Saturday, July 11, 2015

ኢትዮጵያ የዓመቱ ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ ተብላ የተመረጠችው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ባበረከተችው ድንቅ ስጦታ ነው

(ሐምሌ3/2007, (አዲስአበባ ))--''ኢትዮጵያን የዓመቱ ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ ብለን የመረጥናት አገሪቱ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ባበረከተችው ድንቅ ስጦታ ምክንያት ነው''ሲሉ የአውሮፓ የቱሪዝምና የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አስታወቁ።ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ  በያዝነው የአውሮፓውያን 2015 ዓመት ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ አገር ተብላ መመረጧን ተከትሎ የሽልማት ሥነ  ሥርዓት በብሄራዊ ቤተ መንግሥት ተካሂዷል። የምክር ቤቱ ፕሬዘዳንት ዶክተር አንቶን ካራጊ በዚህ ጊዜ "ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰው ልጅን ስልጣኔ፤ባህልና ታሪክን የተመለከቱ ረጅም እድሜ ያስቆጠሩ ቅርሶችን ያበረከተች አገር ናት'' ብለዋል።

ኢትዮጵያ ምርምሮች የሚካሄድባቸው የሰው ልጀን ስልጣኔና ባህል በሚያሳዩ ቅርሶች የተሞላች አገር መሆኗን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ የቅርሶቹን አስተማሪነትና አዝናኝነት በቱሪስቶች የተመሰከረላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

"የፋሲል ግቢ፣የአክሱም ሃውልት፣የላሊበላ ዐብያተ ክርስቲያን፣የሼክ ሁሴን መስጊድና መሰል ቅርሶች ኢትዮጵያን የዓመቱ ምርጥ የዓለም የቱሪዝም መዳረሻ አገር ሽልማትን ከ30 አገሮች ጋር ተወዳድራ ተሸላሚ አገር ሆናለች። የአዋሽ ስምጥ ሸለቆ፣የባሌ ተራሮች፣የሶፍ ዑመር ዋሻ፣የአገሪቱ የሽምግልና ሥርዓትና የቡና ጠጡ ሥነ ሥርዓትና መሰል ባህላዊ ድርጊቶች ኢትዮጵያን የዓመቱ ባህላዊ የቱሪዝም መዳረሻ ሽልማት ለማግኘት አስችሏታል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ቱሪዝም ድህነትን በመቀነስ፣የኢኮኖሚ ነጻነትን በማጎናጸፍና ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የቱሪዝም ልማትን ማሳደግን በተመለከተ ባበረከቱት ሚና የ2015 ምርጥ የቱሪዝም መሪ ሽልማት ከፕሬዚዳንቱ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም "ሽልማቱ አገሪቱ ከዚህ በፊት ያልተዳሰሱ ባህሎችና ቅርሶችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ የበለጠ ያተጋናል"ብለዋል።

ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ባህላቸውንና ቋንቋቸውን የሚያስተዋውቁበት መንገድ በመመቻቸቱ ኢትዮጵያ የዓለም የባህልና የቱሪዝም መዳረሻ አገር ሽልማትን በቀጣይ ዓመታት ማሸነፏን እንደምትቀጥልም ተናግረዋል።

የቱሪስቶች ቀዳሚ መዳረሻ አገር ለመሆን ዘርፉ የሚጠይቃቸውን የመሰረተ ልማት፣የህግ ማዕቀፎችንና መሰል ስራዎችን እየተሰሩ መሆናቸውን አቶ ኃይለማርያም አስረድተዋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር አቶ አሚን አብዱልቃድር በበኩላቸው ሽልማቱ የሕዝቡ፤የባለሃብቱና የመንግስት የተቀናጀ ጥረት ውጤት እንደተገኘ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ እኤአ በ2025 በአፍሪካ ካሉ ምርጥ አምስት አገሮች አንዷ ለመሆን የረጅም ጊዜ ዕቅድ በመንቀሳቀስ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል። በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ ላይ ወደ አገሪቱ የሚገቡ ቱሪስቶችን አንድ ሚሊዮን ለማድረስና ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ የተያዘው ዕቅድ መሳካቱን አብራርተዋል።

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ)የጫምባላላ በዓል፣የገዳ ባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት፣የድሬ ሼክ ሁሴን መስጊድ፣የባሌ ተራሮችንና ሌሎች ቅርሶችን በቋሚነት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

አገሪቱ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወደ አገሪቱ የሚገቡ ጎብኚዎችን ከሁለት ሚሊዮን በላይና ገቢውን ደግሞ ከ6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ የሚያራዝሙ የመሰረተ ልማት ግንባታና ሌሎች ዘርፉ የሚጠይቃቸውን ስራዎችም ይከናወናሉ። የአውሮፓ የቱሪዝምና የንግድ ምክር ቤት በ2014 ዚምባብዌን በ2013 ደግሞ ላኦስን የዓለም የቱሪዝም ምርጥ መዳረሻዎች አድርጎ መሰየሙ ይታወቃል።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

No comments:

Post a Comment