች የማይፈልግ እንደሆነ ያሳየበት ነው። ባለቤትነቱንም በሚገባ አረጋግጦ፤ ለኢህአዴግም ሆነ ለተቃዋሚዎች የቤት ሥራ ሰጥቷል።

•ህገወጥ የሰዎች ዝውውር

ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት በሚከናወነው ተግባር ቀዳሚው ህዝቡ ባለቤት ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ የተጀመረውን ሥራ የማስቀጠል ነው። ከዚህ አኳያ ከገጠር ቀበሌ አንስቶ እስከ ፌዴራል ተቋማት ድረስ ወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ መምህራንና ሌሎች ከወጣቶች ጋር ግንኙነት ያላቸው አደረጃጀቶች ጋር በመቀናጀት እየተሠራ ይገኛል። ህገወጥ ደላሎችን ከመከላከል አኳያም መንግሥት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ከደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል ጀምሮ እስከ ደቡብ አፍሪካ የተዘረጋውን የደላሎች መረብ ለመበጣጠስ ችሏል። ይህንን አጠናክሮ ይቀጥላል።

በቀጣይም ከሰሜኑና ምዕራቡ የአገሪቱ ክፍል በመነሳት እስከ ሊቢያ፣ ጣሊያንና በዚያ አካባቢ ያሉ ደላሎችን መረብ የመበጣጠስ ተግባር ይከናወናል። በዚህ ዙሪያ ከኢንተርፖል ጋርም ውይይት ተደርጓል።

በመሆኑም ይህንን መረብ በጋራ ለመበጣጠስ ዓለም አቀፍ ትብብር ተፈጥሯል፣ ስራውም ተጀምሯል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በህጋዊ መንገድ የተሻለ ገቢ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያንን ማበረታታት ይገባል። ከዚህ ጎን ለጎን ለምክር ቤት የቀረበው አዋጅ ሲፀድቅ ህጋዊ ዝውውሩን የማበረታታት ሥራ የሚካሄድ ይሆናል። በአጠቃላይ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል ላይ የሚሠራው ሥራ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment